የኢትዮጵያውያን የስራ ስምሪት በሳዑዲ አረብያ | ኢትዮጵያ | DW | 20.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያውያን የስራ ስምሪት በሳዑዲ አረብያ

ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ከሚቀጥለዉ ሚያዚያ ወር ጀምሮ  ለስራ  ወደ ሳዉዲ አረቢያ እንደሚቡ ተገለፀ።ኢትዮጵያዉያኑን ለመቀበል የሚመለከታቸዉ የሳዉዲ መስሪያ ቤቶች የቬዛና ተያያዥ ቢሮክራሲዎችን ላይ ዝግጅት እያካሄዱ መሆኑንም አል ጋዜቲ የተባለ አንድ የሳዉዲ አረቢያ ጋዜጣ ዘግቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57

20 ሺ ኢትዮጵያዉያን በሳዉዲ አረቢያ ለስራ ይሰማራሉ

ጋዜጣዉ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ጠቅሶ እንደዘገበዉ ለስራ ወደ ሳዉዲ አረቢያ የሚገቡት 20 ሺህ ኢትዮጵያዉያን  ቢያንስ ለ30 ቀናት ስልጠና የወሰዱ ፤ ጤንነንታቸዉ የተሟላና ከወንጀል ነፃ መሆናቸዉን መስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል።ስለ መካከለኛዉ ምስራቅ የኢትዮጵያዉያን የስራ ስምሪት ሲነሳ በአሰሪዎቻቸዉ የሚደርስባቸዉ በደል ብዙ ጊዜ ተያይዞ ይነሳል።ኢትዮጵያዉያኑ ከአሰሪዎቻቸዉ ጋር ግጭት ዉስጥ ከሚያስገባቸዉና ጉዳይ ዉስጥ ደግሞ ለሚሄዱበት ሀገር ስራ በቂ ልምድና ስልጠና አለማግኔት አንዱ ምክንያት መሆኑ ይነገራል።በህጋዊ መንገድ ሰራተኞችን ወደ ሳዉዲ አረቢያ ለመላክ ፈቃድ ከወሰዱ የኤጀንሲ ባለቤቶች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መልኬ ገ/ሚካኤል ችግሩን ያዉቁታል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም የኢትዮጵያ መንግስት በ2008 ዓ/ም ኢትዮጵያዉያኑ ሰራተኞች ስልጠና ወስደዉ ወደ  ስራ እንዲሰማሩ ደንግጓል።አዋጁ ከዚህ በፊት ብዙ እየተሰራበት ባይሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የተሻለ ነገር መኖሩንና ነዉ አቶ መልኬ የሚናገሩት።ያ መሆኑም በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ቀደም ሲል ይከሰት የነበረዉን ችግር ያቃልላል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

ኢትዮጵያዉያኑን በሳዉዲ አረቢያ የቀረበዉን መስፈርት አሟልተዉ ያለስጋትና ችግር እንዲሰሩ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምን ዝግጅት እየተደረገ ነዉ በሚል  በኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ገብሬን DW አነጋግሯል።እሳቸዉ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የአንድ ቀን የመግቢያ ስልጠና ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን የተሻለ ተከፋይና ተፈላጊ ለማድረግ መደበኛ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነዉ።

ስልጠናዉ በሀገር ዉስጥ ተቀጥረዉ እንዲሰሩ ጭምር የሚሰጥ ሲሆን 8ተኛ ክፍልና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ  ያላቸዉና ለመስራት ፍላጎት ያላቸዉ ወጣቶች እንዲሰለጥኑ መደረጉንም አቶ ፈቃዱ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በ2008 ዓ/ም ባወጣዉ አዋጅ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በዝግ አካዉንት በባንክ እንዲያስቀምጡም ይደነግጋል።ይህ ገንዘብ በሰራተኞቹ ላይ ችግር ቢፈጠር እንደ መድህን ዋስትና ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤አዋጁ በአሁኑ ወቅት በተግባር እየተሰራበት መሆኑንም  አቶ ፈቃዱ ገልፀዋል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጨነዉ ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic