የኢሳይያስ ድንገተኛ ጉብኝትና የምክር ቤቱ ውሳኔ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 08.05.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢሳይያስ ድንገተኛ ጉብኝትና የምክር ቤቱ ውሳኔ

​​​​​​​ኢትዮጵያ በኮሮና ተሐዋሲ ሥጋት ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማድረግ ባለመቻሉ ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መፍትኄን አጽድቆ መወሰኑ እንደተሰማ የተቃዋሚዎች ድምጽ ወዲያው ነው ያስተጋባው። የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በድንገት ኢትዮጵያን ለ3 ቀናት ጎብኝተው የተመለሱትም ይኸው ውዝግብ ጎላ ባለበት ወቅት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:07

የምርጫ ጉዳይ እና የኢሳይያስ ጉብኝት አነጋግሯል

ምርጫ በኢትዮጵያ ቀድሞም ቢኾን ገዢው ፓርቲ እና አንዳንድ ተቃዋሚዎችን ማወዛገቡ አልቀረም። ምርጫው ወደ ነሐሴ ወር መጨረሻ ሲዛወር ወንዞች በሚሞሉበት የክረምት ወራት ለምን ይካሄዳል የሚል ተቃውሞ ተሰምቶ ነበር። አኹን ደግሞ መላ ዓለምን በድንገት ከእንቅስቃሴ መግታት የቻለው የኮሮና ተሐዋሲ ጭራሽ በክረምት ወራትም ታስቦ የነበረው ምርጫ እንዳይካሄድ እንቅፋት ኾኗል። አምስት ዓመቱ የመንግሥት ሥልጣን የሚያከትመውም ከክረምቱ ማብቂያ ጋር መኾኑ ኹኔታው በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ብርቱ ፈተና ደቅኗል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ሳምንት ትዊተር ላይ ባሰፈሩት መልእክት ቀጣዩን ብለዋል። «ሁሌም ዕድገትና መሻሻል ባላለቀ ሥዕል፣ ባልተጠናቀቀ ዜማ፣ ባላለቀ ክርክር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከታሪክ እንማር፡፡ ልዩነታችን የምንሳሳልበት እንጂ የምንጠፋፋበት አይሁን» ሲሉ። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች የምርጫ ጉዳይ ይዞት በመጣው ልዩነት ዙሪያ በስፋት ተወያይተውበታል።

«ምርጫ ተወደደም ተጠላም በየ5ት ዓመቱ መተግበር ሕገ-መንግስታዊ መብት ነው» የሚል አስተያየት ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው ኪዳኔ ሐጎስ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው። ኄኖክ ፋንታ «ለኛ ለኢትዮጵያውያን ህዝብ የሚያስብ ፓርቲ እደሌለ ያወቅኹት አሁን ምርጫ ካልተደረገ ብለው ሲቀውጡ ነው፤ ያሳዝናል» ብሏል። ሮቤል «ይመስለናል እንጂ ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎቹም ጭምር ምርጫ ይፈራሉ። ምርጫ ማድረግ አንችልም ሲሉ የነበሩ ሁሉ በቆረጣ የመንግስትን ስልጣን ለመካፈል በሰላም ሀገር የሽግግር...ይላሉ። ታየኝ እኮ በነሱ ስንሻገር» የሚል አስተያየት ትዊተር ላይ አስፍሯል።

ቀጣዩ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ ይካሔዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው በመጪው ነሐሴ 23 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. ነበር። በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት ግን ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲያስታውቅ ቀጥሎ ምን ይኾናል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር።  ምርጫ ቦርዱ የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ኹኔታዎች ሲመቻቹ ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ሰሌዳ እንደሚያወጣ ገልጾም ነበር።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮቪድ 19ኝ ወረርሺኝ ምክንያት በዚህ ዓመት አይካሄድም ያለውን ምርጫ ወደፊት ለማድረግ የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥት 3 አንቀፆች የሕግ ትርጓሜ እንዲሰጥባቸው በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ አስቀድሞ ተሰማ።  አስተያየቶች የጎረፉት ወዲያው ነበር። ፋንታሁን ዐወቀ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «የሕገመንግሥታዊ ትርጓሜን መሥማት እና የሕዝብ ተወካዮችን መጠባበቅ ነው እንጂ ከአሁኑ አሰተያየት መሥጠት ያስቸግራል» ሲል ጽፏል።

በቀለ ዱጉማ የተባለ ሌላ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ችግርን ለመከላከል እና ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርጫ አካሄዳለው ብሎ ከመነሳት መደራደሩና መወያየቱ አይሻልም ከሌሎች ቡድኖች ጋር በመሆን?» ሲል ጠይቋል። ብሮከር ያሲኒ በሚል የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፦ «ጉዳዩ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ይፈታ ሲባል ቅንድባቸው የቆመው የሕገመንግስቱ ልዩ የጥብቅና ካ ለብሰው የቆሙ መሆናቸው ድንቅ» ብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባው የቀጣዩን ምርጫ እጣ ፈንታ በተመለከተ ከቀረቡለት አራት አማራጭ ሐሳቦች ውስጥ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ ተሰማ። የተቀሩት 3ቱ አማራጮች ምክር ቤቱን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ እና ሕገ መንግስት ማሻሻል የሚሉ ነበሩ።

በዚህም ሐሳብ ዙሪያ አስተያየቶቹ የጎረፉት ወዲያው ነው። «ቆይ ቆይ እኔ እምለው ለ27 ዓ.ም 3 አንቀፆች የሕግ ትርጓሜ ሳይሰጣቸው ነው ምርጫ የምክርቤት አባላት አስቸኳይ አዋጅ» ጠያቂው ላዋይ አካላት ነው። በረደድ ደነቀ የተባለ አስተያየት ሰጪ፦ «ምርጫው መካኼድ አለበት ሳይሆን ሽግግር መቋቋም አለበት። ካበለዚያ ሕገ ወጡ በጣም ብዙ ነው» ሲል ጽፏል። ዓለማየሁ ገለቱ ደግሞ፦ «በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ማንኛውንም ውሳኔ ለሕዝብ እና ለገር ሲል ርምጃ መወሰድ አለበት» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። «የመንግስት አካሄድ ትክክለኛና አማራጭ የሌለው ነው» ይሄ ደግሞ ሰመረ ወርቊ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጽሑፍ ነው።

ሕወሓት ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ

ምርጫው በመላው ኢትዮጵያ መሰረዙ ቢገለጥም የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)ግን ትግራይ ውስጥ ምርጫው እንዲደረግ መወሰኑን ያሳወቀው በዚሁ ሳምንት ነው። ህወሓት አያይዞም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት «በጠራራ ፀሐይ» እየተጣሰ ነው ማለቱ ተዘግቧል።

«ሕወሓት ምርጫ ለማድረግ ለምን ቸኮለ?» ሲል ይጠይቃል ስንታየሁ ሚሊዮን በፌስ ቡክ። «ምርጫ ግዴታ በ5 ዓመት መደረግ አለበት። በዛ ላይ ለሁሉም ከሕወሓትሆነ ከትግራይ ሚመጣው ጥያቄ መልሱ ስድብ ከሆነ ሰንብቷል ለዛም ጋዊ የሆኑ ሁሉም መንገዶች ያለ ምንም ማወላዳት መፈፀም ግድ ይላል» መዘክር ክፍሎም ለስንታየሁ የሰጠው መልስ ነው።

«እኔን በጣም የሚያዝናናኝ ይህ ም/ቤት በተሰበሰበ ቁጥር የህወሓት ተላላኪዎች የሚያለቃቅሱት ለቅሶ ነዉ። የዝብ ዉክልናውን ትተው የ1 ፓርቲ ዘፋኝ ሁነው ሲጮሁ እና ሳይሳካላችው ሲቀር ከምንም በላይ ያዝናናኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ነበር ያረረው» ሲል የጻፈው ደግሞ የአንበሳው ነኝ በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ ነው።

«ሳስበው በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት መንግስት የለም ሁለት የምርጫ ስርዓት የለም አለ ካላችህ አንዱ ሌላ መንግስት ነው ዜችም ይኖሩታል» ያለው ዮሐንስ ወልደ ኪዳን ነው። «ስለዚህ ሁለት እግር አለኝ ብለህ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም ጨዋታው ይቁም ባንዳዎች ሊጋለጡ ይገባል ኢትዮጵያዊነት ይለምልም» ሲል ሐሳቡን ያጠቃልላል።

በአጭሩ «መብት ነው» የሚል አስተያየት የሰጠው ደማ አበባው ነው። በተመሳሳይ በአጫጭር ሐረጋት ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት ኤም ዲ እና ኢትዮጵያ አቢሲኒያ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ናቸው። «ድንቄም ምርጫ» እና «ይናፍቃችኋል» ሲሉ።

የኢሳይያስ ድንገተኛ ጉብኝት

ሌላው በሳምንቱ አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው በድንገት መነገሩ ነው። ፕሬዚደንቱ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መሄዳቸውን በትዊተር ገጻቸው ቀድመው ይፋ ያደረጉት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል ናቸው። ፕሬዚደንቱ አየር መንገድ ውስጥ በቀይ ምንጣፍ ሲጓዙ የሚያሳይ ፎቶግራፍም አያይዘዋል። የፕሬዚደንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዑስማን ሣሌኅ አብረዋቸው መጓዛቸውን ትዊተር ላይ ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ ልዑካኑ ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር በፕሬዚደንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስተናጋጅነት የምሣ ግብዣ ማድረጋቸውንም ጽፈዋል። ፕሬዚዳንቷም የኤርትራ ልዑካንን እንጦጦ ጋራ ላይ እየተገነባ ባሉት ፓርክ ውስጥ በማስተናገዳቸው ደስታቸውን ትዊተር ላይ ገልጠዋል። «የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን የጥበቃ ሥራ ተሰጣቸው እንዴ የት አሉ ወይስ ውይይቱ እሳቸውን ያገለለ ነው?» የአቻምየለህ ደምወዜ ጥያቄ ነው። ጌታነህ አበራ፦ «ሁሉም ነገር አይነገርም። ቢያንስ መልካም ግንኙነት እንዳለ ማወቁ በቂ ይመስለኛል» ብሏል። «አብይ ከምስራቅ አፍሪቃ መሪዎች ጋ ቨርቿል ውይይት ሲያድርግ ነበር! ኢሳያስ አፈወርቂ ግን እንዲመጣ ተደር! ለምን? ኤርትራ ውስጥ ኢንተርኔት ስላሌለ ነው ወይስ ውይይታቸው ከኮሮና ያለፈ ነው? ••• ! አለ ነገር!» ሲል ትዊተር ላይ የጻፈው ዚያድ ተሾመ ነው።

የግብፅ አቤቱታ ፀጥታው ምክር ቤት 

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚብሥትር ለጸጥታው ምክር ቤት ላከው የተባለ ደብዳቤ በኢንተርኔት ተዘዋውሯል። ኢትዮጵያን ኢንሳይደር በሚል የትዊተር ገጽ የወጣው ጽሑፍ፦ «ግብጽ የህዳሴው ግድብ ሙሌት እንዲቆይ የሚጠይቅ አቤቱታ ለፀጥታው ምክር ቤት አስገባች» በሚል ነው የቀረበው። ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌት ለመጀመር መወሰኗንንም፦«ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ደቅናለች» ስትል ግብጽ መጥቀሷን ይገልጣል ጽሑፉ። ናቲ ብ ይፍሩ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ባቀረበው ጽሑፍ፦ «የግብጽ ታክቲክ ወትሮም የሚገመት ነው» ብሏል። ግብጽ ምንጊዜም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ ሲሰማትም ካደፈጠችበት መወርወር እንደምትጀምርም አክሏል።

ደረጀ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ፦ ኢሳይያስ ወደ ኢትዮጵያ በድንገት የመጡት «ግብጽ ከጋረጠችው ግዙፍ ችግር ጋር የሚገናኝ ይመስለኛል» ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic