የኢራን የኑክሌር ዉዝግብ-IAEA ና የኤል በረዳይ ስንብት | ዓለም | DW | 30.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኢራን የኑክሌር ዉዝግብ-IAEA ና የኤል በረዳይ ስንብት

በቴሕራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለማስጣል ለሚፈልጉት ለዩናይትድ ስቴትስና ለተባባሪዎችዋ ግን ጉዳዩን ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለማቅረብ ጥሩ መሰረት መሆኑ አያከራክርም።የኢራን አፃፋ መረር-ከረር ያለዉም ለዚሕ ነዉ።

default

---ከአዲሱ ሐላፊዉ ጋር

30 11 09

የአለም የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንን (IAEA)-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ለአስራ-ሁለት አመት የመሩት ዶክተር መሐመድ ኤል-በረዳይ-እንደ ትልቅ ዲፕሎማት «ለሐይማኖት ያልወገንኩ»ጳጳስነኝ ማለታቸዉ ቀርቶ ወይም ዘንግተዉት በቅዱስ ፍራንሲስ ፀሎት ታላቅ ሥልጣን-ድርጅታቸዉን ሲሰናበቱ ድርጅታቸዉ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራንን አወገዘ።የቴሕራን አፃፋ-አመታት ያወዛገበዉ የኑክሌር መርሐ-ግብሯ ከበረዳይ ዘመነ-ሥልጣን በሕዋላም መቀጠሉን ጠቋሚ ነዉ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የበረዳይ ስንብት፥ የድርጅታቸዉ ዉሳኔ፥ የኢራንና የሐያሉ አለም ዉዝግብ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

የኑክሌር ድርድር-ወይም ተደራዳሪዎች ስድስትን ሳይወዱት አልቀሩም።የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር መራሐ-ግብር በድርድር ለማስቆም-የሚወያየዉ ቡድን ስድስት ሐገራትን ያስተናብራል።የኢራቅ በርግጥ-ስድስትም-ሁለት አይደለም ድርድር የሚባል ነገርም ጨርሶ አላስፈለገዉም ነበር።ኢራን በኑክሌር መርሐ-ግብሯ ሰበብ ከምዕራባዉያን ሐገራት ጋር የገጠመችዉን ዉዝግብ በድርርድር ያስወግዳል የተባለዉ ቡድን ግን አምስት ሲደመር-አንድ ይሉታል።ያዉ ስድስት።

ግብፃዊዉ ዲፕሎማት ዶክተር መሐመድ ሙስጠፋ ኤል-በረዳይ የአለም አቀፉን የአዉቶሚክ ሐይል ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የ(IAEA)ን የበላይ ሐላፊነት ሥልጣን ታሕሳስ አንድ 1997 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከሲዊድናዊዉ ቀዳሚያቸዉ ከሐንስ ማርቲን ብሊክስ ሲረከቡ-የዩናይስትድ ስቴትስና የሰሜን ኮሪያ ዉዝግብ-ንትርክ የዲፕሎማሲ ወዝ-የድርድር ተስፋ እየተላበሰ ነበር።ነገ-አስራ ሁለት አመቱ።

IAEA Treffen in Wien Mohamed ElBaradei

---ከተሰናባቹ ሐላፊዉ ጋር

ኤልበረዳይ-የቪየና ወንበራቸዉን ሲደላድሉ-በፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን መስተዳድር ትዕግስት፥ ብልሐት ይባል ፍርሐት፥ ብቻ ዲፕሎማሲ እንደ በጎ አማራጭ ተይዞ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ለማስፈተሽ፥ እንደ ድርድሩ ሒደት፥ እንደሚሰጣት ካሳ-ዋስትና ብዛት- ጨርሶ ለማቆምም እስከ መስማማት ደርሳ ነበር።

በሁለት አመት እድሜ ዲፕሎማሲዉ ደርቶ-ዉጤቱ ጎምርቶ-የዋሽንግተን-ፒዮንግዮንግ-ሶል ተቀናቃኝ ባለሥልጣን መሪዎችን ከአንዱ ርዕሠ-ከተማ ወደ ሌላዉ ሲያጉዝ ሲያስጎበኝ-መንበሩን ቪየና ላደረገዉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት እፎይታ፥ ለኤል-በረዳይ ደግሞ የመልካም ጅምር እርካታ አይነት ነበር።

ሁለት ሺሕ ማብቂያ ዋሽንግተን ላይ የተደረገዉ የመሪዎች ለዉጥ-የነበረዉን እንዳልነበረ ማስቀረቱ በርግጥ አያነጋግርም።ፕሬዝዳት ቡሽ በሰይጣን ዛቢያነት ከፈረጇቸዉ ከሰወስቱ ሐገራት ኢራቅን በሐሰት መረጃ ወርሮ-በሰሜን ኮሪያ ላይ ሲዝት፥ ቴሕራንን ዳግማዊት ባግዳድ ሊያደርግ ሲፎክር፥ የሐንስ ብሊክስ፤ የኤል-በረዳይ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይሁን የአለም ሕዝብ ጥሪ ጩኸት በርግጥ ስፍራ አልነበረዉም።

ያም ሆኖ ኤል-በረዳይና ድርጅታቸዉ ከሰሜን ኮሪያ እስከ ኢራቅ፥እስከ ኢራን በኑክሌር ሰበብ የሚነሱ ዉዝግብ ጠቦችን ለማርገብ ላደረጉት ሙከራ የሁለት ሺሕ አምስቱን የሰላም ኖቤል ለመሸመለም በቅተዋል። አምና ዋሽንግተን ላይ ሌላ-የመሪዎች ለዉጥ ሲደረግ ደግሞ ለኤል-በረዳይ፥ ለድርጅታቸዉ፥ዉዝግብን በድርድር መፍታት ለሚሹት ሁሉ በርግጥ ሌላ ተስፋ ነዉ።

ባለፈዉ ወር የስድስትዮሽ-የሚባለዉ ቡድን ቤጂንግ ላይ ለመሰብሰብ አንድ ሁለት ሲል አምስት-ሲደመር አንድ የሚባሉት ሐገራት ዲፕሎማቶች ጄኔቭ ላይ ከኢራን ጋር መደራደራቸዉ የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር የፈነጠቀዉ ተስፋ የመዳበሩ ተጨባጭ ምልክት-መልዕክትም ነበር።

«ዛሬ ጄኔቭ ዉስጥ ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ከሆኑት ከሌሎቹ ሐገራት ማለትም ከሩሲያ፥ ከቻይና፥ ከፈረንሳይ፥ ከታላቅዋ ብሪታንያ እንዲሁም ከጀርመን ጋር በመሆን ከኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ ጋር ተደራድረዋል።ይሕ ስብሰባ የተደረገዉ ከወራት ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በሕዋላ ነዉ።ከኢራን ጋር በሚደረገዉ ድርድር ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ሙሉ ተሳታፊ ከቡድን 5+1 ተሻራኪዎች ጋር ለመቀየጥ ዝግጁ መሆንዋን ሥ’ልጣን እንደያዝኩ ግልፅ አድርጌ ነበር።ከኢራን መንግሥት ጋር ትርጉም ያለዉ ድርድር ማድረግ እንደምን ፈልግ ፍላጎቴን ገልጬያለሁ።ዩናይትድ ስቴትስ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይመረት የሚያግደዉ ዉል እንዲከበር አበክራ ለመጣር ቁርጥ አቋም እንዳላት አስታዉቄ ነበር።ይሕ ከሆነ ሐገራት በሙሉ አለም አቀፍ ግዴታቸዉን እስከተወጡ ድረስ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚዉል የኑክሌር ሐይል ሊኖራቸዉ ይችላሉ።»

የጄኔቩ ድርድድር ኤል-በረዳይን ቴሕራን ወስዶ-ሲመልስ፥ የድርጅታቸዉ ባለሙያዎች ኢራን በድብቅ ተክላዋላች የተባለዉን የቆም የኑክሌር ማብላያ ተቋም ሳይቀር እንዲቆጣጠሩ በር ከፍቷል። ኢራን ለሰላማዊ አገልግሎት አዉለዋለሁ ለምትለዉ የኑክሌር ሐይል የሚያስፈልገዉ ንጥረ ነገር-በተለይም ዩራንየም ሩሲያና ፈረንሳይ እንዲብላላ የጄኔቭ ተደራዳሪዎች መስማማታቸዉን አስታወቀዉ ነበር።

የኦባማ መልዕክት፥ ከኢራን ጋር በቀጥታ ለመደራደር መፍቀዳቸዉ፥ ለጄኔቩ ዉል ማብቃቱን ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት መሐመድ ኤል-በረዳይ ጅምሩ ለበጎ ዉጤት፥ለመልካም ግንኙነት እንዲበቃ ተስፋ ማድረጋቸዉን አልሸሸጉም።

«ሰዎች ትልቁን ሥዕል ይመለከታሉ የሚል ጥልቅ ተስፋ አለኝ።ስምምነቱ የኢራንና የአለም አቀፉን ማሕበረሰብ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሠላማዊ ወደ ማድረግ ዉጤት በሚያመራ መልኩ ይታያል የሚል ተስፋ አለኝ።»

በወር-እድሜ ሰሞኑን ተስፋዉ ጨርሶ-ባይጠፋ በርግጥ ሟሿል።ለኤል-በረዳይ አስራ-ሁለት አመት የመሩትን-ትልቅ አድርገዉ፥ ለትልቅ ሰላማዊ ሽልማት የበቁበትን ያበቁትን ድርጅት የሚሰናበቱበት የፌስታ-ደስታ እለት በሆነ ነበር።ለጃፓናዊ ተከታያቸዉ ለዩኪያ አማኖ በጎ-መጥፎ ተሞክሯቸዉን የሚያጨዋዉቱበት እለት በሆነ-ነበር-አርብ።አልሆነም።

የኤል በረዳይ የመጨረሻ የስራ ቀን-የድርጅታቸዉ የገዢዎች ቦርድ ኢራንን በሚወነጅል ዉሳኔ-አበቃ።አርብ። ሰላሳ አምት አባል ሐገራትን የሚያተናብረዉ የአለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የገዢዎች ቦርድ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ኢራን በተለይ ቆም በተባለዉ ሥፍራ የሚገኘዉን የኑክሌር ማብላያ ተቋም ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ደብቃ በመቆየቷ ተጠያቂነች።

የአርቡ ዉሳኔ ከወር በፊት ጄኔቭ ላይ የተደረገዉ ድርድር-ስምምነት የፈነጠቀዉን ተስፋ በርግጥ የሚያዳፍን አይሆን-ይሆናል።ኤል-በረዳይ ያኔ ያሉት የመልካም የሰላማዊ ግንኙነት መሠረት-ተስፋ ግን ቢያንስ ላሁኑ የለም።እንደ ትልቅ ባለሥልጣን የመጨረሻ ቃላቸዉም-ለብዙ አመታት የሚታወቀዉን የዉዝግብ፥ ንትር

Iran - Atomkraftwerk Buschehr

ከኢራን የኑክሌር ተቋማት አንዱ

ክ ምክንያት መዘርዘር-ነዉ።

«ሥለ ኢራን የኑክሌር አለማ በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ሥጋት አለ።ይሕ ሥጋት ከበርካታ አመታት ጀምሮ የነበረ ነዉ።የሥጋቱ ምክንያት በከፊል እኛ እንደ IAEA የኢራን መርሐ-ግብር ሙሉ በሙሉ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚዉል መሆኑን ማረጋጋት በለመቻላችን ነዉ።»

በዘመነ-ሥልጣናቸዉ-የኢራንን አለማ ማረጋገጥ በርግጥ አልቻሉም።ከ2002-ማብቂያ እስከ ሁለት ሺሕ ሰወስት መጀመሪያ ግን ኤል-በረዳይም፥ ሐንስ ብሊክሲም የያኔዋ ኢራቅ የኑክሌርና የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ እንዳሌላት ካንዴ በላይ አረጋግጠናል ብለዉ ነበር።የኢራን ፖለቲከኞች የዛሬ ጥያቄም ይኸዉ ነዉ።ያኔ-ሥለ ኢራቅ የተሰጠዉ ማረጋገጪያ «ወረራን ለምን አላስቀረም።»-የሚል።

የኤል-በረዳይ ድርጅት ባለፈዉ አርብ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ለጊዜዉ በኢራን ላይ የሚያደርሰዉ ብዙ ተፅኖ አይኖርም።በቴሕራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለማስጣል ለሚፈልጉት ለዩናይትድ ስቴትስና ለተባባሪዎችዋ ግን ጉዳዩን ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለማቅረብ ጥሩ መሰረት መሆኑ አያከራክርም።የኢራን አፃፋ መረር-ከረር ያለዉም ለዚሕ ነዉ።

ትናንት የተሰየመዉ የኢራን ምክር ቤት የሐገሪቱ መንግሥት ከአለም አቀፉ አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ጋር የሚያደርገዉን ትብብር እንዲቀንስ አዟል።አስር-ተጨማሪ የኑክሌር ተቋማት እንዲቋቋሙም ፈቅዷል።አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ዛሬ እንዳስታወቁት የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪዉ ድርጅት ዉሳኔ እስከተሰማ ድረስ ኢራን ተጨማሪ ተቋማት የመገንባት እቅድ አልነበራትም።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤና የቀድሞዉ የኑክሌር ጉዳይ ዋና ተደራዳሪ አሊ ላርጃኒ «የአሞሌ-አርጩሞ ጨዋታችሁን ካላቆማችሁ ለአፀፋዉ አንሰፍም» አሉ-ትናንት።

«ከአዉቶሚክ ተቆጣጣሪዉ ባለሥልጣን ጋር የምዳደርገዉ ትብብር በጣም ወደ አነሳ ደረጃ ዝንቅ እንድናደርግ እያስገደዳችሁን ነዉ።የሚቀጥለዉን እርምጃችሁን በጥንቃቄ እንከታተላለን።ይሕን የማይረባ የአሞሌ-አርጩሜ አይነት ጨዋታችን ካላቆማችሁ ተጨማሪ እርምጃዎችን መዉሰዳችን አይቀርም።»

ከነገ-ጀምሮ ተራዉ የዩክያ አማኖ ነዉ።አል-በረዳይ በሁለት ሺሕ አምስት ኖቤል ሲሸለሙ ለማንኛዉም ሐይማኖት ያልወገንኩ ግን ጳጳስ ነኝ ብለዉ ነበር።የሰላም-ጳጳስ።የኑኬሌር ስጋት በማስወገድ ሰላምን ለማዉረድ ብዙ መጣር መልፋታቸዉ በርግጥ አላነጋገረም።ዉጤቱ-እንጂ አጠያያቂዉ።ለሐይማኖት አል-ወግኑም ያሉት የሰላም ጳጳስ-የቅዱስ ፍራንሲስን ፥«ፈጣሪ ሆይ ጥላቻ ባለበት የፍቅር መሳሪያ አድርገኝ»ን ፀልየዉ-በጥላቻ የተሞላችዉን አለም-እንደ ጡረተኛ ሊታዘቡት-ነገ-አንድ ይላሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic