የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር:ድርድርና ዉጤቱ | ዓለም | DW | 05.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር:ድርድርና ዉጤቱ

አልበረዳይ የሚመሩት ተቋም ባለሙያዎች በፋንታቸዉ የኢራን የኑክሌር ባለሙያዎች የአዉዳሚዉን ቦምብ አካላት ለመገጣጠም-እየተመራመሩ-እየሞከሩም ነዉ-ይላሉ

default

የኢራን የኑክሌር ተቋም-ካየር የተነሳ ፎቶ

በቴሕራን አንፃር ካራትነታቸዉ ይልቅ አንድነታቸዉ የጎላዉ የዋሽግተን፣ ለንደን፣ የፓሪስ በርሊን ባለሥልጣናት፣ የቴሕራን ተፃራሪዎቻቸዉ፣ መሐል የቆሙት የሞስኮ፣ ቤጂንግ አቻዎቻቸዉም ሁሉም አርብ ጄኔቭ ላይ ባደረጉት መደሰት መርካታቸዉን አልሸሸጉም።መሐመድ አል በረዳይ፥ ሳኢድ ጃሊሊን ተከትለዉ ቴሕራንን መጎብኘታቸዉ ድሞ ለጄኔቩ እንጭጭ-ተስፋ-ብርታት፣ለጅምር ደስታ-እርካታዉ ጥንካሬነቱ በርግጥ አያከራክርም።እርካታ-ደስታዉ የአራት አንዶቹን-እና የቴሕራን ተፃራሪዎቻቸዉን የቆየ-ዛቻ-አፀፋ ዛቻን ለማስወገድ ብዙም አለመተከሩ-እንጂ ጭንቁ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የጄኔቩ ድርድር ዉጤት መነሻችን፣ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ማጣቃሻ፣ የደስታ-እርካታ፣ የዛቻ-አፀፋ ዛቻዉ ተቃርኖ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ከኢራቅ ጦራቸዉን በማስወጣት፥ ኢራንና-ሰሜን ኮሪያን በድርድር በማሳመን፥ የአፍቃኒስታን ደፈጣ ተዋጊዎችን በሐይል-በማንበርከክ-ለስምንት አመታት አለም-የጠላዉን የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉን ቡሽን የዉጪ መርሕ እንደሚቀይሩ በምርጫ ዘመቻቸዉ ቃል የገቡት ባራክ ኦባማ የሚገጥማቸዉን ፈተና ክብደት ወትሮም አላጡም ነበር።

የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን እንደያዙ ከሐገራቸዉ የሥለላ ድርጅት የደረሳቸዉ መረጃ-ግን ለሥልጣን ካባቃቸዉ አለማ-መርሕቸዉ ቢያንስ አንዱን ገቢር ማድረጉ ከሁለቴ በላይ ማሰብን የሚጠይቅ ካሰቡት-በላይ የሚከብድ መሆኑን አረጋገጠላቸዉ።ኢራን ከቅድስቲቱ ከተማ ቆም-አጠገብ አዲስ ዩራንየም ማብላያ ጣቢያ በድብቅ መመሥረቷን የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ሐላፊዎች ላዲሱ ፕሬዝዳንታቸዉ ሹክ አሏቸዉ።ጥር-2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)

ኦባማ የአዲሱን መረጃ ጥልቀትና ትክክለኝነት፥ለወራት ሲያስጠኑ ሲያጠኑ ቆይተዉ መስተዳድራቸዉ ሰላማዊ ድርድርን ከማዕቀብ ቅጣት-የቀየጠ መርሕ እንደሚከተል ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ አደረጉ።ያም ሆኖ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ መርሕ የበላይ ሐቪየር ሶላና ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ እንዳሉት መርሑ፥ ድርድሩ፥ የድርድሩ ተካፋዮችም፥ መንፈሱም ከዚሕ በፊት የነበረዉ አይነት አልነበረም።

«መልዕክተኞቹ ወደዚሕ ሲመጡ ያሁኑ ስብሰባ ከዚሕ በፊት ከነበሩት ሁሉ የተለየ መሆኑን አዉቀዉት ነዉ።ተናግሬያለሁ።እደግመዋለሁም።የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የሚካፈልበት ድርድር ሲደረግ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ እስካሁን በተቆጠሩት ወራት ሰፊ ጥረት አድርገዋል።ቢሆንም ሁላችንም ባንድነት ስንሰበሰብ ያሁኑ የመጀመሪያችን ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ተባባሪዎችዋ ለድድር የዘረጉትን እጅ ኢራን እንቢኝ ብትል በተለይ የኦባማ መስተዳድር የሚገጥመዉ ፖለቲካዊ ኪሳራ ቀላል-የሚባል አይነት አይደልም።ከዚሕም በላይ ኢራን ወትሮም እንደምትለዉ ለሰላማዊ አገልግሎት ለሚዉል የኑክሌር መርሐ-ግብር አልደራድርም ብትል-በማዕቀብ ለመቅጣት ሩሲያና ቻይናን የመሳሰሉ ሐይላትን ለማሳመን የሚወስደዉ ጊዜ፥ማዕቀቡን ለማስከበር የሚወጣዉ ሐብት-ሐይል ብዙነትን ዋሽንግተንና የተባባሪዎችዋ አላጡም።

ከሁሉም በላይ ቴሕራኖችን እያዋዙ ወደ ድርድር ካልሳቧቸዉ በስተቀር የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር እንዳደረገዉ በማዕቀብ እና በሐይል ማስፈራራቱ ሁለት ሺ ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘግ ሚሳዬል እንዲሰሩ፥ እንዲሞክሩ፥ የኢራቅ ደፈጣ ተዋጊዎችን እንዲረዱ፥ የኑክሌር መርሐ-ግብራቸዉን በግልፅ-በድብቅም እንዲገፉበት ከማድረግ በስተቀር የተከረዉ አልነበረም።

በዚሕም ሰበብ ፖለቲካዊን አማራጭ-አጥብቀዉ የሚሹት ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ አርብ ጄኔቭ ላይ የሚሹት ሲሆን-የማይደሰቱበት ምክንያት አልነበረም።

«ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን በተመለከተ ሐላፊነትዋን እንደምታከብር በተጨባጭ እርምጃዎች ማረጋገጥ አለባት።ከዚያ ለመድረስ ዛሬ የተደረገዉ ዉይይት ግንቢ ጅምር ነበር።ይሁንና ጅምሩ በኢራን መንግሥት ተጨማሪ ገንቢ እርምጃዎች ሊጠናከር ይገባል።»

የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕመድ አሕመዲኒጃድ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ሐገራቸዉ ቆም አጠገብ ከምድር በታች የዩራኒየም ማብላያ መገንባቷን ጉዳዩ ለሚመለከተዉ ለአለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት IAEA አስታዉቃለች።ያረጋገጠላቸዉ፥ ያመናቸዉም የለም።ከዚሕ ቀደምም ኢራን ናታናዝ ላይ ዩራንየም ማብላያ ተቋም እንዳላት በሁለት ሺሕ ሁለት ያጋለጠዉ ብሔራዊ ምክር ቤት ለኢራን ተቋቁሞ (NCRI)-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ የተሰኘዉ ተቃዋሚ ሐይል ነበር።

እንጂ-የቴሕራን መንግሥት ፈቅዶ ያስታወቀዉ፥ የምዕራብ የሰለላ ባለሙያዎች በርብረዉ ያገኙት አልነበረም።ዛሬም-አሕመዲኒጃድን የሚያምን የለም።አሁንም የዩናይትድ ስቴትስ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ኢራን አዲስ የዩራንየም ማብላያ ጣቢያ ማቋቋሟን ያጋለጠዉም ያዉ-ተቃዋሚ ድርጅት ነዉ።
የድርጅቱ የዉጪ ግንኙነት ቃል አቀባይ ሞሐመድ ሞሐንደሲ እንደሚሉት ኢራን አዲሱን ማብላያ መገንባት የጀመረችዉ በሁለት ሺሕ ሁለት ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ከሁለት አመት በፊት ባወጣዉ ጥናንቱ ኢራን ዩራንየም ማብላላቷን እንዳቋረጠች አስታዉቆ ነበር።አዲሱ መረጃ ግን ይሕን ዉድቅ አድርጎታል።

ሞሐንዲስ እንደሚሉት አዲሱን የዩራንየም ማብለያ ተቋም በመገንባቱ ሒደት ሁለት የሩሲያ ሳይንቲስቶች ተካፋዮች ናቸዉ።ለኢራን የኑክሌር ተቋም መሳሪያና እዉቀት የምትሸጠዉ ሩሲያ በነሞሐንደስ መረጃ አለሞቃትም-አልበረዳትምም።ይልቅዬ የፕሬዝዳት ቡሽ መስተዳድር ሩሲያ አፍንጫ ስር ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬልና ራዳር ለመትከል ያሳለፈዉን ዉሳኔ ፕሬዝዳት ኦባማ በመሻራቸዉ ሞስኮዎች ኢራንን በመጫን ለዋሽግተኖች አፀፋዉን የመመለስ ያልተፃፋ ግዴታ ነበረባቸዉ።

አደረጉት።ቤጂንጎችም-ለሰሜን ኮሪያ እንደሚያደርጉት ለኢራንም «ሰላማዊ መፍትሔ» የሚለዉን መርሕ-እንቢኝ ሊሉ አይችሉም።የሚስጥር ተቋሙ መጋለጥ፥ የምዕራቡ ዛቻ፥ የሞስኮ-ቤጂንጎች ጫና ለቴሕራኖች ለድርድር ከመቀመጥ ሌላ-የሚያፈናፍን አማራጭ አልነበረም።የኢራን ልዩ ተደራዳሪ ሳኢድ ጃሊሊ አርብ ጄኔቭ ላይ በገቡት ቃል-መሠረት ተሰናባቹ የአለም የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ሐላፊ መሐመድ አል-በረዳይ ቅዳሜ ቴሕራን መግባታቸዉ የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሉት ድርድሩን ለመደራደር ሲሉ ብቻ የገቡበት አለመሆኑን መስካሪ ነዉ።

አል-በረዳይ ከቴሕራን ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በሕዋላ እንዳስታወቁት ደግሞ ኦባማ ተጨባጭ ያሉትን እርምጃ ኢራን ለመዉሰድ-አንድ ማለትዋን አመልካች ነዉ።

«ከዶክተር ሳሊሒ ጋር ባደረግነዉ ምክክር ተቆጣጣሪዎቻችን ክትትሉን ለማድረግና ቆም ለመሔድ ጥቅምት ሃያ-አምስት እዚሕ እንዲመጡ በመስማማታችን ተደስቻለሁ።ተቆጣጣሪዎቻችን እዚያ የሚገኘዉን ተቋም በተቻለ ፍጥነት እንዲመረምሩና ይዘቱን ማረጋገጥ እንዲችሉ ኢራን እንደምትተባበራቸዉና ግልፅ እንደምትሆንላቸዉ ተስፋ አደርጋለሁ።አምናለሁም።»

Mohamed ElBaradei IAEA bei der Ankunft im Iran

አል በረዳኒይና ጃሊሊ-ቴሕራን

ዲፕሎማሲያዊዉ ጥረት ከዚሕ መድረሱ ለተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆን አንድ የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማት እንዳሉት ለፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ፥ ለመላዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ለድፍን አለም ሠላምም አንድ በጎ እመርታ ነዉ።ከጄኔቭ-ቴሕራን የዲፕሎማሲዉ መፍትሔ በጎነት እርምጃ ሲሰማ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ዉዝግቧን በድርድር ለመፍታት መዘጋጀትዋ ከፒዮንግያንግ ተዘግቧል።

ይሕም ለሰላም የሩቅ ግን በርግጥ ቸር-ወሬ ነዉ።ሐቪየር ሶላና ባለፈዉ ሐሙስ እንዳሉት የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር በተመለተከተ ምዕራቡ በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ትከተለዉ የነበረዉ የሐይል-ዛቻ መርሕ ተለዉጧል።አል-በረዳይም ፍጥቻዉ በትብብር ተቀይሯል ባይ ናቸዉ።

«ተደስቻለሁ።ይሕ በጎ እርምጃ ነዉ።እኔ ሁል ጊዜ ያለኝ እምነት የኢራን የኑክሌር ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፥ በድርድር ይፈታል የሚል ነዉ።ለበርካታ አመታት ከኢራን በኩል ግልፅነት ያስፈልጋል፥ ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ በኩል ደግሞ ትብብር ያሥፈልጋል ሥል ነበር።እና አሁን ያለነዉ ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሆነ ይታየኛል።አቋማችን ከፍጥጫ ወደ ግልፅነትና ትብብር እየቀየርን ነዉ።»

ሁሉንም ያስደሰተዉ እርምጃ እንዴትነት አነጋግሮ ሳያበቃ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት እንደራሴዎች ኢራንን በማዕቀብ እንቀጣለን-የሚል ዛቻ አሰምተዋል።የኢራን አቻዎቻቸዉም ለአፀፋ ዛቻ አላመነቱም።አልበረዳይ የሚመሩት ተቋም ባለሙያዎች በፋንታቸዉ የኢራን የኑክሌር ባለሙያዎች የአዉዳሚዉን ቦምብ አካላት ለመገጣጠም-እየተመራመሩ-እየሞከሩም ነዉ-ይላሉ።እና በዛቻ-አፀፋ ዛቻ የታጀበዉ ደስታ-እርካታ አሁንም መንታ መንገድ ላይ ነዉ።

dw,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic