የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማዳን የሚጥሩ ኢትዮጵያዊ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማዳን የሚጥሩ ኢትዮጵያዊ

በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተዘረፉም ሆነ እየተገዙ ከሀገር የሚወጡት የኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች የውጭ ዓለም ቤተ መዘክር ማድመቂያ መሆናቸው እንዳስቆጨ ነው። እነዚህ ምትክ የሌላቸው ቅርሶች በግለሰቦችም እጅ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ቅርሶች በመሰብሰብ፣ ከብክነት ለማዳንና እንዳሉ ለመጠበቅ በግል ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦች አሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:31

የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለአደጋ ተጋልጠዋል

ከአንድ ወር በፊት ለንደን ብሪታንያ ውስጥ በአንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ የደረሰው እና ከ80 በላይ ሰዎችን ህይወት እንዲሁም ብዙ ንብረት ያጠፋው ከባድ የእሳት አደጋ ልዩ ልዩ መዘዞችን አስከትሏል።ከህንጻው ቃጠሎ በኋላ ተመሳሳይ አደጋ ያሰጋቸዋል የተባሉ ሌሎች 5 ሰማይ ጠቀስ የመኖሪያ ህንጻዎች ፣ 4ሺህ የሚገመት ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲባል ከህንጻዎቹ በአስቸኳይ እንዲለቁ ተደርገዋል። ኢትዮጵያውያን የዛሬ 34 ቀኑ የእሳት አደጋ ሰላባ እንደሆኑት ሁሉ በዚህ ድንገተኛ እርምጃም የተቸገሩ አልጠፉም።  ከመካከላቸው አንዱ ከነዚህ ህንጻዎች በአንዱ ነዋሪ የሆኑት እና በቤታቸውም በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶችን አሰባስበው ያስቀመጡት አቶ አለባቸው ደሳለኝ ይገኙበታል።

አቶ አለባቸው ደሳለኝ በሞያቸው የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ ናቸው። ከምንም በላይ የሚያረካቸው ግን ከዚሁ ሞያቸው ጎን ለጎን ከዛሬ 20 ዓመት አንስቶ የሚያካሂዱት የኢትዮጵያን ቅርሶች የማሰባሰብ ሥራ ነው። ከዛሬ 23 ዓመት አንስቶ በሚኖሩባት በለንደን ቅርሶችን ማሰባሰብ የጀመሩትም በቁጭት መሆኑን ይናገራሉ። አቶ አለባቸው ለበርካታ ዓመታት ያሰባሰቧቸውን እነዚህን ብዙ ገንዘብ ያወጡባቸውን እና ከመካከላቸው ምትክ ሊገኝላቸው የማይችሉ ቅርሶችን በዚሁ ህንጻ ውስጥ ጥለው ለመውጣት ተገደዋል። 

አቶ አለባቸውም ይሁኑ ሌሎች ከየህንጻዎቹ ለጊዜው እንዲወጡ የተደረጉት ነዋሪዎች መቼ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ አያውቁም። ይህ ግን አቶ አለባቸውን ብዙም አያስጨንቃቸውም። ከዚያ ይልቅ ትተዋቸው ከመሄድ ውጭ ለጊዜው ሌላ አማራጭ ያላገኙላቸው ቅርሶች ደህንነት እና ጥበቃ ነው የሚያሳስባቸው። እስከዛሬ በተቻላቸው ሁሉ ሲንከባከቧቸው ቢቆዩም እንደ እስካሁኑ መቀጠል መቻላቸውን ይጠራጠራሉ።

የፎቶግራፍ ባለሙያው የሰበሰቧቸውን ቅርሶች ከጎበኙት መካከል በቅርቡ በሞት የተለዩት እንግሊዛዊው ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ጨምሮ የታሪክ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና የፊልም ባለሞያዎች ይገኙበታል። ከዛሬ 23 ዓመት አንስቶ ለንደን የሚኖሩት አቶ አለባቸው የኢትዮጵያ ቅርሶችን ማሰባሰብ ከጀመሩ 20 ዓመታት አልፈዋል። ቅርሶቹን ከሚያሰባስቡባቸው ዘዴዎች አንዱ በሚኖሩበት በብሪታንያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም የኢትዮጵያ ቅርሶች ለሽያጭ በሚቀርቡባቸው የተለያዩ ጨረታዎች ላይ እየተሳተፉ በመግዛት ነው። በዚህ መንገድ በመኖሪያ ቤታቸው ካሰባሰቧቸው በርካታ ቅርሶች መካከል በርካታ  የኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሰነዶች ሰነዶች ይገኙበታል ።

ቅርሶች በኢትዮጵያ የደረሰባቸው ጥፋት ለሁሉም ኢትዮጵያ ግልጽ ነው ይላሉ አቶ አለባቸው። ስለዚህ እርሳቸው እና ሌሎች ግለሰቦች ያሰባሰቧቸውን ከጥፋት የተረፉ እና አደጋ ላይ የሚገኙት ቅርሶችን ለማዳን እንመካከር እንረባረብ ሲሉ ለቅርስ ተቆርቋሪ ወገኖች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ አለባቸው ያሰባሰቧቸው ቅርሶች ለአደጋ መጋለጥ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ማሳሰቡ አልቀረም።  ችግሩን በውል ከተረዱት ውስጥ ቅርሶቹን ቤታቸው ወስደው ለማስቀመጥ ፈቃዳቸውን የገለጹላቸው እንዴት እንርዳ ብለው የጠየቋቸውም አሉ። ጉዳዩ ከሚያስጨንቃቸው መካከል ቅርሶቹ በሚገኙበት በብሪታንያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ አባላትም ይገኙበታል ። አቶ ዮስያስ ታደሰ በብሪታንያ የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌደሬሽን  ጸሀፊ መፍትሄው በጋራ ሊፈለግ ይገባል ይላሉ። 

 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 
 

Audios and videos on the topic