የኢሰመኮ ምክረ ሃሳብ ለፖሊስ እና ማረሚያ ቤቶች | ኢትዮጵያ | DW | 02.08.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢሰመኮ ምክረ ሃሳብ ለፖሊስ እና ማረሚያ ቤቶች

በኦሮሚያ ክልል አልፎ አልፎ ተጠርጣሪዎችን በሕግ በተቀመጠ ጊዜ አሊያም ከእናካቴው ፍርድ ቤት የአለማቅረብ ችግሮችን በሰፊው ማስተዋሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አመለከተ።

ኢሰመኮ በክልሉ 126 ፖሊስ ጣቢያና 27 ማረሚያ ቤቶች ላይ ምልከታና ምርመራ ማድረጉን ገልጧል

በኦሮሚያ ክልል አልፎ አልፎ ተጠርጣሪዎችን በሕግ በተቀመጠ ጊዜ አሊያም ከእናካቴው ፍርድ ቤት የአለማቅረብ ችግሮችን በሰፊው ማስተዋሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አመለከተ። ኢሰመኮ «በፍርድ ቤት ነፃ የተባሉ፣ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ወይም በዋስትና የተለቀቁ ሰዎችን አስሮ ማቆየት በኦሮሚያ ክልል እየተለመደ የመጣ ተግባር ሆኗል» ሲል ወቅሷልም። «በወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር በስፋት በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች ታይቷልም» ያለው ኢሰመኮ በክልሉ 126 ፖሊስ ጣቢያ እና 27 ማረሚያ ቤቶች ላይ ምልከታ እና ምርመራ በማድረግ የግኝቶቹ ምክረ ሀሳብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከሩንም ዐስታውቋል።

“ፖሊስ እና ማረሚያ ቤቶች በሰብአዊ መብቶች መርሆዎች ሊመሩ ይገባል” ኢሰመኮ

የአትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 126 ፖሊስ ጣቢያዎችና 27 ማረሚያ ቤቶች ላይ አካሄድኩ ባለው ክትትል የተስተዋሉ ክፍተቶች ለማረም እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን አመልክቷል፡፡

በማረሚያ ቤቶች የታዩ ጠናካራ ስራዎች እና ክፍተቶቹ

ለ2 ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ውይይት ማድረጉን ያመለከተው መንግስታዊው ገለልተኛ የመብቶች ተሟጋች ተቋም ኢሰመኮ “የታራሚዎች መረጃ አያያዝ፣ ታራሚዎችን በፈርጅ ለያይተው መያዝ፣ የቀለም ትምህርት መስጠት፣ በጀት በመጨመር የምግብ ጥራትና መጠን ማሻሻል፣ ከታራሚዎች ጋር የተፈጠረ መልካም ግንኙነት፣ በአብዛኞቹ የማረሚያ ቤቶች እንደ ድብደባ ያሉ ኢ-ሰብአዊ አያያዞች መቅረታቸው፣ የተሻሻለ የማረፊያ ቦታ እና ለታራሚዎች የሚሰጥ ይቅርታ” ኮሚሽኑ ጠንካራ ጎን በሚል ካነሳቸው ናቸው፡፡

በምርመራ ሂደቱ የተሳተፉት የኮሚሽኑ የጂማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ፤ “የማረሚያ ቤትን ዓላማና መተዳደሪያ ደንብ ለታራሚዎች በአግባቡ አለማሳወቅ፣ በሚሰጠው የትምህርትና የሙያ ስልጠና የሴት ታራሚዎች ተሳትፎ ማነስ፣ የማደሪያ ክፍሎች መጨናነቅና ንጽህና ጉድለት፣ የሕክምና አገልግሎት በቂ አለመሆን፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት፣ ለነፍሰ ጡርና ከህጻናት ጋር ለሚኖሩ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች ልዩ ድጋፍ አለመኖሩ” ደግሞ ሊታረሙ የሚገባ ክፍተት ነው በሚል በውይይቱ ከተነሱት ናቸው ብለዋል፡፡

Karte Äthiopien AM

የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር ኢብራሂም ሃጂ «በኮሚሽኑ አቅም መፈታት የሚችሉ ክፍተቶችን ለማረም ቁርጠኛ መሆናቸውን» ከበጀት ጋር የተያያዙ እንዲሁም የሌሎችን መስሪያ ቤቶች ትብብር የሚፈልጉ ተግባራት ላይ ድጋፍ መጠየቃቸውን የኢሰመኮ መግለጫ ጠቁሟል፡፡

በፖሊስ ጣቢያዎች የታዩ ተስፋ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች

በተመሳሳይ ኢሰመኮ በ2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያደረገውን ክትትል መሰረት በማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር መምከሩን አውስቷል፡፡

ኢሰመኮ ባደረገውም ክትትል “ተጠርጣሪዎች በብዛት በሕግ መሰረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ በፖሊስ መዝገብ ላይ እንደሚመዘገብ፣ ሥርዓታዊ የአካልና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት መቀነስ፣ የቤተሰብ ጉብኝት ሁኔታ መሻሻል” ከታዩ እምርታዎች ናቸው ብሏል፡፡

ይሁንና በዓመቱ “በወቅታዊ ሁኔታ እና ጸጉረ ልውጥ ናቸው ተብለው የሚያዙ ሰዎችን በእስረኛ መዝገብ ላይ አለማስፈር፣ በዚህ ሁኔታ የሚያዙ ተጠርጣሪዎችን በሕግ በተቀመጠ ጊዜ አሊያም ከናካቴው ፍርድ ቤት አለመቅረብ፣ ለተጠርጣሪዎች የተያዙበትን ምክንያት አለመንገር፣ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሕግን ባልተከተለ መልኩ ከአስተዳደር አካላት እና ‘ከፀጥታ ምክር ቤቶች’ በሚሰጡ ትዕዛዞች ሰዎችን ማሰር” ከተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው ተብለዋል። 

“በፍርድ ቤት ነፃ የተባሉ፣ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ወይም በዋስትና የተለቀቁ ሰዎችን አስሮ ማቆየት በኦሮሚያ ክልል እየተለመደ መጥቷል” ብሏል ኢሰመኮ፡፡ “በወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር በስፋት በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች ታይቷልም” ነው የተባለው፡፡ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑና ለሚፈጽሙት ጥፋት መደብደባቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ለተጠርጣሪዎች የሚቀርቡ የምግብ፣ የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት ውስንነትም ከቤተሰብ ርቀው ለሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ሆኖ መስተዋሉም ተነስቷል፡፡

በነበረው ውይይት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ “በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር የፖሊስ ሥራ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን፤ ሆኖም የተጠርጣሪዎችን መብቶች እንዳይጣሱ፤ የታዩ ክፍተቶችም መታረም ያለባቸው ናቸው” ማለታቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አንስቷል፡፡

የኢሰመኮ ምክረ ሃሳብ

የኢሰመኮ የምርመራ እና ክትትል ሪጅናል ዳይሬክተር አቶ ኢማድ አብዱልፈታ፤ ኢሰመኮ ከሚያቀርባቸው ምክረ ሀሳቦች ተቀባይነት አግኝተው ተፈጻሚ የሚሆኑ የመብዛታቸውን ያህል ገቢራዊ የማይሆኑ የኮሚሽኑ ጥሪዎችን በተመለከተም የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶችም ጭምር ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ግፊቱ እንደሚቀጥል ነግረውናል፡፡

ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን ባለማክበር የሚፈጸሙ እስራቶች እና በጸጥታ አካላቱ ከፍርድ ሂደት ውጪ የተፈጸሙ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል በተለያዩ ጊዜያት መግለጫ አውጥቶ ያውቃል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic