የኢትዮጵያዉያን ሮሮ በሱዳን እና የተገኘዉ መልስ | ኢትዮጵያ | DW | 23.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያዉያን ሮሮ በሱዳን እና የተገኘዉ መልስ

«እዉነት ነዉ መታወቅያዉን በተመለከተ የዛሬ ዓመት ነበር የሱዳን መንግሥት የወሰነዉ። 2030 የሱዳን ፓዉንድ ለመታወቅያ እንዲከፈል በሚል ነበር የወሰነዉ። ነገር ግን ከዜጎቻችን አቅም አንፃር ከባድ መሆኑ ቢታወቅም የሐገሪቱን ሕግ አክብሮ መኖር ግዴታ ስለሆነ ያንን አቅዋም ለህዝቡ ገልፀን፤ አሁን ሕዝቡ መታወቅያ እያወጣ ነዉ።» 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:33

በካርቱም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መልስ

ሱዳን ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን  «ለመታወቂያ ክፈሉ የምንባለዉ የገንዘብ መጠን ናረ መታወቂያ ስናወጣ በሱዳን ፖሊሶች እየተቀደደብን እንደገና አዉጡ እንባላለን፤ አልያም እየታፈስን እንታሰራለን»  ሲሉ ለዶቼ ቬለ  ቅሬታቸዉን እየገለፁ ነዉ። ኻርቱም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ የዛሬ ዓመት በሱዳን መንግሥት የተደነገዉን የመታወቂያ ማዉጫ ገንዘብ መጠን ለማስቀነስ ጥረት ቢያደርግም ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ገልጿል። አዜብ ታደሰ  ካርቱም ሱዳን በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያስፖራ ክፍል ኃላፊን አነጋግረናል።

ዶቼ ቬለዎች ችግራችንን ለዓለም አሰሙልን በማለት በየጊዜዉ ከሱዳን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አቤቱታቸውን የያዘ የደብዳቤ እንዲሁም የድምፅ መልክት ይደርሰናል።

«ምን ብዬ መናገር እንዳለብኝ ባላዉቅም፤ በሱዳን ኑሮ ከአቅማችን በላይ ነዉ የሆነዉ። የኑሮ ዉድነቱም በጣም እየከፋ ነዉ። እንደገና ከመታወቅያዉ ዋጋ ንረት የባሰ የእስራቱ መጠኑ፤ ከወንጀለኛ ያልተናነሰ ቅጣት ነዉ እየደረሰብን ያለዉ። የዛሬ ዓመት እኔ ከስድስት ሽህ ብር ያላነሰ ቅጣት ተቀጥቼ ስድስት ወር ቅጣት ኖሮብኝ ነዉ ከእስር የወጣሁት። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ከመታወቅያ ቅጣቱ ይልቅ ከስምንት ሽህ ብር ያላነሰ ቅጣት ነዉ ነዉ እየቀጡን ያለዉ። ከአቅማችን በላይ ነዉ የሆነብን። ይህን ጉዳይ የዓለም መገናኛ ብዙኃን እንዲያዉቀዉ ነዉ» ይላሉ የዶቼ ቬለዉ አድማጭ ። 

ካርቱም በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤንባሲ የዲያስፖራ ክፍል ኃላፊ አቶ አምሳሉ ሃቴ እንደሚሉት በኢትዮጵያዉያኑ የሚገለፀዉ ችግር እዉነት ነዉ።  

«እዉነት ነዉ መታወቅያዉን በተመለከተ የዛሬ ዓመት ነበር የሱዳን መንግሥት የወሰነዉ። 2030 የሱዳን ፓዉንድ ለመታወቅያ እንዲከፈል በሚል ነበር የወሰነዉ። ነገር ግን ከዜጎቻችን አቅም አንፃር ከባድ መሆኑን አምነንበት ለአንድ ዓመት ያህል ከሱዳን መንግሥት ጋር ስንከራከር ነዉ የቆየነዉ። በዚህ ዓመት መጨረሻ ግን እንደማይቀነስ ለኛ አሳዉቀዉናል። አምነንበት አይደለም።  ለዜጎቻችን ይህ ከአቅማቸዉ በላይ ነዉ። ቢሆንም ግን የሐገሪቱን ሕግ አክብሮ መኖር ግዴታ ስለሆነ ያንን አቅዋም ለህዝቡ ገልፀን፤ አሁን ሕዝቡ መታወቅያ እያወጣ ነዉ።» 

ለኢትዮጵያዉያኑ ከሱዳን መንግሥት የሚሰጠዉ መታወቅያ በሐገሪቱ ስለመኖራቸዉ ማረጋገጫ እንጂ የሥራ ፈቃድ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ አምሳሉ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸዉ ማረጋገጫ ለመስጠት አይተባበረንም የተባለዉን ወቀሳ ግን አስተባብለዋል።

 

«መታወቅያዉን ለማዉጣት ፓስፖርት አያስፈልግም። ከዚህ ቀደም ኤምባሲዉ ተነጋግሮ ጊዜያዊ መታወቅያ ከኢሚግሪሽን ያወጡት መታወቅያ አለ። በዚያ መታወቅያ መሰረት የመኖርያ መታወቅያዉን ማዉጣት ይቻላል። ሌሎችም ፓስፖርት የሌላቸዉ ሰዎች ዜግነታቸዉን ገልፀዉ መታወቅያዉን መዉሰድ ይችላሉ። በዚያ በኩል ብዙም ችግር የለዉም። ከዝያ ዉጭ ግን ብዙ ዜጎቻችን ወደ ሱዳን በሚገቡበት ጊዜ አንዳንዶቹ ፓስፖርት ሳይኖራቸዉ ነዉ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡት። ሌሎች በሕጋዊ መንገድ የገቡም ቢሆኑ ፓስፖርታቸዉ ቀኑ ሳይታደስ ያለፈበት ነዉ። ስለዚህ ወደ ሃገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች በቆንስላ ክፍላችን በኩል ኢትዮጵያዊ መሆናቸዉ የተለያየ ማጣራት ከተደረገ በኋላ እንዲመለሱ ይደረጋል።»      

የሱዳን ፖሊሶች መታወቅያችንን ይሰብሩንናል ማለታቸዉ ይቀድዱብናል ለማለት ነዉ፤ እንደገናም ለማዉጣት ተገዳናል ይላሉ። በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ኤንባሲ የሚረዳዉ ነገር አለ? 

«እንደዚህ አይነት ክስተቶች የሉም ማለት አይቻልም። ደግሞም የሉም ማለት አይቻልም። አልፎ አልፎ መታወቅያ የመስበር የመቀማትና የመደበቅ ነገር ይኖራል። ነገር ግን የኛ ዜጎች በሱዳን ብዙ ናቸዉ። እጅግ በጣም ብዙ ከዚያ አንፃር ሲታይ ግን በጣም በጣም ጥቂት ነዉ ብለን መናገር እንችላለን። የተወሰኑ አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ትንንሽ አጋጣሚዎችም ቢሆኑ በኤንባሲያችን በኩል ለማስወገድ ቀን እና ለሊት ነዉ እየሰራን ያለነዉ። አልፎ አልፎም እንደዚህ የሚያደርጉ ፖሊሶችን ካገኘን ከሱዳን መንግሥት ጋር ተባብረን እርምጃ እንዲወሰድባቸዉ ያደረግንበት አጋጣሚም አለ። በአሁኑ ጊዜ እየከፋ የመጣዉ የሱዳን መንግሥት ፖሊሲም ሳይሆን ከዋጋ ግሽበት ጋርም ተያይዞ ኑሮም ትንሽ መወደዱ ነዉ። ዜጎቻችን ደሞዛቸዉ ጥቂት በመሆኑ ችግር ላይ ወድቀዋል። እሱ ነዉ የኢትዮጵያዉያኑን ሮሮ እያሰፋ የመጣዉ እንጂ ከሱዳን መንግሥት በኩል ያለዉ ይሄን ያህል የከፋ ነዉ ብለን ማለት አንችልም።»      

በአጠቃላይ በሱዳን ስንት ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ? ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ለሚፈልጉት ኢትዮጵያዉያንስ በእናንተ በኩል የሚደረግ ርዳታ አለ?

« በሱዳን የሚኖሩትን ኢትዮጵያዉያን ቁጥር መገመት ትንሽ ከበድ ይላል። ሱዳን የመቆያ ሳትሆን ስደተኞች የሚተላለፉባት ሐገር ስለሆነች በጣም ብዙ ዜጎች ወደ ሐገሪቱ ይገባሉ ይወጣሉ። ኢትዮጵያዉያኑ እንዳይገቡ ለማስቆም ሞክረን ነበር አልቻልንም። በየጊዜዉ ሰዎች ይወጣሉ። ወደ ሊቢያ የሚሄድ አለ። ወደ ሐገሩም የሚመለስም አለ። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የሱዳን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደነገረን ከሆነ በሱዳን ሐገር የሚኖሩና የተመዘገቡ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር 350 ሺ ገደማ ነዉ። ከዚህ ዉጭ ግን ሲገመት የሕዝብ ወደ ሱዳን መግባት መዉጣቱም እያለ ወደ 500 ሺህ በላይ ብለን መዉሰድ እንችላለን። ይህን ያህል ብለን ግን በትክክለኛ ቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም»

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic