1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና ልማት

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 2016

"ኢትዮጵያዊነት እሴቶች እንቀፍ ስንል ሕዝብን ማወቅ፣መቅረብ ለአዲሱ ዜጋ እድል መስጠት፣የአዲሱ ዜጋ ስንል የብዙ ቋንቋ፣ የባህል ባለቤት የሆነ፣ የሚቻቸል፣የነቃ፣ብልዕ፣አዋቂ፣ተፍጨርጫሪ፣ተንቀሳቃሽ፣ ትምህርት ፈላጊ፣መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅ፣ቴክኖሎጂ ተቀባይ፣ሥራ ፈጣሪነትን ያጠቃልላል።"

https://p.dw.com/p/4ja5h
Logo Ethiopiawinet
ምስል Ethiopiawinet

"የአብሮነትና የጥንካሬ ሚስጢር"

በአሜሪካ የሚገኘው፣ ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ጉባዔ፣" ኢትዮጵያዊነት የአብሮነት እና የጥንካሬ ምሥጢር" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ተከታታይ የበይነ መረብ ውይይት ሰሞኑን ተካሄዷል።

የኢትዮጵያን ህዝብ ለብዙ ሺህ ዓመታት ያጋመዱ በተባሉ የአብሮነት እሴቶችን  በመረመረው በዚህ ጉባኤ ላይ፣ በአውስትራሊያው ከርቲን ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ይርጋ ገላውየኢትዮጵያዊነት እሴትን ከመሬት ጋር አስተሳሰረው ተመልክተውታል።

"የኢትዮጵያን ህዝብ ማወቅ ማለት፣ሕዝቡ ሕይወቱን የመሰረተበትን የመሬቱን ጸባይ መረዳት፣ ከመሬት ጋር ያለውን ትስስር ማክበር ፣በመሬቱ ላይ ያለውን መብት ማስከበርና  የመክሊቱን ፍሬ መጀመሪያ እርሱ እንዲጠግብ፣የእርሱ ሃብት እንዲሆን አበክሮ መስራትን ይጠይቃል።"

የኢትዮጵያ ገበሬዎች መሬትን አርሰው በመብላታቸው፣ህይወታቸው የተመሰረተበት በመሆኑና አስተሳሰባቸውን የሚጋራ በመሆኑ አንድ ያደረጋቸዋል ያሉት ዶክተር ይርጋ፣ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ማለት  ከመሬቱ ጋር መታረቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የጋራ እሴቶች ለዘላቂ ልማትና ሰላም

በቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት የፕላንና ልማት ሚኒስትር የነበሩት አቶ መርስዔ እጅጉ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ለዘላቂ ልማትና ሰላም ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል።

"ኢትዮጵያዊነት እሴቶች እንቀፍ ስንል፣ምን ማለት ነው?ሕዝብን ማወቅ፣መቅረብ ለአዲሱ ዜጋ እድል መስጠት፣የአዲሱ ዜጋ ስንል የብዙ ቋንቋ፣ የባህል ባለቤት የሆነ፣ የሚቻቸል፣የነቃ፣ብልህ፣አዋቂ፣ተፍጨርጫሪ፣ተንቀሳቃሽ፣ ትምህርት ፈላጊ፣መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅ፣ቴክኖሎጂ ተቀባይ፣ሥራ ፈጣሪነትን ያጠቃልላል።"

ባለፉት ስድሳ ዓመታት፣ የኢትዮጵያ መንግስታትና መሪዎች፣አውቀውሞ ሆነ ሳያውቁ ከኢትዮጵያዊነት በማፈግፈግ፣ውድቀትን መርጠዋል የሚሉት አቶ መርስዔ፣ጠባብ አስተሳሰብ ካሉት የብሔረሰብ ትርክት ወደ ልማት ትርክት በመሸጋገር፣ ድህነትና ኃላቀርነትን ማስወገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያዊነት እሴቶችና የተማሩ ሰዎች ሚና

በዚሁ ውይይት፣በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የስነ መለኮት ምሁር ሊቀ ማዕምራንን መምህር ዶክተር ዘበነ ለማ፣ የኢትዮጵያዊያንን አብሮ የመኖር የጋራ እሴቶች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

"እንግዳ በመቀበል፣ ሌላውን በማክበር፣ የራስንም በመጠበቅ የራስን ባለማሰወሰድ፣የሌላውንም ባለመንጠቅ እሴት ላይ የተመሰረተ ነው።የኢትዮጵያ እሴት፣ አብሮ የመኖር፣ እምነቶችን የማክበር፣የሌሎችንም ሳይገፉ የራስንም አክብሮ መኖር በራሱ ውበት ነው ለአንድ ሃገር።"

ኢትዮጵያ ከገጠማት በጎሳና በነገድ አስተሳሰብ አውጥቶ፣ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ፣ከተማሩ ሰዎች ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅም ዶክተር ዘበነ አሳስበዋል።

ታሪኩ ሃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር