የኢትዮጵያዉያኑ አትሌቶች ድል | ስፖርት | DW | 19.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የኢትዮጵያዉያኑ አትሌቶች ድል

ሞስኮ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለዉ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዉያኑ አትሌቶች ድል ቀንቶአቸዋል።

ሞስኮ ላይ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በተካሄደው የወንዶች ማራቶን ሩጫ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ለጥቂት የወርቅ ሜዳሊያ አመለጣቸው። በውድድሩ ያለፈው የለንደን ኦሎምፒክ ማራቶን አሸናፊ የኡጋንዳው የወህኒቤት ዘብ ባልደረባ ስቴፈን ኪፕሮቲች ባለድል ሆኗል። የኢትዮጵያ አትሌቶችም ብርቱ ጥንካሬ በማሳየት ከሁለት እስከ አራት ተከታትለው ከግባቸው ሲደርሱ ሌሊሣ ደሢሣ የብርና ታደሰ ቶላም የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። የ 2008 የቤይጂንግ ኦሎምፒክና የተከታዩ ዓመት የዓለም ሻምፒዮና የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ጸጋዬ ከበደ ደግሞ ሩጫውን በአራተኝነት ፈጽሟል። አሁን በቅርቡ ደግሞ በሴቶች አምስት ሺህ ሜትር ሩጫ መሠረት ደፋር አሸናፊ ሆናለች። አልማዝ አያናም ሩጫውን በሶስተኝነት ፈጽማለች።

ባሳለፍነዉ ሳምንት የጀመረዉ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞስኮ ላይ በተደረገ የሴቶች የማራቶን ዉድድር ኬንያዊትዋ ኤድና ኪፕላገርት በአንደኝነት መጨረስዋ ይታወሳል። የ33 ዓመትዋ ኬንያዊትን በመከተል ጣልያናዊትዋ ሯጭ በሁለተኛነት፤ ጃፓናዊትዋ በሶስተኛነት ተከታትለዉ ገብተዋል። በሴቶች ማራቶን ዉድድር ኢትዮጵያዉያቱ ድል ሳይቀናቸዉ ቀርቶአል። ረዘም ላለ ኬሎ ሜትሮች በሶስተኛነት ስትሮጥ የነበረችዉ መሰለች መልካሙ ዉድድሩን ሳትጨርስ መዉጣትዋ ይታወሳል። በወንዶች የ800 ሜትር ዉድድር መሀመድ አማን በአንደኛነት ማጠናቀቁ ይታዉቃል። ባለፈዉ ሳምንት በጉጉት የተጠበቀዉ የወንዶች 10 ሺ ሜትር ሩጫ ዉድድር፤ ሶማልያዊዉ የብሪታንያ ዜጋ ሞህ ፋራህ በአንደኝነት፤ ኢትዮጵያዊዉ ኢብራሂም ጄላን በሁለተኝነት፤ ኬኒያዊዉ ሯጭ በ3 ተኝነት አጠናቀዋል። ዘንድሮ ሞስኮ የምታስተናግደዉ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ 206 ዓለም ሀገራት የተሰባሰቡ ስፖርተኞች ለሜዳልያ ይፎካከራሉ።

አዜብ ታደሰ

መስፍን መኮንን

Audios and videos on the topic