የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዕጣ በኬንያና ዝምባብዌ | ይዘት | DW | 27.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ይዘት

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዕጣ በኬንያና ዝምባብዌ

ኢትዮጵያውያን በብዛት ወደ ደቡባዊው አፍሪቃ ይሰደዳሉ ፤ የመጨረሻ የጉዞ መዳረሻ ደቡብ አፍሪቃ መሆኗ ነው። ከዚያው ከደቡብ አፍሪቃ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እየተገደሉ አስከሬን ወደ ትውልድ ሀገር የሚላክበት ሁኔታ አልተገታም። ይህን ዘግናኝ ድርጊት የደቡብ

default

መንግሥት ፤ የአፍሪቃ ሕብረትም ሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሊገቱት አልቻሉም። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያን ፤ አሁንም መከራ ወደሚያጋጥምባቸው አገሮችም መሰደዳቸውን አላቆሙም።

ባለፈው ሰኞ በኬንያ 101 ኢትዮጵያውያን ተይዘው ሲታሠሩ ፣ 179 ኙ ደግሞ ዝምባባዌ ውስጥ ተይዘው ከታሠሩ በኋላ፣ ተገደው የሚጋዙበትን ዕለት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የሐራሬ ፍርድ ቤት ዳኛ ቴንዳይ ማሕዌ ፤ ዕድሜአቸው በ 15 እና 28 መካከል እንደሆነ የተነገረላቸውን 179 ኙ ን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፤ ተገደው ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ሲሉ በይነዋል። ይህን የሰሙ መገናኛ ብዙኀን፤ ለስደተኞቹ የሚቆረቆሩም ሆኑ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ምን ብለው ይሆን?! በዚያው በሐራሬ፤ ዝምባባዌ የሚገኘውን የዶቸ ቨለ ዘጋቢ ኮሎምበስ ማቭሁንጋን በስልክ ጠይቄው ነበር።

«በፍጹም --እንዳሉን ስለተያዙት ኢትዮጵያውያን የሰሙት ጉዳይ የለም። የሰሙት የሰዎቹ ጉዳይ ፍጻሜ ካገኘ እንዲባረሩ ከታዘዘ በኋላ ነው።»

በእግር ፣ ተራራውን ፤ ሸለቆውን ፣ በረሃውን በእግር ጉዞ በማቋረጥ ፤ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቁር ችሎ ፣ ከሀገር ሀገር እያቆራረጡ በመጓዝ ፣ ከዱር ዐራዊት ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ ፤ ከ ድንበር ጠባቂዎች ቁጥጥር አልፎ ካለሙት ቦታ ከመድረስ በፊት የሰሞኑን ዓይነት ብርቱ ሳንክ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም። ኮሎምበስ፤ ኢትዮጵያውያንን ፈልጎ ለማግኘት ቢቸገርም ወደ ኤምባሲም ደውሎ እንደነበረ ገልጾልኛል።

«ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ደውዬ ነበር፤ ስለኢትዮጵያውያን ስደተኞች መያዝ ከጋዜጦች ከመገንዘባቸው በስተቀር የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ነው የነገሩኝ። ይሁንና የዝምባብዌ የፍልሰት ጉዳይ ባለሥልጣናት መንግሥት መሣፈሪያቸውን አዘጋጅቶ እስከሚልካቸው ድረስ፤ ስደተኞቹን ይዘው እንደሚያሥሯቸው ነው የገለጹት፤ ይህም መደረግ እንዳለበት በአገሪቱ ሕግ የሠፈረ ጉዳይ ነው። »

ወደ ደቡባዊው አፍሪቃ የሚጓዙ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ፤ የመጨረሻ ግባቸው በመግቢያችን ላይ እንዳልነው ደቡብ አፍሪቃ ናት። ራቅ ካለ የአፍሪቃ ሃገር ያን ያህል ረጅም ጉዞ ማድረግ ፣ የዝምባብዌን ተወላጆች ማስገረም ብቻ ሳይሆን አጥብቀው እንዲጠይቁም ሳይገፋፋ አልቀረም፣ ኮሎምበስ ማቭሁንጋ አምና ይህን ርእሰ ጉዳይ አንስቶ በጥሞና ማነጋገሩን እንዲህ ያስታውሳል።

አንዳንዶቹን አነጋግሬአቸው ነበር። 7 ኢትዮጵያውያን ነበሩ ዝምባብዌ እንደገቡ በቡድን ያነጋገርኳቸው። እነርሱ እንደነገሩን በአፍሪቃ ቀንድ ያለw ውዝግብ --ኤርትራ --ኢትዮጵያ ፣ በጣም አስከፊ ነው። እናም ወደ አፍሪቃው ቀንድ ከመመለስ ፣ አንድም ወደ ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መጓዝ አለበለዚያም ፣ ምንም እንኳ ዝምባብዌ ራሷ ችግር ያለባት ሀገር ብትሆንም ከምንም ከምንም እዚህ እንደሆንነው ብንሆን ይሻላል በማለት ነበረ ያወጉኝ»

በአፍሪቃ የስደተኞች ጉዳይ በክፍለ ዓለምም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነው። የዘንድሮው የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀ መንበር የዝምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ መሆናቸው የታወቀ ነው። የአፍሪቃ ሕብረት ፤ የመሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ የአፍሪቃ ሕዝብም ሕብረት ሊሆን እንደሚገባ በየጊዜው ነው የሚነገረው። መንግሥታት ለህዝብ ግንኙነትና የአፍሪቃ ዜጎች በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ላይ የቱን ያህል ይሆን የሚያጤኑበት!?

ባለፉት ዓመት ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ፤ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የአሥር ቤት ዘበኞች በአፍሪቃ ሕብረት ሊከሠሱ እንደሚfገባ ነው። ይሁን እንጂ የአፍሪቃ ሕብረት የመንግሥታትን አቋም በማክበር ላይ ነው የሚያዘነብለው። እናም እዚህ ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ከመመልከት መንግሥት ለሚከተለው መርሕ ነው የሚቆመው። ስለዚህ ፣ ሕብረቱ በአዲስ አበባ ያለው መንግሥት የሚለውን ሳይሆን ከትውልድ አገራቸው የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን የሚሉትን ሊያዳምጥ ይገባል።»

ትምህርትንም ሆነ ሥራን አቋርጦ ፣ «እልፍ ቢሉ እልፍ » በሚል ያልተጨበጠ ተስፋ ፣ ሃገራትን እያቆራረጡ ለመጓዝ መሞከር ምነው እግሬን በሰበረው የሚያሰኝ ፣ እጅግ አስከፊ ከሆነ ችግር ጋር መጋፈጥና ፤ መከራ መቀበል ሊያጋጥም እንደሚችል ባለፉት ጊዜያትና ከሰሞኑንም በኬንያና ዝምባብዌ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው በበቂ ሁኔታ አመላካች ነው።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic