የኢቦላ በሽታ ተኅዋሲ ስርጭትና ስጋቱ | ዓለም | DW | 14.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢቦላ በሽታ ተኅዋሲ ስርጭትና ስጋቱ

የኢቦላ በሽታ ከምዕራብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ ድረስ ዓለምን እያተራመሰ ነው። በተኅዋሲው የተያዘ ሰው ከከስድስት እስከ አስራ ስድስት ባሉ ቀናት ዉስጥ ከታደለ ከህመሙ ይፈወሳል።አብዛኞቹ ግን ይሞታሉ። ለዓለም ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ነው የተባለው የኢቦላ ወረርሽኝ በተባበሩትመንግስታትድርጅትየአስቸኳይጊዜግብረ-ሃይል ተቋቁሞለታል።

ይሁንና ግብረ-ሃይሉ በስልሳ ቀናት ውስጥ ወረርሽኙን ለመግታት ያዘጋጀው እቅድ እስካሁን ፍሬ አላፈራም። የኤቦላን ወረርሽኝ ለመግታት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል ሲቋቋም የተኅዋሲው ስርጭት በምዕራብ አፍሪካ ብቻ የተወነ በመሆኑ ዋና ፅህፈት ቤቱን ጋና ነዉ-ያደረገዉ። ግብረ-ሃይሉ ገዳዩን ወረርሽኝ በስልሳ ቀናት ዉስጥ ለመግታት የነደፈዉን እቅድ ገቢር ለማድረግ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በፍጥነት እንዳላገኘ ተልዕኮውን የሚመሩት አንቶኒ ባንበሪ ይናገራሉ። 'የጤና ባለሙያዎች፤ ሄሊኮፕተሮች እና ለእርዳታ ድርጅቶች የሚሰጥ ገንዘብ ያስፈልገናል' የሚሉት ባንበሪ አሁንም የስልሳ ቀናት እቅዳቸው ወረርሽኙን ለመግታት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ያምናሉ።

Anthony Banbury, Vorsitzender der UNO-Sondermission UNMEER

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል ተልዕኮ መሪ አንቶኒ ባንበሪ

''በኢቦላ ከተያዙ ሰዎች መካከል ሰባ በመቶውን በስልሳ ቀናት ማከም፤ ይህን ቀውስ ለመቀልበስ ቁልፉ ጉዳይ ነው። ቢሆንም እጅግ የተለጠጠ እቅድ ነው። አሁን እቅዱን ለማሳካት ከአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይሉ ብቻ ሳይሆን የኢቦላን ወረርሽኝ ለመግታት ከሚሰሩ አጋር አካላት ምን እንደሚያስፈልገን በመለየት ላይ ነን። በስልሳዎቹ ቀናት አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ በማሟላት ይህን ሰፊ እቅድ ለማሳካት ጠንክረን እንሰራለን''

የኤቦላ ወረርሽኝ ምዕራብ አፍሪካን ተሻግሮ ሰሜን አሜሪካም ስጋት ፈጥሯል።በኢቦላ ተሕዋሲ ተለክፎ መታመም ፤መሰቃየት፤መገለልና መሞት ከተራ የምዕራብ አፍሪካ ዜጎች ተሻግሮ በሰሜን አሜሪካና ስፔን የጤና ባለሙያዎች ላይ አንዣቧል። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ድንበር በተሻገረው ተኅዋሲ ላይ ቢያርፍም በምዕራብ አፍሪካ ሁኔታው አሰቃቂ ደረጃ ላይ መድረሱን አንቶኒ ባንበሪ ይናገራሉ።

በላይቤሪያ፤ጊኒ እና ሴራሊዮን የሚኖሩ ሰዎች በዚህ በሽታ ያሉበት አስከፊ ሁኔታ እጅግ አስደንግጦኛል። እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው። ሰዎቹ እና የሃገራቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ወረርሽኙን ለመግታት የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይልን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ቀውስ ለመግታት ኢቦላ ሰዎች መግደሉን ለማስቆም መፍትሄ መፍጠር አለባቸው። የእኛ ግብረ-ሃይል ይህንን ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል።

በምዕራብ አፍሪካ እስካሁን በኢቦላ ተኅዋሲ ከተያዙት፤ 400 የጤና ባለሙያዎች 233 መሞታቸዉን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

በጊኒ ፤ላይቤሪያ፤ ናይጄሪያ፤ሴኔጋል እና ሴራሊዮን በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 8,000 መድረሱንም አለም አቀፉ ተቋም በድረ-ገጹ አስፍሯል። የአሜሪካን የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ ወረርሽኙ በአራት ወራት ውስጥ 1.4 ሚሊዮን ሰዎችን ሊያዳርስ ይችላል ብሏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግብረ-ሃይል የሚመሩት አንቶኒ ባንበሪም ይህን ወረርሽኝ መቼ መቆጣጠር እንደሚችሉ በግልጽ አያውቁም።

ዓለም በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽንኝ ለሃገራቱ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ነዋሪዎችና ከዛ በላይ ስጋት እንደሆነ ከሶስቱ ሃገሮች ተሻግሮ መስፋፋት ሲጀምር የተረዳ ይመስለኛል። የዓለም ሃገሮችና ህዝቦችን ለመጠበቅ የተሻለው መንገድ ደግሞ ወረርሽኙ በተከሰተበት አካባቢ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። ይህ የእኛ ግብረ-ሃይል ጥረት ዋንኛ ትኩረት ነው። መተንበይ አንችልም። የበሽታውን ባህሪና መስፋፋት የሚከታተሉት ሌሎች ናቸው። እኛ መሬት ላይ ላለው እውነታ ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን። በሽታውን ባለበት ለመግታት ጠንክረን እየሰራን ነው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic