የኢቦላ ወረርሽኝ አንደኛ አመት | አፍሪቃ | DW | 24.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኢቦላ ወረርሽኝ አንደኛ አመት

ጊኒ፤ላይቤሪያ እና ሴራሊዮንን ያመሰው የኢቦላ ተኅዋሲ ወረርሽኝ ከተከሰተ አንድ አመት ሞላው። ወረርሽኙን በመግታት ረገድ ስጋቱ ያረበበባቸው ሴኔጋል፤ናይጄሪያ እና ማሊ ስኬታማ የመሆናቸውን ያህል ላይቤሪያ ከኢቦላ ተኅህዋሲ ነጻ ለመባል የምታደርገው ጥረት ተደናቅፏል።

አገሪቱ በየካቲት 26 ቀን 2007ዓ.ም. የመጨረሸዋን ህመምተኛከህመም ተፈውሰዋል በማለት ወደ ቤታቸው ከሸኘች በኋላ ባለፈው ሳምንት አዲስ የኢቦላ ህመምተኛ መገኘታቸው ተሰምቷል።

በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ኮንጎ በተባለ መንደር በእለተ እሁድ ማለዳ ህጻናት እግር ኳስ ይጫወታሉ። የአስር አመቱ ሮቢንሆ ድዌህ የኢቦላ ወረርሽኝ በመቀነሱ ደስተኛ መሆን ይናገራል። የስምንት አመቱ ሮሚዎ ሆልምስ በመኖሪያ ከተማው ሞኖሮቪያ የኢቦላ ተኅህዋሲ ጥላውን ባጠላበት ወቅት ብዙ ሰዎች በሆስፒታል አልጋ ላይ እንደነበሩ ያስታውሳል። እናም እንደ ጓደኛው ሮቢንሆ ሁሉ ነገሮች በመቀየራቸው ደስተኛ ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት በተለይም በጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓ.ም. ከመጋቢት እስከ ታህሳስ ላይቤሪያ በኢቦላ ተህዋሲ ወረርሽኝ ትናጥ ነበር። ሞት እና ፍርሃት በላይቤሪያ እና ላቤሪያውያን ላይ ጥላቸውን ያጠሉበት አራት ወራት። በዛ ፍርሃት ውስጥ ከነበሩት የአገሪቱ ዜጎች አንዱ ሞሰስ ካርተር ነው።

«የኢቦላ ወረርሽኝ የተከሰተበትን አንደኛ አመት ስናከብር በኢቦላ ተኅዋሲ ምክንያት በርካታ ሰዎች የሞቱበት ያለፈው አንድ አመት በአገራችን ታሪክ ፈጽሞ የማንረሳው ጊዜ ነው። በአገሪቱ ላይ በቀላሉ የማይፋቅ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግርም ፈጥሮ አልፏል።»

ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በጊኒ የታየውና በሚያዝያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ኢቦላ መሆኑ የተደረሰበት ወረርሽኝ የላይቤሪያን ብቻ ሳይሆን የምዕራብ አፍሪቃ አገራት ዜጎችን በየጎዳናው እና የህክምና ማዕከላት ለሞት ዳርጓል። በወረርሽኙ የሰብዓዊ ድርጅቶች እና የህክምና ማዕከላት ሐኪሞችና ባለሙያዎችም ሌሎችን ለማዳን ሲረባረቡ ህይወታቸውን አጥተዋል። ወረርሽኙ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የጤና መሠረተ-ልማት የበለጠ አዳክሞታል። አንድ አመት ያስቆጠረው ወረርሽኝ ጋብ አለ ቢባልም እንደገና እንዳያገረሽ ያሰጋል። በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ባለፈው ሳምንት ሶስት የህክምና ዶክተሮች በተኅዋሲው መያዛቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የካቲት 26 ቀን 2007 የመጨረሻዋን ህመምተኛ ነጻ በማለት የሸኘችው ላይቤሪያ ለተከታታይ 21 ቀናት አዲስ ህመምተኛ ሳይገጥማት ቆይታለች። ከተኅዋሲው ሙሉ በሙሉ ነጻ ለመባል የሚያስፈልጉትን 42 ቀናት ሲቆጥሩ የከረሙት ላይቤሪያውያን አሁን አዲስ ህመምተኛ ገጥሟቸዋል። በላይቤሪያ የኢቦላ መቆጣጠር ም/ል ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ፍራንሲስ ካቴህ የአገሪቱ ዜጎች ተኅዋሲውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ይናገራሉ።

«ኢቦላ ሙሉ በሙሉ ስለመጥፋቱ እርግጠኞች እስክንሆን ድረስ ጠፍቷል ማለት አንችልም። ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ስንናገረው የነበረ ነው። ከነበርንበት እዚህ ያደረሱንን የመከላከያ ስልቶች መተግበራችንን መቀጠል ይኖርብናል።»

የዓለም ጤና ድርጅት የወረርሽኙን አንደኛ አመት በማስመልከት ባወጣው ዘገባ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የተኅዋሲውን ከመለየት ጀምሮ ለወረርሽኙ ፈጣን አገራዊ ምላሽ እስከመስጠት ድረስ ፍጹም ዝግጁ አለመሆናቸው አስከፊ እንዳደረገው አትቷል። በቀጣናው ባለው አስከፊ ድህነት ሰዎች ሥራ እና ምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለተኅዋሲው መዛመት ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል።እንደ ስርዓተ-ቀብር ያሉ የምዕራብ አፍሪቃውያን ክዋኔዎች እና ባህላዊ እምነቶች ደግሞ ከፍተኛውን ቦታ ወስደዋል። በዚህ ዘገባ መሠረት በሴራሊዮን የኢቦላ ተኅዋሲ ከሰው ወደ ሰው ከተላለፈባቸው መንገዶች ውስጥ 80 በመቶው በስርዓተ-ቀብር አፈጻጸም ወቅት በሚደረግ ንክኪ ነበር።በጊኒ፤ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን ያለው ደካማ የመንገድ እና የስልክ መሠረተ ልማት ህሙማንን እና ለምርመራ የሚፈለጉ የደም ናሙናዎችን በፍጥነት ወደ ህክምና ማዕከላት ለማድረስ እንቅፋት እንደነበሩም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ዶ/ር ፍራንሲስ ካቴህ ከኢቦላ ወረርሽኝ ነጻ ለመሆን ያላቸውን አቋም ላይቤሪያውያንም ይጋሩታል። ቪቪያን ሳሙኤልስ እና ሳራ ሳይዴ እያንዳንዱ ላይቤሪያዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ይናገራሉ።

«ከኢቦላ ጋር የሚደረገው ትግል አልተጠናቀቀም። ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከላይቤሪያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሰጠውን ምክር በንቃት መቀበል ይኖርብናል። የኢቦላ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የተጀመሩትን የመከላከያ ስልቶች አሁንም ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል።»

Bildergalerie Ebola - Schutzbekleidung für Ärzte und Pfleger amharisch

የኢቦላ ወረርሽኝ አንደኛ አመት በሚታሰብበት በዚህ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ተኅዋሲው በተስፋፋበት ወቅት ዓለም አቀፍ ጥሪ ለማቅረብ ዳተኛ ሆኗል የሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል። ድርጅቱ የተኅዋሲውን ዓለም አቀፍ ስጋት ለማወጅ ሊፈጠር የሚችለውን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት አድርጓል በማለት አሶሲየትድ ፕረስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የዜና ወኪሉ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሃላፊ ዶ/ር ማርጋሬት ቻን የተላኩ የውስጥ መልዕክቶችን መሠረት አድርጎ በሠራው ዘገባ በጊዜው የኢቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ስጋት ነው ብሎ መናገር በምዕራብ አፍሪቃ አገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል በሚል ፖለቲካዊ ውሳኔ ሃላፊነቱን ሳይወጣ ቀርቷል ብሏል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዶ/ር ማርጋሬት ሐሪስ ነቀፋውን ማጣጣላቸውን የዜና ወኪሉ ጨምሮ ገልጿል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ቢሮ ሠራተኞች የኢቦላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ሃሳብ ማቅረባቸውን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል። የዓለም ጤና ድርጅት የኢቦላ አስቸኳ ጊዜ አዋጅ ያወጀው ግን ሃሳቡ ከቀረበ ከሁለት ወራት በኋላ ነበር።

ጁሊየስ ካኑባህ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic