የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር በጀርመን

የኢትዮዽያ ጥናት በጀርመን የረጅም ዓመታት ታሪክ ያለው ነው። በተለያዩ ጀርመናውያን ተመራማሪዎች ከ17ኛው ከፍለ ዘመን ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የኢትዮዽያ ጥናት ሳይቋረጥ እስከ ዛሬ ዘልቋል። በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል።

default

ለረጅም ዘመናት የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር እየተካሄደበት ያለው የሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ

ኢትዮዽያ ባህሏን ቋንቋዎቿን፤ ታሪኳን በማጥናት ረገድ የአውሮፓ ተመራማሪዎች ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በተለይም የጀርመን ተመራማሪዎች በተለያዩ ዘመናት ወደ ኢትዮዽያ በማምራት ጥንታዊ የሆነውን ግዕዝን ጨምሮ በአማርኛ፤ በትግርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር አካሂደዋል። ከ17ኛው ከፍለ ዘመን ጀምሮ ጀርመንያውያን ተመራማሪዎች በኢትዮዽያ ጥናት ላይ ያደረጉት የምርምር ስራ የኢትዮዽያን ባህል፤ ቋንቋና ታሪክ ለአለም በተለይም ለአውሮፓውያን በማስተዋወቅ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ በተለያዩ የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮዽያ ቋንቋዎች የትምህርት ክፍል ተቋቁሞላቸው አውሮፓውያን ተማሪዎችን እያስተማሩ ይገኛሉ። በዛሬው አውሮፓና ጀርመን በተሰኘው ዝግጅት የኢትዮዽያ ጥናት በጀርመን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፤ በተለይም ጥናቱ በተጠናከረ ሁኔታ በመሰጠት ላይ ባለው የሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ምን እንደሚመስል፤ ለመቃኘት ይሞክራል። መሳይ መኮንን ።

የኢትዮዽያ ጥናት በጀርመን ታሪካዊ መነሻው 17ኛው ከፍለ ዘመን ላይ ያርፋል። በዚያን ዘመን የነበሩት ስመጥሩው ጀርመናዊ ተመራማሪ ሂዮብ ሉዶልፍ አባ ጎርጎርዮስ ከሚባሉ መነኩሴ ግዕዝንና አማርኛን እንዲሁም የኢትዮዽያን ታሪክ ይማራል። ሉዶልፍ ከአባ ጎርጎሪዮስ ያገኘው ትምህርት ስለኢትዮዽያ ሰፊ የምርምር ስራ ለማድረግ ፍላጎት ያሳድርበትና ወደ አውሮፓ ሙሉ ጊዜውን በኢትዮዽያ ጥናት ላይ ማድረግ ይጀምራል። በሁምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ተቋም የኢትዮድያ ጥናት ክፍል ሃላፊ ጣሊያናዊው ፕሮፌሰር አሌክሳንድሮ ባውዚ እንደሚሉት ሂዮብ ሉዶልፍ በአውሮፓ የኢትዮዽያ ጥናት ፈር ቀዳጅ ነው።

«ጀርመን የኢትዮዽያ ጥናት በአውሮፓ እንዲጀመር ልዩ የሆነ ሚና ተጫውታለች። ከ17ኛው ከፍለዘመን ጀምሮ ጀርመን የኢትዮዽያ ጥናት በአውሮፓ እንዲፈጠር አድርጋ በመሪነት ቆይታለች። በዚያው ዘመን ሂዮብ ሉዶልፍ የተባለው ጀርመናዊ ምሁር የኢትዮዽያ ጥናት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ መሰረቱን ጥሏል። በአውሮፓ በተለይም በሮም አከባቢ ካለው አነስተኛ የኢትዮዽያ ማህበረሰብ ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር የግእዝንና የአማርኛ ቋንቋዎችን ይማራል። ሉዶልፍ በእነዚህ ቋንቋዎች መዝገበ ቃላትንና ሰዋሰው አዘጋጅቷል። ከዚህ በተጨማሪ በ17ኛው ከፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሉዶልፍ ሳይንሳዊ የሆነ የኢትዮዽያን ታሪክ በዘመናዊ መልክ በማዘጋጀት ለኢትዮዽያ ጥናት ጉልህ ድርሻ አበርክቷል። እናም ጀርመን በዓለም ዙሪያ የኢትዮዽያ ጥናት መስራች በመሆኗ ትኮራለች።»

በ17ኛው ክፍለዘመን በአባ ጎርጎሪዎስ አስተማሪነት ሂዮብ ሉዶልፍ የጀመረው የኢትዮዽያ ጥናት በሌሎች ጀርመናውያን ተመራማሪዎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የእስያና የአፍሪካ ጥናት ተቋም ውስጥ የአፍሪካና የኢትዮዽያ ጥናቶች ትምህርት ክፍል የአማርኛ ቋንቋና የአፍሪካ ፎክሎር እንዲሁም ስነቃል መምህር ዶክተር ጌቴ ገላዬ ከሂዮብ ሉዶልፍ በኋላ የነበረውን የኢትዮዽያ ጥናት ታሪካዊ ሂደት እንዲህ ይገልጻሉ።

ድምጽ/ ዶክተር ጌቴ ገላዬ

ኦይጎን ሚትቮህ የሚባሉ የምስራቃዊ ቋንቋዎች ፕሮፌሰርና አለቃ ታዬ ገብረማርያም የሚባሉ ኢትዮዽያዊ ከ1905 እስክ 1907 እ.ኤ.አ ግዕዝንና አማርኛን በበርሊን ዩኒቨርሲቲ ማስተማራቸው የኢትዮዽያ ጥናት በጀርመን ታሪኩ ሲወሳ የሚጠቀስ ነው። አለቃ ታዬ ገብረማርያም በጀርመን ሀገር የመጀመሪያው ኢትዮዽያዊ መምህር በሚል በታሪክ ሰፍረዋል። ፕሮፌሰር ኦይጎን ሚትቮህ ከአለቃ ታዬ ጋር በመሆን ስለአማርኛ ልዩ ልዩ ግጥሞች፤ ስለባህል ስለግዕዝ ስለሥነፅሁፍ የተለያዩ የጥናትና የምርምር ስራዎችን አድርገዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የኢትዮዽያ ጥናት በተለያዩ የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ክፍል ተቋቁሞለት በተጠናከረ ሁኔታ ይሰጥ ጀመር። በበርሊን፤ በማይንስ፤ በቲዩቢንገን፤ በሀምቡርግ፤ በፍራንክፈርት የኢትዮዽያ ቋንቋዎች ይሰጡ እንደነበር ዶክተር ጌቴ ገላዬ ገልጸዋል። ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በሌሎቹ ከተሞች የኢትዮዽያ ጥናት ሥራ እየተዳከመ ቢመጣም በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጥንካሬንውን እንደያዘ እስከአሁን ሊቀጥል ችሏል።ዶክተር ጌቴ በሀምቡርግ የኢትዮዽያ ጥናት እንዴት እንደተጀመረና አሁን ያለበትን ደረጃ ሲገልጹ

ድምጽ/ ዶክተር ጌቴ

በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቷቋም የኢትዮዽያ ጥናት ክፍል ሃላፊ ፕሮፌሰር አሌክሳንድሮ ባውዚም በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮዽያ ጥናት ክፍል በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ይላሉ።

«የኢትዮዽያ ጥናት በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጠንካራ ነው። ኢትዮዽያ ላይ ትኩረት በመስጠት እንቅስቃሴ የሚያደርግ የትምህርት ክፍል ስላለ በጥሩ ሁኔታ ምርምሮችና ጥናቶች ይደረጋሉ። በመሆኑም መደበኛ በሆነ መልኩ የአማርኛና የግዕዝ ትምህርቶችን ለተማሪዎች እንሰጣለን። ከእነዚህ በተጨማሪም አልፎ አልፎ ትግርኛና ኦሮምኛ እንዲሁም ሌሎች ቋንቋዎችንም እናስተምራለን። በርካታ ፕሮጀክቶችንም እናካሂዳለን። ከኢትዮዽያ ጥናቶች ጋር የተያያዙ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርምር ስራዎችን በዓለም ዙሪያ እናሰራጫለን።»

በእርግጥ የኢትዮዽያ ጥናት በጀርመን እንደአነሳሱ ተጠክሮ አልቀጠለም። በአንዳንድ የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች ከነጭራሹ የኢትዮዽያ ቋንቋዎችን ማስተማር እስከመቋረጥ ደርሷል። በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ለ6 ዓመታት ያህል የኢትዮዽያ ጥናት ክፍል ሃላፊ ሳይመደብ በመዝለቁ የምርምር ስራዎች ያልተካሄዱ ሲሆን እንቅስቃሴው በአጠቃላይ ተዳክሞ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው አንዳንድ ኢትዮዽያውያንና ጀርመናውያን ምሁራን ታዲያ የተዳከመው የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር ስራ እንዲያንሰራራ መጎትጎት ከጀመሩ ቆይተዋል። በተለይም ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተ ከሆለት ዓመት በፊት በአንድ የጀርመን ጋዜጣ ላይ አቤቱታ አቅርበው ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበው ነበር። በእርግጥ በበርሊን ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠውን የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር ለማስጀመር ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የእስያና የአፍሪካ ጥናት ተቋም ውስጥ የአፍሪካና የኢትዮዽያ ጥናቶች ትምህርት ክፍል የአማርኛ ቋንቋና የአፍሪካ ፎክሎር እንዲሁም ስነቃል መምህር ዶክተር ጌቴ ገላዬ በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ችግሩ መልክ ይዟል ይላሉ።

ድምጽ/ ዶክተር ጌቴ

ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ተቋም የኢትዮዽያው ክፍል ሃላፊ ሆነው የተመደቡት ጣሊያናዊው ፕሮፌሰር አሌክሳንድሮ ባውዚም የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር በተቋማቸው እየጠናከረ እንደመጣ ይገልጻሉ።

« በአሁኑ ጊዜ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ የተሰኘ ፕሮጀክት አለን። ይህ ፕሮጀክት ትልቁ ስራችን ሲሆን ከ500 በላይ ጸሃፊያን እየተሳተፉበት ይገኛሉ። ከ5000 በላይ ጽሁፎች ተሰብስበው በ5 ጥራዞች የሚቀርቡበት ስራ ነው። ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ ለምርምር ስራዎች መነሻ መረጃዎችን የሚያቀርብና ኢትዮዽያን በተመለከተ ማጣቀሻ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል። ኢትዮፒካ የተሰኘ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት ሳይንሳዊ የሆነ አነስተኛ መጽሄትም አለን።»

አድማጮች የዕለቱ አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ያዳመጣችሁትን ይመስላል። መሳይ መኮንን ነበርኩ። ጤና ይስጥልኝ።

መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ