የኢቦላ ሕሙማንና የ ኩባ ሀኪሞች ተልእኮ | ዓለም | DW | 27.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢቦላ ሕሙማንና የ ኩባ ሀኪሞች ተልእኮ

ኩባ ዓለም አቀፍ ቀውስ ሲያጋጥም እንዴት ባፋጣኝ ለርዳታ መረባረብ እንደሚቻል ፣ ወረት የማካበት ሥርዓት ያለውን ምዕራቡን ዓለም በማስተማር ላይ ናት። ከመስከረም ወር ማለቂያ ገደማ አንስቶ እስካሁን ከ 250 በላይ የህክምና ዶክተሮችንና ነርሶችን ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ልካለች።

ወደፊት በተጨማሪ 50 ይከተላሉ፤ አንዳንድ የዜና ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን 200 ይሆናሉ ወደፊት የሚላኩት። ባለፈው መጋቢት የኢቦላ መከሠት ከተገለጠ ወዲህ በ ሶስት የምዕራብ አፍሪቃ አገሮች፤ ላይቤሪያ ፤ ሴራሊዮንና ጊኒ ፤ ባጠቃላይ 4,900 ገደማ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ኩባው ፕሬዚዳንት ራውል ራውል ካስትሮ አስተዳደር ባሳየው ሰፊ ትብብር ፤ ራሳቸው ካስትሮና የኩባው ጤና ጥበቃ ሚንስትር ሮቤርቶ ሞራለስ ፣ በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት(WHO) ዋና ጸሐፊ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ዴቪድ ናባሮ ተወድሰዋል። የኩባ የርእዮት ጠላት የምትባለው ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ሳይቀሩ የኩባን ተነሳሽነት አድንቀዋል።

ኩባ በዛ ያሉ ሀኪሞችን ባፋጣኝ በመላክ በዓለም ዙሪያ የሚያቅማሙትን ሃገራት በመላ አሳፍራለች። ኩባ፤ ለርዳታ ፈጥና ስትደርስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋም አይደለም። እ ጎ አ በ 2005 በካሽሚር ብርቱ የምድር ነውጥ አጋጥሞ ብርቱ ጉዳት ሲደርስ ከፓኪስታን ይልቅ ባጣዳፊ በዛ ያሉ ረዳቶች የላከች ኩባ ነበረች። እ ጎ አ በ 2010 ሄይቲ በመሬት መንቀጥቀጥ ክፉኛ ስትጎዳ ቀድመው ለርዳታ የደረሱ ኩባውያን ሃኪሞች ነበሩ።

አሁን የኢቦላ ወረርሽኝ ምዕራብ አፍሪቃን ቀስፎ ይዟል። ቀውስ በሚያጋጥምበት ጊዜ ድጋፍ የሚሰጡ ረዳቶችና ቁስቁስ የሚልኩ ሌሎች መንግሥታትም አሉ። የኩባ ግን የተለየ ነው። በሃቫና የዓለምን ጤና ጥበቃ ድርጅት ቅርንጫፍ መ/ቤት የሚመሩት ሆሴ ልዊስ ዲ ፋቢዮ እንዲህ ይላሉ---

«ኩባ ፣ እዚህ ላይ የተለየ አቋም ያላት ሃገር መሆኗን መመሥከር ይቻላል። በመጀመሪያ ባስቸኳይ

ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ችሎታ አላት፤ የፖለቲካ በጎ ፈቃደኝነቱ አለ። የምትልካቸው ረዳቶች ተመክሮም ቀላል አይደለም።»

ኩባ በሀኪሞቿ የውጭ ሥምሪት ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደምታገኝም የታመነ ነው።በስደት የሚገኘው የኩባ ሊብራል ሕብረት የተሰኘው ለዘብተኛ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ፣ በሙያ ሀኪም የሆኑት አንቶኒዮ ገዴስ እንደሚሉት ከሆነ፣ የኩባ መንግሥትየፖለቲካ በጎ ፈቀደኝነት፣ የሚያስቀድመው የመርዳት ፍላጎትን ሳይሆን፤ የሃቫናው የካስትሮ መንግሥት የሚያገኘውን ዓለም አቀፍ በጎ ስምና እውቅና ነው።

«ኩባ በመጀመሪያ የፖለቲካ ገጿንn ማሳመር ነው የምትሻው፤ ሁለተኛ ምክንያት ኤኮኖሚ ነው። ሦስተኛ ፣ ኩባ የተባበሩት መንግሥታትን ወይም የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች፤ የምትፈልገው ሃገራት የእርሷን አቋምም ሆነ ፍላጎት በተመለከተ የድምጽ ድጋፍ እንዲሰጧት በተለየ መንገድ ማግባባት ነው»።

የኩባ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር 50,000 ሠራተኞች አሉት። በአሁኑ ጊዜ በ 66 አገሮች ተሠማርተው ለተቀጠሩበት ሃገርና ለትውልድ ሃገራቸው አገልግሎት ይሰጣሉ። 30 ሺ በቬነዝዌላ ተሠማርተዋል።

ከ 83 ሺ ኩባውያን ሀኪሞች መካከል ከሞላ ጎደል ሲሦው በተለያዩ አገሮች ይሠራሉ። 11,000 በብራዚል፤ 2,000 በአንጎላ፤ በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች በአጠቃላይ 2,000 ተሠማርተዋል። የኩባ መንግሥት በውጭ ሃገራት ከሚሠሩ ሃኪሞቹ ከ 6 ቢሊዮን ዩውሮ በላይ ገቢ ያገኛል። በከፊል እንደ ብድርም ነው ኩባውያኑ ለመንግሥታቸው የሚከፍሉት። ብራዚል ብቻ ለእያንዳንዱ ኩባዊ ሀኪም በወር 3,100 ዩውሮ ደመወዝ ብትከፍልም 900 ዩውሮ ብቻ ነው ለሀኪሙ የሚደርሰው ፤ አብዛኛው ለኩባ መንግሥት ነው የሚተላለፈው።

ኩባ አሁን ኢቦላን ለመታገል ወደ ምዕራብ አፍሪቃ የምትልካቸው ሀኪሞች፤ ሰፊ ተመክሮ ያላቸው ናቸው። በሥራ በሚሠማሩበት ጊዜ ከአደገኛው ተኃዋሲ ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ፣ ሃቫና አጠገብ በፔድሮ ኩሪ የሞቃት አካባቢዎች የህክምና ተቋም ፣ የ 3 ሳምንታት ሥልጠና ወስደዋል።

በካሪቢያን ባህር የምትገኘው ደሴት ተወላጆች የሆኑ 15,000 የጤና ባለሙያዎች ኢቦላ ወደአለበት አካባቢ ሄደው በሥራ ለመሠማራት ፈቀደኞች መሆናቸውን አመልክተዋል። አንቶኒዮ ገዴስ በፍላጎት መመዝገብ የሚባለው እንዲሁ ነው ባይ ናቸው።

«ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኝነት የማያሳይ፣ የሥራ ቦታውን ኀላፊነትም ካለው ይህንንም ሊያጣ ይችላል። ወይም ልጅ ያለው ከሆነ ፤ ልጅየው በዩንበርስቲ የሚማርበት ቦታ አያገኝም።»

ተክሌ የኋላ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic