የኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ ስቃይ | ኢትዮጵያ | DW | 21.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ ስቃይ

የዝና እዘዘው የአስራ ስድስት አመት ልጅ ሳለች ከጎንደር ወደ ሱዳን ለመሄድ ስትወስን ከፊቷ ስለተደቀነው የምታውቀው አንዳች ነገር አልነበረም። ልታስታውሰው የምትፈልግ አትመስልም። የግድ ስታስታውሰው ግን ከስሜቷ ጋር ግብ ግብ ትገጥማለች። ሐዘን ይገባታል። ንግግሯም ይቆራረጣል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:46
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:46 ደቂቃ

ከጎንደር እስከ ሱዳን-የኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ ስቃይ

ተወልዳ ያደገችው በጎንደር ገጠራማ አካባቢ ነው። አባቷ ከቤት የሉም። ትምህርቷን አቋርጣ ከአክስቷ ሱቅ ትሰራም ነበር። «በጣም የምወዳት» የምትላት የአክስቷ ልጅ ወደ ሱዳን ለመሄድ መወሰኗን ነገራቻት። የዝና አብራት ከምትበላውና ከምትጠጣው የአክስቷ ልጅና ወዳጇ መለየት አልሆነላትም። ተስማማች።

በስሚ ስሚ ሰዎችን ከጎንደር ወደ ሱዳን የሚወስድ ሰው የመኖሩ መረጃ ደረሳት። ፈልጋ አገኘችው። የምታውቀው ያገሯ የመንደሯ ሰው ሆኖ ተገኘ። «ውሰደኝ ስለው እሺ ችግር የለም። አሁን ብር ካልከፈልሽ ሰርተሽ ተከፍይኛለሽ አለኝ።» የምትለው የዝና ካገሯ ደላላ ጋር በስድስት ሺህ የኢትዮጵያ ብር መስማማታቸውን ታስታውሳለች።

እንደ የዝና እዘዘው የተሻለ የስራ እድልና ገቢ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ጅቡቲ፤ግብፅ፤ሶማልያ፤ሱዳንና የመን ይጓዛሉ። ብዙዎቹ ዋንኛ መዳረሻቸው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ናቸው። በመነሻ እና መድረሻቸው መካከል ደግሞ ህገወጥ-የሰዎች አዘዋዋሪዎች አሉ። የዝናና ሌሎች አስራ አንድ እንስቶች በተለምዶ ሚኒባስ ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ መኪና ወደ መተማ ተጓዙ። ከመተማ ወደ ሱዳን ለመጓዝ ሌላ ሁለት ሳምንት መጠበቅ ነበረባቸው። አሁን የተጓዦቹ ቁጥር እነ የዝናን ጨምሮ አርባ ተሻግሯል።

የሚቀርበው ምግብ ደረቅ ዳቦና የማሽላ እንጀራ እንደነበር የዝና ታስታውሳለች። ከአካባቢው ሙቀትና ሁኔታ ጋር መስማማት ያዳገታት የዝና ሰውነቷ በትንኝ ንክሻ አባብጧል። ወደ መጣችበት የመመለስ ሃሳብ ነበራት። ግን አልሆነም። እናም ሁለተኛው መንገድ ገላባትን በመሻገር ተጀመረ። መንገደኞቹ ደግሞ ስልሳ እንስቶች አስራ ሁለት ወንዶች ሆነዋል።«ወንዙን ተሻግረን የአንድ ሰዓት መንገድ እንደሄድን ገጀራ የያዙ ስድስት ሽፍታዎች ያዙን።» የምትለው ድምጿ መቆራረጥ ጀመረ። ወደ ሱዳን ሊወስዳቸው በስድስት ሺህ ብር የተዋዋለው ደላላ ኢትዮጵያ ቀርቷል። በሰልፍ የሚጓዙት መንገደኞች ከፊትና ከኋላ ሁለት ሱዳናውያን አጃቢዎች አሏቿው። እንደ የዝና ከሆነ የሽፍቶቹ የመጀመሪያ ጥያቄ «መጀመሪያ ገንዘብ አምጡ» ነበር። መንገደኞቹ በቂ ገንዘብ የላቸውም። ደላላው ተደውሎ ሲጠየቅ «እኔ ብር የለኝም።» አለ። የዝና ደላላው «ያላችሁን አዋጥታችሁ ስጡ።» ማለቱን ታስታውሳለች። ሰባ ሁለቱ መንገደኞች ያላቸውን አጥተው ሲሰጡ ሁለተኛው ጥያቄ ተከተለ። «ስድስት ሴት ለስድስታችን እንፈልጋለን።» ማለታቸውን ስታስታውስ ሐዘን በተቀላቀለበት የቁጭት ስሜት ነው።

ከአመት በፊት የአሜሪካ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ይፋ ያደረገው ዘገባ እንደሚጠቁመው በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ሁለተኛ አገር ለመሻገር ከሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን 85 በመቶው እንስቶች ሲሆኑ ዋንኛ ምክንያታቸው ደግሞ የተሻለ የስራ እድል ፍለጋ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጥጋቢ ውጤት ያላመጡ አሊያም ያቋረጡ እና ስራ አጥ የሆኑ እንስቶች ጅቡቲና ሱዳንን በማቋረጥ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለመድረስ የህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ያማክራሉ። በጉዟቸው ወቅት አስገድዶ መደፈር፤ ያለ ክፍያ በግዳጅ ስራ የመስራት፤እስርና እንግልት ይገጥማቸዋል። እነ የዝናም የገጠማቸው ይኸው ነው። አብረዋቸው የሚጓዙ ወንዶች እንስቶቹን ከጥቃት ለመከላከል ቢሞክሩም የተረፋቸው ድብደባ ነው። የዝና ከአምስት አመታት በፊት የገጠማትን ስታስታውስ ሐዘን ይገባታል።

ሱዳናውያኑ ከመረጧቸው እንስቶች መካከል የአስራ አራት አመት «ቆንጆ ልጅ» እንደነበረችበት የምትናገረው የዝና «አልሄድም ብላ እየጎተቷት ሲወስዷት፤ሲደበድቧት፤ከስድስቱ ውስጥ እስካሁን ከሆዴ ትገባለች።» ስትል ትናገራለች።

ከየዝና ጋር በመጓዝ ላይ ከነበሩትና በሱዳናውያኑ ከተመረጡት መካከል ከመካከለኛው ምስራቅ የተመለሱ ኢትዮጵያውን ነበሩበት።

ለሱዳናውያኑ የወሲብ ፍላጎት ተመርጠው ከተወሰዱት ስድስት እንስቶች መካከል አንዷ ብቻ መመለሷን የዝና ለዶይቼ ቨሌ ተናግራለች። የየዝናን ስሜት ላለፉት አምስት አመታት የያዘችው የአስራ አራት አመት ታዳጊ «ሞታለች ይላሉ። ድናለች ይላሉ።» ስትል እጣ ፈንታዋ አለመታወቁን ትናገራለች።

የዝና እዘዘው በሱዳናያኑ ከተመረጡት እንስቶች መካከል የነበረች ቢሆንም በእድል ተርፋለች። በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሰው ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ደሞዟን ለህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪው ከፍላለች። ሶስት አመት በቆየችበት ሱዳን ከተዋወቀችው ሰለሞን ጋር የሰሐራ በረሃና የሜድትራኒያን ባህርን አቋርጣ አውሮጳ ከትማለች። ጀርመን ከገባች አምስት ወራት ያስቀጠረችው መንገደኛ የአምስት ወር ነፍሰ-ጡር ነች። ከጎንደር እስከ ጀርመን ስትጓዝ ከልቧ የከተበችው አሰቃቂ ትዝታ ቢረብሻትም በአዲሱ መኖሪያ ቤቷ አዲስ ትዝታ ለመፍጠር ከባለቤቷ ጋር እየታገለች ነው።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic