የኢትዮጵያዉያን የባህል ትስስርና ችግርን የመፍታት አቅሙ | ባህል | DW | 30.07.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የኢትዮጵያዉያን የባህል ትስስርና ችግርን የመፍታት አቅሙ

ባህላችንን ባለማጥናታችን፤ አንዱን ባህል ለሌላዉ ባለማስተዋወቃችን ፤ ሃገራችን ወደ ቀዉስ እንድትገባ ዳርጓታል።በሃገራችን የሚገኘዉን የሌላዉን ማኅበረሰብ ባህልን በማጥናት ለሌላዉ ወገን ብናስተዋዉቅ መከባበሩም መዋደዱም እየጨመረ ይሄድ ነበር። አሁን ሃገራችን ዉጥንቅጥ ዉስጥ የገባችዉ፤ ለራሳችን ስላልሰራን ነዉ።»   

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:03

ባለፉት ዓመታት ከባህላችን አንዱን ነገር በማዉጣት ወጣቱ እንዲጣላላ እንዳይከባበር ነዉ ያደረግነዉ

 

«ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን አንድ ማንነት ብቻ አይደለም ያለዉ። ብዙ አይነት ማንነት አለ። ማንነት ቋንቋ ብቻ አይደለም። ሃይማኖት ዉስጥም ማንነታችን አለ። አለባበሳችን ዉስጥም ማንነታችን አለ። ታሪካዊ ግንኙነታችን ዉስጥም ማንነታችን አለ። ብዙ አይነት ነገር ነዉ ማንነታችን ዉስጥ አለ።  

ይህን ያሉት ስለኢትዮጵያዉያን የተለያዩ ባህሎችና ትስስራቸዉ የነገሩን የሰው ልጅ ጥናት ወይም ሥነ-ሰብእ «አንትሮፖሎጂ» ምሁር አቶ ዳዊት ሳሙኤል ናቸዉ። አቶ ዳዊት ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በአንትሮፖሎጂ ማለትም ስለ ሰው ልጆች ሁኔታና ግንኙነቶችና ባሕል ትምህርትን ተከታትለዉና ጥናት አድርገዉ የመጀመርያ ዲግሪያቸዉን ይዘዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸዉን ደግሞ በቅርቡ Global labour studies ማለትም የጉልበት ሰራተኛ ኤኮኖሚና ሕጉን በተመለከተ በጀርመን በርሊን ከሚገኘዉ ዩንቨርስቲ ተቀብለዋል። አንትሮፖሎጂ ወይም በአማርኛ  ሰብእ ምን ማለት ይሆን አቶ ዳዊት ሳሙኤል ያስረዳሉ።  

«አንትሮፖሎጂ ማለት የሰዉ ልጅ ጥናት በአማርኛ ሥነ-ሰብእ ማለት ነዉ። አንትሮፖሎጂ በመሰረቱ አራት አይነት የጥናት ዘርፍ አለዉ።  አንደኛዉ ስለማኅበረሰብ የሚያጠና ነዉ። በዚህ ጥናት የማኅበረሰቡን አባት እናት ቅድም አያት ጨምሮ ወደኋላ ያለዉን ታሪክ የሚያጠና ነዉ። ሶሻል አንትሮፖሎጂ ይባላል። ሁለተኛዉ በሰዉ ልጆችና በእንስሳ መካከል ያለዉን ግንኙነት የሚጠናዉ ነዉ። ሌላዉ ጥንታዊ እና በቁፋሮ የሚገኙ የሰዉ ልጅ ታሪክን የሚያጠና ነዉ። እኔ ያጠናሁት የማኅበረሰብን ባህል እና የታሪክ ሂደትን የሚመለከተዉን ነዉ።    

የእዚህ ጥናት ጠቀሜታ በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ምንድን ነዉ ?   

«ጠቀሜታዉ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሄረሰቦች እና ጎሳዎች ያሉባት ጥንታዊ ሃገር ናት። የሰዉ ልጆች መነሻ ሃገር ናት። በሌላ በኩል ደግሞ በሌላዉ አካባቢ የጠፋ ግን ጥንታዊዉ ባህል አሁንም ኢትዮጵያ ዉስጥ አለ። እናም ያንን ታሪካችንን ማወቃችን እና ማጥናታችን እንዴት ልንኖር እንደምንችል ፤ እንዴት ሃገራችንን የተሻለ ልናደርግ እንደምንችል ፤ እንዴት ለሌላዉ ባህላችንን ልንሰጥ እንደምንችል፤ እንዴት ራሳችንን ጠብቀን እንደምንኖር የሚያሳየን መሳርያ ነዉ። መጀመርያ የራሳችንን ማወቅ አለብን የእዚህ ሳይንስ ጥናት ዋና ዘርፍ እና አተኩሮ ይህ ነዉ።»  

 

እንደሚታወቀዉ ኢትዮጵያ ከ 80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባት ሃገር ናት ። የዛኑ ያክል ደግሞ የተለያዩ ባህሎች እና የተለያዩ ልምዶች በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ይታያል ። ከዚህ ባህልና ልምድ መካከል ታድያ ምን  ያህሉ ተጠንቶአል። ገሚሱ ተጠንቶአል ማለት ይቻላል? ምን ያህሉ ተጠንቶአል ብለን ልንገምት ወይም ልንናገር እንችላለን?

«ኢትዮጵያዉያን ምሁራን በዚህ ዘርፍ ብዙ ጥናትን አድርገዋል ብዬ ባልልም ፤ ፈረንጆቹ እኛ ሃገር ላይ  መጥተዉ ብዙ ጥናት አድርገዋል።  ፈረንጆቹ እስከ ገጠር ፤ እሩቅ እስከ ምንለዉ እስከ ሙርሲ ድረስ እየሄዱ ፤ እስከ ከፋ ድረስ እየሄዱ ፤ እዛዉ ኑሮአቸዉን እያደረጉ አጥንተዋል። አፋር ድረስ ይህንኑ ለማጥናት ይሄዳሉ። እነሱ ግን የሚያጠኑት ለኛ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸዉም በሚጠቅማቸዉ መንገድ ነዉ። በተለይ አሁን ዉጭ ሃገር ዩንቨርስቲዎች ዉስጥ ስመለከት ስለኢትዮጵያ ብዙ ጥናት መጠናቱን አይቻለሁ። ግን ከኛ ይልቅ ስለኢትዮጵያ ብዙ አጥንተዉ በደንብ የያዙት ፈረንጆቹ ናቸዉ። »

እና ባህላችንን ስለማናዉቅ ነዉ። በተለይ ወጣቱ ትዉልድ ፤ ባህሉን ስላልተማረ ስላላወቀ ፤ ስላላስተማርነዉ  ስላልሰጠነዉ ሰሞኑንን እና ባለፉትም ዓመታት በታየዉ ቀዉስ የስነ-ምግባር ጉድለት እና አሰቃቂ ሁኔታ ታይቶአል። አሁንም በብዙ ቦታዎች እየታየ ነዉ። ይህ በፊት የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትነት መጥፋቱ ስለማኅበረሰቡ ባለመጠናቱ ነዉ።?

« ወደዚህ ጥያቄ ከማለፌ በፊት ስለባህል ምንነት ልናገር። ባህል ማለት በማኅበረሰብ ዉስጥ ሁሉን ነገር የሚያጠቃልል ነዉ። የምንለብሰዉ ልብስ፤ ከምንመገበዉ ምግብ፤ ከምናስበዉ አስተሳሰብ፤ ከምናገረዉ ቋንቋ ፤ ሰዉ ለሰዉ ያለን ግንኙነት ሁሉ ያጠቃለለ ነዉ። ሃይማኖት ሁሉ ባህል ዉስጥ ይጠቃለላል። ባህል ዉስጥ የማኅበረሰብ ልማዶች ሁሉ ይጠቃለላሉ። እና ስለማኅበረሰብ ባህል ጥናት ማጥናታችን ለቀጣይ ትዉልድ እንዲተላለፍ ነዉ። ለምሳሌ ልጆች ከሦስት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ነዉ ባህላቸዉን፤ ሃይማኖታቸዉን እንደሚያዉቁ ዓለም አቀፍ ጥናት የሚያሳየን። እኛ ስለባህላችን ስለ አኗኗራችን ስለወጋችን ምን አስተምረናል ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ባህላችንን ለማቆየት ምን አድርገናል፤ ልንል ይገባል። እነዚህ ጥናቶች ተቋሞቻቸን ዉስጥ አሉ ዉይ? ባለፉት ሰላሳ ዓመታት አልያም ከዝያ በላይ በእኛ ሃገር የተሰራዉ የራሳችን ባህል ራሳችንን ጠልፎ እንዲጥለን ብቻ ነዉ።

ከባህላችን አንዱን ነገር በማዉጣት ወጣቱ እንዲጣላላ እንዳይከባበር ነዉ ያደረግነዉ። እና ባህላችንን ባለማጥናታችን፤ አንዱን ባህል ለሌላዉ ባለማስተዋወቃችን ፤ ሃገራችን ወደ ቀዉስ እንድትገባ ዳርጓታል። አሁንም በማኅበረሰቡ  ወግ ባህል እና ልማድ ላይ ጥናት ካላደረግን እራሱ ማኅበረሰቡ እንዲያዉቀዉ ካላደረግን ፤ አገራችን አሁን ካለችበት ወደባሰ ሁኔታ ልታመራ ትችላለች። ከኦሮኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ባልመጣም እንደ ቦረና ባህል የሚያስደስተኝ ነገር የለም። የእነዚህን ሰዎች ባህል ለሌላዉ ማኅበረሰብ ሄጄ ባስተዋዉቅ በጣም ያስደስተኛል። ምክንያቱ ደግሞ የዚህን ማኅበረሰብ ባህል በመማሪ ነዉ። ልክ እንደዚህ ሁሉ የሌሎች ማኅበረሰብ ባህልን በማጥናት ለሌላዉ ብናስተዋዉቅ መከባበሩም መዋደዱም እየጨመረ ይሄድ ነበር። አሁን ሃገራችን ዉጥንቅጥ ዉስጥ የገባችዉ፤ ለራሳችን ስላልሰራን ነዉ።»   

ወጣቱን እናስተምር ወጣቱ ላይ ስራ መሰራት አለበት እንላለን ፤ የዚህ ትምህርት መሰረተ ልማት እንዴት ነዉ መሆን ያለበት?

አዜብ ታደሰ  

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic