የኢትዮጵያዉያን ሰሚ ያጣ ጩኸት | ኢትዮጵያ | DW | 26.05.2014
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያዉያን ሰሚ ያጣ ጩኸት

ግፍ-ሥቃይ መከራ ስንት ዓይነት ነዉ? ክብደት ቅለቱስ የሚለካዉ እንዴት ነዉ ?የየመኑ ስደተኛ እንደሚለዉ በኢትዮጵያዊዉ ስደተኛ ላይ የሚፈፀመዉን ግፍ-ለመዘርዘር ቋንቋ ራሱ አቅመ ቢስ ነዉ።

ኢትዮጵያዊዉ ወጣት ይሰደዳል።ከያሰበበት ሳይደርስ አንድም በረሐ፤አለያም ባሕር-ሕይቅ ዉስጥ ይሞታል።ሌላዉ በየደረሰበት ይገረፋል፤ አካሉ ይቆረጣል፤ይታሰራል፤ይታገታል፤ይሸጣል። ሴቷ በመንጋ ትደፈራለች።

ከግፍ፤መከራ ስቃዩ የተረፈዉ ይጋዛል።ይጮሐል።ሰሚ ግን የለዉም።እንደገና ይጮኸል።ተረኛዉ ይሰደዳል።የሥደት ስቃይ፤ ጩኸት ዑደት።ይጥይቃል-የየመኑ ስደተኛ።የኛም ጥያቄ ነዉ።ከዚሕ ቀደም በርግጥ ጠይቀናል።መልስ የለም። እንደገና ላፍታ እንጠይቅ።እንደገና ጩኸት እንስማ።

ሟቿ ኬንያዊት የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋችና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ዋንጋሪ ሙታ ማሳይ፤«በሬ ሆይ ሳሩን አይተሕ---»የሚለዉን ነባር ኢትዮጵያዊ ብሒል ማወቃቸዉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ወደ አዉሮጳና ሰሜን አሜሪካ ለመሰደድ፤ ሲሞክሩ በየበረሐ-ባሕሩ ሥለሚያልቁ አፍሪቃዉያን ወጣቶች የተናገሩት ግን ለኢትዮጵያዊዉ ነባር ብሒሉን የሚያስታዉስ ነበር።

የአዉሮጳና ሠሜን አሜሪካ ላይ «ሳሩ ይበልጥ አረንጓዴ» ሥለሚመስላቸዉ-ነበር ያሉት ማሳይ-ያኔ።ከሁለት ሳምንት በፊት ከማሳይ ሐገር አጭር መልዕክት የላኩልን ኢትጵያዊ አድማጭ ስደተኛ መሆናቸዉን መልዕክታቸዉ ያሳብቃል።«ሳዑዲ አረቢያ ሥለተሰደዱ ኢትዮጵያዉን ያን ያሕል ስትዘግቡ ኬንያ በምንገኝ ኢትዮጵያዉያን ላይ ሥለሚፈፀመዉ ግፍ ለምንድነዉ የማትናገሩት ይላል መልዕክቱ።

«ሳሩ ይበልጥ አረንጓዴ» ከሚመስለዉ በብዛኛዉ ደቡብ አፍሪቃን በጥቂቱ አዉሮጳ አሜሪካን መድረሻ ግቡ ባደረገዉ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ላይ ከኬኒያ ፀጥታ አስከባሪዎች እስከ ቤት አከራዮች፤ ከታንዛኒያ ሾፌሮች እስከ ማላዊ ጀልባ ነጂዎች ሥለሚያደርሱበት ስቃይ ሰቆቃ ባለፉት ዓመታት ያልተነገረበት ጊዜ የለም።

ያም ሆኖ የኬንያዉ አድማጫችንን መልዕክት ይዘት፤ቅሬታ አዘሉን ድምፀትም አዲስ አሮጌነት እንዲሕ እንዳሁኑ አስተንትነን ሳነበቃ ከሰሜን ሱዳን የደረሰን የሌላ የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ተመሳሳይ መልዕክት አናጠበን።

                  በአብዛኛዉ አዉሮጳ፤ በጥቂቱ እስራኤል ለመግባት አልመዉ የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን በሱዳን ደላሎች እንደ እንስሳ ከመሸጥ መለወጥ ከዳኑ፤ በፀጥታ አስከባሪዎች ይመዘበራሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይገረፋሉ።ከስራት ዱላዉ ሲያገግሙ ሰሐራ በረሐ ላይ በጋጠ ወጦች፤ በዘላኖች፤በመንገድ መሪዎች፤ ይደፈራሉ።ይታገታሉ።አካላቸዉ ተቆርጦ ይሽጣል።በረሐዉ ላይ በዉሐ ጥም፤ ሜድትራንያን ባሕር ላይ በዉሐ ሙላት ያልቃሉ።

የተረፉት ይጮኻሉ። የካርቱም ስደተኞች ጩኽትን ከዚሕ ቀደም ብዙዎች ብዙ ጊዜ ጮኽዉታል።ያኔም-አሁንም ሰሚ የለም።ለካርቱም ስደተኞች ጩኸት መልስ ለመፈለግ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን (UNHCR) ባለስልጣናትን ለማነጋገር ሞከርን።ካርቱም ያሉት ለጄኔቭ፤ ጄኔቭ ያሉት ለካርቱም ባልደረቦቻቸዉ ሲያቀባበሉን ሰወስት ቀን ፈጀ። መልስ የለም።

ስደተኛዉ ግን-መልስ አለዉ።ችግር ፈጣሪዉ ማሆነና-የሚል መልስ።

ይላሉ የካርቱሙ ስደተኛ።ከሰነዓም ተመሳሳይ ነዉ-የሚሰማዉ።የሰነዓዉ ስደተኛ የፍርድ ቤት ገጠመኙን ይቀጥልልን።

የኢትዮጵያዉኑን ስደተኞች ጩኽት ከናይሮቢ፤ ካርቱም ሰነዓ ሠምተን ሳናበቃ የደቡብ አፍሪቃዉ አድማጫችን አጭር መልዕክት ከእጃችን ደረሰች።«ጁሐንስበርግ ዉስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ ተገደለ።» ትላለች-መልዕክቷ።

ከኬንያ እስከ ሞዛምክ ጠረፍ ያለዉን መከራ አይችሉ- ችለዉ አለያም አምልጠዉ ደቡብ አፍሪቃ የገቡ ኢትዮጵያዉያን የፊጥኝ እየታሰሩ ሱቃቸዉ ተመዝብሯል። ባል ታርዶ-ሚስት ተደፍራለች።እናት ከነልጇ ተረሽናለች።ሁሉንም ሰማን።እና መልዕክቱም ግድያዉም አዲስ አይደለም።ለሳምቱ አዲሱ ነገር ከናይሮቢ የሰማነዉ ነበር።

ኬንያ የሶማሌዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን መዉጋት ከጀመረች ከ2011 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ ቆጣጠር ነዉ) የአሸባብ የቦብ የጥቃት ኢላማ ሆናለች።የፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ መንግሥት ጥቃቱን ለመበቀል መፍትሔ ካለዉ አንዱ ኬንያ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞችን ማሰር፤ከከተማ ዉጪ ማጎር እና ማጋዝ ነዉ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሑዩማን ራይትስ ዋች አጥብቆ ባወገዘዉ የኬንያ መንግሥት እርምጃ የሚሰቃይ-የሚጋዘዉ የሶማሊያ ስደተኛ ብቻ አይደለም።ለአካለ-መጠን ያልደረሰ ኢትዮጵያዊ ጭምር እንጂ።

«ለምሳሌ ወደ ሞቃዲሾ የተጋዘ አንድ ኢትዮጳዊ ልጅ አነጋግረናል።ልጁ በሕይወቱ ጨርሶ ሶማሊያ ዉስጥ እንዳልነበረ ግልፅ ነዉ።ሥለዚሕ እርምጃዉ (ማጋዙ) በጣም አሳሳቢ ነዉ።»

ግፍ-ሥቃይ መከራ ስንት ዓይነት ነዉ? ክብደት ቅለቱስ የሚለካዉ እንዴት ነዉ ?የየመኑ ስደተኛ እንደሚለዉ በኢትዮጵያዊዉ ስደተኛ ላይ የሚፈፀመዉን ግፍ-ለመዘርዘር ቋንቋ ራሱ አቅመ ቢስ ነዉ።

የመን በገቡና በሚገቡ ኢትዮጵያዉን ላይ ሥለሚፈፀመዉ ግፍ በዝርዝር ያተተዉ ሑዩማን ራይትስ ዋች እንደሚለዉ ስደተኛዉን የሚያሰቃዩት የየመን ሹማምንታት ጭምር ናቸዉ።

ሰደተኛዉ ከባሕር እንደወረደ አድፍጠዉ የሚጠብቁ አጋቾች ያፍኑታል።ከዚያ በየሥፍራዉ ባዘጋጁት ማሰሪያ ቦታ ያጉሩታል።ማጎሪያዎቹ መግደያ፤ መግረፊያ፤ መድፈሪያ ገንዘብ ማስከፈያ፤ማስራቢያም ጭምር ናቸዉ።

የሑዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ቤልኪስ ዊል እንደሚሉት ታጋቹ ስደተኛ ለየዘመድ ወዳጆቹ ሥልክ እየደወለ ላጋቾቹ እንዲከፍል ከሚያስልከዉ ገንዘብ የሚቀራመቱት፤ አጋቾቹ ብቻ አይደሉም።የፀጥታ አስከባሪዎች ሹማምንት ጭምር እንጂ።

«(ጥናቱ)የመንግሥት ባለሥልጣናት በቀጥታ ከሥደተኞቹ አሸጋጋሪዎች ጋር እንዴት እንደሚሠሩ ያተኮረ ነዉ።ሥደተኞቹን የሚያሸጋግሩት የማጎሪያና የማሰቃያ ሥፍራዎችን በግልፅ እንዲያደራጁ፤ ሥደተኞቹን እንዲገርፉና (አስገድደዉ) ገንዘብ እንዲያስከፍሉ ባለሥልጣናቱ ከለላ ይሰጧቸዋል።ከለላ መስጠት ብቻ ሳይሆን የጦርና የፀጥታ ኃይላት ሥደተኞችን ከየመንገዱ እየያዙ ለሚያሰቃዩት ሰዎች ይሸጧቸዋል።»

እሷ ወጣት ናት።ቢልላት እንደ እድሜ አቻዎቿ የወደፊት ሕይወቷን ለማሻሻል፤ ወላጅ አሳዳጊዎችዋን ለመጦር ማቀድ፤ መማር መጣር፤ ደግሞ በመሐሉ ማጌጥ፤ ማማር የልጅ አገረድ ወጓ በሆነ ነበር።አልታደለችም።ተታላለች። ወይም ታግታለች፤ ወይም ተሸጣለች።ባንድ ቃል አልቻለችም። ከስደተኛም-አቅም ለመሰደድ ክብር አልበቃችም።ግፍ-ነዉ እጣዋ።መደፈር፤ መጨነቅ፤አባቱ ከማይታወቅ ሕፃን ጋር መቆራመድ ነዉ-ትርፏ።እንደምትለዉ ሞትም እራቃት።ላሁኑ እንባ ነዉ-ጉልበቷ።

ኢትዮጵያዊዉ ወጣት በገፍ የመሰደዱ ሰበብ- ምክንያት ኬንያዊቱ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች ዋንጋሪ ማታይ እንዳሉት «ሳሩ ይበልጥ አረንዴ ሥለሚመስለዉ» ብቻ አይደለም።የሑዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ዋና ዋና የሚሏቸዉ ሌሎች ሰወስት ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ።

«እንዱ፤-እነዚሕ ሰዎች ሐገራቸዉ ዉስጥ ያለባቸዉ የምጣኔ ሐብት ችግር ሲበዛ ከባድ ነዉ።ለወላጆቻቸዉ ገንዘብ ለመላክ ሲሉ ሊያጋጥማቸዉ የሚችለዉን አደጋ ሁሉ ለመጋፈጥ ቆርጠዉ ይሰደዳሉ።ሁለተኛዉ፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያጠኑ የሑይማን ራይትስ ዋች ባልደረቦች በተደጋጋሚ እንዳሉት በተወሰኑ አናሳ ጎሳ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመዉን በደል ሽሽት ነዉ።ይሕን አደገኛ ጉዞ የሚያደርጉት በአብዛኛዉ የተወሰኑ ጎሳ አባላት መሆናቸዉ ሐገራቸዉ የሚፈፀምባቸዉን በደል ይናገራል።ይሁንና ሌላዉ ምክንያት በግልፅም እንደሚታወቀዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥለ ችግሩ በቂ መረጃ የለም።ያነጋገርናቸዉ ሥደተኞች በሙሉ እንዲሕ አይነት መከራ ሊገጥማቸዉ እንደሚችል አናዉቅም ነዉ ያሉት።»

የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን-በጀት ለማስቆረጥ ሥደተኞችን ይቆጥራል።ስሞታቸዉን ለመስማት ይደበቃል። ንጉስ አበደላሕ የሶሪያ ሕዝብን የሚፈጅ ፤ የሚያሰድድ ፤የሚያፈናቅለዉን ጦርነት ለማማጋጋም መባተል ከጀመሩ ሰወስተኛ ዓመታቸዉ።ፕሬዝዳንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ በጎሳ ግጭት፤ በአሸባሪዎች ጥቃት፤ በተገንጣዮች አመፅ የተሽመደመደችዉን የመንን በሁለት እግሯ ማቆም ተስኗቸዉ ግራ-ቀኝ ይላጋሉ።

ፕሬዝዳናት ኡኹሩ ኬንያታ ከዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሙግት ያዳናቸዉን ሥልጣን በቅጡ ሳይደላደሉበት አሸባብን ጥሎባቸዉ-ደፋ ቀና እያሉ ነዉ።ፕሬዝዳንት ዑመር አል-በሽር ከዳርፉር ግጭት፤ ከደቡብ ሱዳን ጦርነት፤ ከምዕራባዉያን ጫና የተረፋቸዉን ጊዜ የኢትዮጵያና የኤርትራን አቋም ርምጃ በጥንቃቄ ለመርመር ነዉ የሚያዉሉት።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሐብት ዕድገት፤ የሠላም ፍትሗን ስፍነት ከመዘርዘር የሚተርፍ ጊዜ ካላቸዉ፤ አድም ደቡብ ሱዳኖችን ለመሸምገል፤ ሁለትም ካይሮዎችን ለመቃኛት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ የኢትዮጵያዊዉን ወጣት ሥደተኛ ሞት፤ሥቃይ፤ ሠቆቃ-ማን መቼ እንዴት ይስማ?

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

Audios and videos on the topic