የኢራን የመገናኛ ብዙሀን አፈናና የአውሮፓ ህብረት ተቃውሞ | ዓለም | DW | 25.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኢራን የመገናኛ ብዙሀን አፈናና የአውሮፓ ህብረት ተቃውሞ

ኢራን ከአውሮፓ በሳተላይት የሚተላለፉ ያራድዮ እና የቴሌቪዥን ስርጭቶችን መፈኗን እንድታቆም የአውሮፓ ህብረት ጥሪ አቀርቧል። የኢራንን የመረጃ ልውውጥ አፈና የተቃወሙት የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሀገሪቱ የምታካሂደውን የስርጭት ዕወካ ለማስቆም ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

default

በፋርስ ቋንቋ ከተለያዩ አገሮች በራድዮ ወደ ኢራን ከሚሰራጩና ከታፈኑ ጣብያዎች መካከል፤ የዶቸ- ቬለ ራድዮም ይገኝበታል። የዝግጅት ክፍሉ ስርጭት ከመታፈኑም ሌላ ድረ-ጾቹም በኢራን ላሉ አንባብያን በከፊል እንደሚደርስ የስርጭት ቅንብር ክፍሉ አስታዉቋል። ይህንኑ በመገንዘብ የአዉሮጻ ህብረት ኢራን ዓለም አቀፍን የቴሌኮምኒኬሽን ደንቦች ተግባራዊ ለማድረግ የገባችውን ግዴታ እንድታከብር ጠይቋል። ሂሩት መለሰ ዘገባ ይዛለች

የኢራን ባለሥልጣናት በሳተላይት አማካይነት ወደ ኢራን የሚተላለፉ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ስርጭቶችን ማፈን የጀመሩት ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኃላ ነው ። የኢራኑ ፕሬይዳንት መሀሙድ አህመዲነጃድ ዳግም መመረጣቸው ተቃውሞ ካስከተለ በኃላ መንግስት ዶቼ-ቬለ እና ቢቢሲ በፋርስ ቋንቋ የሚያሰራጯቸውን ዝግጅቶችን አፈነ ። በርካታ ጋዜጠኞችንም አሰረ ። ከዚህ በተጨማሪም የኢራን ዜጎች ከኢንተርኔት መረጃ የሚያገኙባቸው መንገዶችም ተደናቀፉ ። የመረጃ አፈናው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውም እ.ጎ.አ የካቲት 11, 2010 ዓ.ም የኢራን እስላማዊ አብዮት 31 ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ነው ። በዚህ ወቅት ኢራን በፈረንሳዩ የሳተላይት ድርጅት Eutelsat አማካይነት ወደ ኢራን የሚተላልፉ ወደ 70 የሚጠጉ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ስርጭቶችን እንዲሁም ኢራናውያን የቀረጹዋቸውን የተቃውሞ ሰልፎችን የተመለከቱ ፊልሞችን እንዳይለዋወጡም አግዳለች ። አንዳንድ የአውሮፓ ህበብረት ምንጮች እንደሚሉት የኢራን ባለሥልጣናት በኢንተርኔት የሚላኩ የፅሁፍ መልዕክት ልውውጦችንም ይጠልፋሉ ። ኢራን ዜጎቿ በሳተላይት ከሚሰራጩ የቴሌቪዥንና የራድዮ ስርጭቶች እንዲሁም ከኢንተርኔት ፣ በነፃነት መረጃ እንዳያገኙና እንዳያሰተላልፉ ማገዷ እንደሚያሳስበው የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል ። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ብራሰልስ ቤልጅየም ውስጥ የተሰበሰቡት የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስለ እገዳው ባወጡት መግለጫ የኢራንን ድርጊት ተቃውመዋል ። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ቨርነር ሆየር የኢራን ዕርምጃ ተቀባይነት የለውም ብለዋል ።

«እንደምታውቁት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የራዲዮ ጣቢያዎችና መሰል ድርጅቶች የሳቴላይት ሥርጭቶች ፣ ሆን ተብሎ እየታወኩ ነው ። ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው ።»

Volksmudschahedin Iran

ህብረቱ ኢራን ፣ መቀመጫውን ስዊስ ላደረገውና የራድዮ ስርጭትን ብዛት ዓይነት ለሚቆጣጠረው እንዲሁም የሳተላይቶችን ምህዋር ለሚያደላድለው ዓለም ዓቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት በእንግሊዘኛው ምህፃር ITU የገባችውን ቃል እንድትጠብቅም ጠይቋል ። ድርጊቱን የኮነነው የአውሮፓ ህብረት በኢራን ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወስድ ግን በግልጽ አላሳወቀም ። ሆኖም አንዳንድ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ዕርምጃው የአውሮፓ ኩባንያዎች የኢሜል መልዕክቶችንና የሞባይል ስልክ ንግግሮችን መጥለፍ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለኢራን እንዳይሸጡ ማገድን ሊያካትት እንደሚችል ጠቁመዋል ። ይህም Le Figaro የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ዕትሙ ላይ እንዳሰፈረው ሲመንስ እና ኖኪያ የመሳሰሉት ኩባንያዎች የሚያመርቱዋቸውን መሳሪያዎች ሽያጭ ዕገዳ ማለት ሊሆን ይችላል ። የኢጣልያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንኮ ፍራቲኒ እንዳሉት አሁንም ቢሆን ኢራን መሰል መሳሪያዎችን እንዳታገኝ ተከልክላለች ።

« በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ረቂቅ የስነ ቴክኒክ መሣሪያዎቸ ለኢራን እንዳይሸጡ ተከልክሏል ። » ህብረቱ በኢራን ላይ የሚጥለው ዕገዳ ከዚህም ሊያልፍ እንደሚች ነው የሚጠበቀው ። ዕገዳው ኢራን በፈረንሳዩ Eutelsat በኩል ወደ አውሮፓ በሳተላይት የምታሰራጫቸው ዝግጅቶች ላይ ገደብ መጣልንም ሊጨምር ይችላል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሃመድ