የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች እልቂት | ኢትዮጵያ | DW | 28.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች እልቂት

የተረፉት እንደነገሩን ሾፌሩ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ይጮሁ፥ ይደበድቡም ነበር።የጣር-ጩኸት። የሞት-ሽረት ሲቃ። የመጨረሻ ሙከራ።ሾፌር ግን ይዘዉራል።ወደ ማላዊ።ሐበሻ ይረግፍ ያዘ፥ አንድ፥ ሁለት፥ ሰወስት እያለ እየተዝለፈለፈ ወደቀ።ከዚያስ?

***Für mögliche Ergänzungen der Karte, wie z.B. andere Sprachen, zusätzliche Orte oder Markierungskreuz, wenden Sie sich bitte an infografik@dw-world.de (-2566), Außerhalb der Bürozeiten an bilder@dw-world.de (-2555).***


በጭነት መኪና ተሳፍረዉ ከታንዛኒያ ወደ ማላዊ ለመሻገር የሞከሩ አርባ-አንድ ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ሞቱ።የታንዛኒያ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ስደተኞቹ የሞቱት በተሳፋሪዎች ብዛት በተጨናነቀ የጭነት መኪና አየር አጥተዉ ወይም ታፍነዉ ነዉ።ከሟቾቹ ጋር ይጓዙ የነበሩ ሌሎች ከሰባ በላይ ስደተኞች በሕይወት ተርፈዉ ታንዛኒያ ዉስጥ ሠፍረዋል።ስደተኞቹ ተሳፍረዉበት የነበረዉ የጭነት መኪና ሾፈር እስከ ዛሬ አልተያዘም።ከታንዛኒያ በማላዊ አቋርጠዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር የሚሞክሩ ኢትዮጵያዉያን በጅምላ ሲያልቁ ባንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ያሁኑ ሁለተኛዉ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።


ትናንት ሟቾቹ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ዜጎች ናቸዉ ተብሎ ነበር።ዛሬ ግን፥
«በሙሉ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።» የታንዛኒያዉ ምክትል የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ፔሬይራ ሲሊማ።

የሟቾቹ ቁጥር አርባ-ሰወስት ነዉ ተብሎም ነበር።«አርባ-ሰወስቱም ሟቾች ማለትዎ ነዉ? ጠየኳቸዉ ምክትል ሚንስትሩን።

«የለም አርባ ሰወስቱ ብቻ አይደሉም።ባጠቃላይ አንድ መቶ ሃያ-ሰባት ነበሩ።»

ነበሩ።ከአስከሬን መሐል ሁለት ሰዎች ከነነብሳቸዉ ተገኝተዋል።አርባ አንዱ ግን ነበሩ-ነዉ ወጋቸዉ።እና ኢትዮጵያዉያን ዳግም አስከሬኑን ላላዩ፥ ላልቀበሩት ልጅ ዘመድ-ወዳጃቸዉ ሞት አረገዱ።።ጦር ሜዳ አይደለም፥ ተስቦ፥ ወረርሺኝ፥ ድርቅ-ረሐብም አይደለም።ስደት-እንጂ።ባለፈዉ ሳምንት አርባ-ሰባት፥በዚሕ ሳምንት አርባ-አንድ ኢትዮጵያዉያን ከድሕነት-ችግር ለማምለጥ አገር-ላገር ሲማስኑ የማላዊ ሐይቅ፥ የታንዛኒያ ጫካ ዉጦ አስቀራቸዉ።

ማን ይናገር የነበረ እንበል ይሆን?

«ከመነሻዉ ከኢትዮጵያ በናይሮቢ አቋርጠዉ፥ በታንዛኒያ አድርገዉ ወደ ማላዊ ለመግባት ነበር-ያቀዱት፥ እነሱ እንደነገሩን።»

ምክትል ሚንስትር ሲሊማ።ማላዊ። ከዚያም ደቡብ አፍሪቃ ለመድረስ ስደተኛዉ ለአጓጓዦቹ ወይም ለአስርጎ አስገቢዎች በነብስ ወከፍ ከሰወስት እስከ አራት ሺሕ ዶላር ይከፍላሉ።ከሐምሳ-እስከ ሰባ ሺሕ ብር።ይሕ በጉዞዉ መሐል ለምግብ መጠጥና ለሌላ ወጪ የሚቋጥሩትን አይጨምርም።ጉዞዉ ግን እንዲሕ ነዉ።

«ከኢትዮጵያ በጭነት መኪና ወደ ናይሮቢ ተጉዞዉ፥ ከናይሮቢ በሁለት የጭነት መኪናዎች ተጭነዉ አሩሻ ታንዛኒያ ገቡ።»

አሩሻ ላይ የብረት ሰንዱቁ ከሚቆለፈዉ ካሚዎንም አቅም ጠፋ።እና አንድ-መቶ ሃያ ሰባት ሐበሻ በአንድ የጭነት መኪና፥ ባንድ የብረት ሰንዱቅ እየተፋፈገ፥ ከዉጪ ተቆልፎበት ጉዞ ጀመረ።

«እርግጥ ነዉ በጣም ብዙ ነበሩ።የመኪናዉ አየር ማቀዝቀዣም አይሰራም።በዚሕ ምክንያት ተራ በተራ ይታፈኑ ያዙ።የተረፉት እንደነገሩን ሾፌሩ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ይጮሁ፥ ይደበድቡም ነበር።»

የጣር-ጩኸት። የሞት-ሽረት ሲቃ። የመጨረሻ ሙከራ።ሾፌር ግን ይዘዉራል።ወደ ማላዊ።ሐበሻ ይረግፍ ያዘ፥ አንድ፥ ሁለት፥ ሰወስት እያለ እየተዝለፈለፈ ወደቀ።ከዚያስ?

«ሾፌሩ ለመፈተሽ ምን እንዳነሳሳዉ አላዉቅም።መኪናዉን አቁሞ ጭነቱን ለማየት ከኋላ ዞረ።»

ትልቁን የብረት ሰንዱቅ ከፈተዉ።በጣም ዘግይቷል።ለአርባ አንዱ ደግሞ ፍፁም ዘግይቷል።አስከሬኖቹን ጥሎ፥ መኪናዉን አፅድቶ ተራፊዎቹን ይዞ ጥቂት ከተጓዘ በሕዋላ ቀሪዎቹን ጫካ ዉስጥ ጥሎ ተሰወረ።እስከ ዛሬ አልተያዘም።ተራፊዎቹ እየወደቁ ሲነሱ የአካባቢዉ ገበሬዎች አግኝተዉ አበሉ፥ አጠጧቸዉ እና ለፖሊስ ጠቆሙ።

«ሔድን።አስከሬኑን ሠበሰብን።አሁን ሆስፒታል ዉስጥ ነዉ።የተረፉትን አንድ ቦታ አስፍረን የሕክምናና የምግብ አገልግሎት እየሰጠናቸዉ ነዉ።ኋላ ፍርድ ቤት እናቀርባቸዋለን።አስከሬኖቹን በተመለከተ የመጨረሻ ማረፊያቸዉን ለመወሰን ከኤምባሲያቸዉ ጋር እየተነጋገርን ነዉ።»

አንድ መቶ ሃያ-ሰባቱም ወንዶች ናቸዉ።ወይም ነበሩ።አብዛኞቹ በሃያ-የእድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ-ወጣቶች።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic