የኢራን አብዮት ምክንያት፣ዉጤትና መዘዙ | ዓለም | DW | 11.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢራን አብዮት ምክንያት፣ዉጤትና መዘዙ

 ሻሁ የዘመናት አንፀባሪቂ ጀንበራቸዉ በ38ኛዉ ዓመት ከምዕራብ አድማስ ጥግ መድረሷን የተረዱት መሠለ።ጥር 1979 «ለዕረፍት» በሚል ሰበብ ጓዛቸዉን ጠቅልለዉ ከቴሕራን ዉልቅ አሉ።በወሩ የአመፁ በተለይ እስልምናን እንደ ርዕዮተ ዓለም አንግበዉ የሚታገሉ ወገኖችን--- ይመሩ የነበሩት ታላቁ አያቱላሕ ሩሆላሕ ኾሚኒ ከ16 ዘመን ስደት በኋላ ቴሕራን ገቡ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:34

የኢራን አብዮት፣ መካከለኛዉ ምሥራቅን የለወጠ ክስተት

110219

እስራኤል እንደ ሐገር ከተመሰረተች ከ1948 ጀምሮ የፀናዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ፖለቲካዊ ሥርዓት ባዲስ ጎዳና ይሾር ገባ።ከ1917 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ዓለምን በኮሚንስት-ካፒታሊስት እሁለት ገምሶ የሚያናክሰዉ ርዕዮተ-ዓለም፣ እስላምን-ከአብዮት የቀየጠ ሰወስተኛ አስተሳሰብ ታከለበት።የካፒታሊስቱ ቁንጮ የዓለም ልዕለ-ኃይል ዩናይትድ ስቴትስ ሐብታም ታማኝ፣ታዛዥ ጥብቅ ወዳጅዋን አጣች።የፋርሶች የ2500 ዘመን ንጉሳዊ አገዛዝ ተገረሠሠ።የካቲት 11 1979።ቴሕራን።የኢራን እስላማዊ አብዮት።ዘንድሮ አርባ ዓመቱ።ምክንያት፣ዉጤት፣መዘዙን ላፍታ እናቃኛለን።

ነሐሴ 1953።ቴሕራን። የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ሰላዮች ከአንድ ዓመት በላይ ያሴሩ፣ያቀነባበሩ፣በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የረጩበት የመፈንቅለ መንግስት ሴራ በድል ተጠናቀቀ።ዘመቻ አጃክስ ብለዉት ነበር። በ1951 በኢራን ሕዝብ የተመረጡት ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞሳደጊ ከስልጣን ተወገዱ።የለንደን ዋሽግተን ታማኝ አገልጋይ ንጉስ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲታገሉ የነበሩት ኢራኖች በጅምር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታቸዉ ቅጭት አንገታቸዉን ሲደፉ፣ ለለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ፅናት እንደሚታገሉ ጧት ማታ የሚደሰኩረት የለንደን-ዋሽግተን መሪዎች በሴራቸዉ ድል ይቦርቁ ገቡ።ደስታ-ፌስታዉ ወዳጅነቱን አጠንክሮ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ደዌይት አይዘናወር

ቴሕራንን እንዲጎበኙ ምክንያት ሆኖ ነበር።

«ፕሬዝደንቱ ቴሕራን ሲገቡ ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አቀባበል አድርጎላቸዋል።ለዚሕ ታሪካዊ ጉብኝት ሻሕ ፓሕላቪ ንጉሳዊዉ ቤተ-መንግስት ዉስጥ ልዩ አቀባበልና ለፕሬዝደንቱ ስጦታ አቅርበዉላቸዋል።»

ታሕሳስ 1959።

በርግጥም 1977፣ 1952 ወይም 53 ወይም 59 አልነበረም።ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተርም አይዘናወርን አይደሉም።ካርተር በ1977 ማብቂያ ወደ ቴሕራን የተጓዙት ግን አይዘናወር በ1953 ከዙፋናቸዉ ከተከሏቸዉ፣ በ1959 ቴሕራን ድረስ ተጉዘዉ ከጎበኟቸዉ ከንጉሰ-ነገስት መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ጋር የ1978ን አዲስ ዓመት ዋዜማን ለማክበር ነዉ።

ካርተር እንደ ልዕለ ኃያል ሐገር መሪ ቴሕራን ቤተ-መንግሥት ዉስጥ ሲንበሻበሹ በድፍን ኢራን፣  ዉስጥ ዉስጡን የሚንተከተከዉን ሕዝባዊ ብሶትና ቁጣ ያወቁት አይመስሉም።የዓለምን እንቅስቃሴ እያጮለገ ሰዓት-በሰዓት

ለመሪዎች ያቀርባል የሚባለዉ CIAም ሆነ ተባባሪዎቹ የብሪታንያዉ MI6 ወይም የእስራኤሉ ሞሳድ ለአሜሪካ መሪ የሰጡት መረጃ አልነበረም።ከነበረም ሰዉዬዉ ይፋ ማድረግ አልፈለጉም።

የፈለጉት ንጉሰ ነገስት መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ለ37 ዘመን ረግጠዉ የገዟት ኢራን «የሰላም ደሴት» እንደሆነች ማወደስ ነበር።«ኢራን በሻህ ታላቅ አመራር ምክንያት፣ በዓለም እጅግ ከሚታወከዉ አካባቢ አንዱ በሆነዉ አካባቢ የመረጋጋት ደሴት ናት።ይሕ ሊሆን የቻለዉ፣ ግርማዊ ሆይ፣ በእርስዎ አመራርና ሕዝብዎ በሚሰጥዎ ክብር፣ አድናቆትና ፍቅር ምክንያት ነዉ።»

ካርተር ያንቆለጰሷቸዉ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ የኢራን ንጉሰነገስ ናቸዉ።ሻሐንሻሕ፣ የአርያን ነገድ ብርሐን ናቸዉ።የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸዉ።የኢራን ዘመናይ ሥርዓት መሥራች ናቸዉ።በ1979 በኢራን የአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ማይክል ሜኪንኮ እንዳሉት ደግሞ ለአሜሪካኖችም ታማኝ አጋልጋይ ናቸዉ።«እሳቸዉ በኢራን የኛ ሰዉ ናቸዉ።የሳቸዉ ኢራን የኛ ሐገር ናት።ኢራን የነዳጅ ምንጫችን ናት።ኢራን የጦር መሳሪያ ደንበኛችን ናት።ኢራን በራስዋ መንገድ ከሶቭየት ሕብረት ጥቃት የምትከላከለን ናት።»

ሰዬዉ ለታማኞቻቸዉና ለሚታመኑላቸዉ በርግጥም ሁሉም ናቸዉ።ለአብዛኛዉ ኢራናዊ ግን ረጋጭ፣ጨቋኝ፣ ጨካኝ ናቸዉ።የ37 ዘመኑ ጭቆና ያንገሸገሸዉ ሕዝብ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ቴሕራንን ከጎበኙ ከጥቂት ወራት በኋላ የተደበቀ ቁጣ ተቃዉሞዉን ባደባባይ ይዘርገፈዉ ገባ።

ካርተር የመካከለኛዉ ምሥራቅ «የሠላም ደሴት» ያሏት ጥንታዊት ሐገር በአመፅ፣ ሁከት፣ ግድያ ተተረማሰች።ኮሚንስቶች፣ዴሞክራቶች፣ብሔረተኞች፣ እስላማዉያን ባንድ አብረዉ የመሩት ሕዝብ የአሜሪካኖች ጥይት፣የአሜሪካ-እስራኤል-ብሪታንያ የስለላ መረብ፣ የአረቦች ገንዘብ አልበገረዉም።«ሞት ለሻሕ»ን ይፈክር ያዘ።

 ሻሁ የዘመናት አንፀባሪቂ ጀንበራቸዉ በ38ኛዉ ዓመት ከምዕራብ አድማስ ጥግ መድረሷን የተረዱት መሠለ።ጥር 1979 «ለዕረፍት» በሚል ሰበብ ጓዛቸዉን ጠቅልለዉ ከቴሕራን ዉልቅ አሉ።በወሩ የአመፁ በተለይ እስልምናን እንደ ርዕዮተ ዓለም አንግበዉ የሚታገሉ ወገኖችን መጀመሪያ ኢራቅ ኋላ ፈረንሳይ ሆነዉ ይመሩና ያስተባብሩ የነበሩት ታላቁ አያቱላሕ ሩሆላሕ ኾሚኒ ከ16 ዘመን ስደት በኋላ ቴሕራን ገቡ።የካቲት 1 1979።

«ኢማሙ ገና ወደ ፈረንሳይ ከመሰደዳቸዉ ወይም አብዮቱ መልክና ቅርፅ ከመያዙ በፊት የሐገሪቱ መሪ መሆናቸዉ ሐቅ ነዉ።ምን ማለት ነዉ ሕዝብ እሳቸዉን ከተከተለ፣የሚሉትን ከሰማና ገቢር ካደረገ ወደድንም ጠላንም እሳቸዉ መሪ ናቸዉ።»

ከኮሚኒ ተከታዮች አንዱ።

በርግጥም የኢራን ሕዝብ እንደ

ታላቅ መሪ በደማቅ ስርዓት ተቀበላቸዉ።የሚሉትንም ገቢር ያደርግ ገባ።የሻሁን አገዛዝ ጥላቻ ብቻ ባንድ አብረዉ የነበሩት ኮሚንስቶች፣ዴሞክራቶችና ብሔረተኞች በእስላማዉኑ ተራ በተራ እየተደፈለቁ ተበታተኑ።ኾሚኑ ቴሕራን በገቡ በአስረኛዉ ቀን የኢራን አብዮት ድል በይፋ ታወጀ።የካቲት 1979።ዛሬ 40 ዓመቱ።

ከወር በኋላ በተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ የአምስት ሺሕ ዘመን ባለታሪኳ፣የፋርሶች ስልጣኔ መሠረትዋ፣ የነዳጅ ዘይት ሐብታሚቱ ሐገር ከ2500 ዘመን በላይ የፀናባትን ንጉሳዊ አገዛዝ በይፋ አስወግዳ እስላማዊት ሪፐብሊክ ሆነች።የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ አጥኚ ፕሮፌሰር ዓሊ አንሳሪ እንደሚሉት የኢራን አብዮት በጣሙን የመካከለኛዉ ምሥራቅን በመጠኑም የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓትን ለዉጦታል።

«እስላማዊዉ አብዮት በዓለም ላይ ያስከተለዉ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነዉ።መካከለኛዉ ምሥራቅን ቀይሮታል።የዩናይትድ ስቴትስና የምዕራባዉያንን ቁልፍ ተባባሪ አስወግዷል።ከዚያ ጊዜ በኋላ የመካከለኛዉ ምሥራቅን እንቅስቃሴ በሙሉ እየነካ ነዉ።»

በርግጥም የአረብ-እስራኤል ጦርነት-ከአረብ እስራኤል ይልቅ የኢራን እስራኤል ጦርነት ዓይነት መልክ ይዟል።የሊባኖስ፣የሶሪያ፤የኢራቅ፣ የሳዑዲ አረቢያ የባሕሬን፣ አሁን ደግሞ የየመን ጦርነት፣ፖለቲካዊ ዉዝግብ፣የስልጣን ሽኩቻ ይሁን ሕዝባዊ አመፅ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የእራን እጅ አለበት።

ዩናይትድ ስቴትስ ለረጅም ጊዜ ጥቅሟ «አደገኛ» የምትለዉን አብዮት ለመቀልበስ ገና ከጅምሩ መሞክሯ አልቀረም።የቀድሞ ታማኟን መደገፍ ቀዳሚዉ ነበር።ይሁንና ሐገር አልባዉን ንጉስ አንዴ በሕክምና ሌላ ጊዜ በሰብአዊነት ሰበብ ከሆስፒታል-ሆቴል ስታመላልስ ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ጀምሮ አሜሪካ ላይ ያቄመዉ የኢራን ሕዝብ በተለይም ታሪኩን የሰማዉን ወጣት ለበቀል ከማነሳሳት በስተቀር ለዋሽንግተንም ለስደተኛዉ ንጉስም የተከረዉ የለም።  

ሕዳር 4 1979።አሜሪካ ላይ ያቄሙት የኢራን ወጣቶች በቴሕራን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ወረሩ።«በመስኮቴ በኩል ወደ ዉጪ ስመለከት የኾሚንን ፎቶ ግራፍ ያነገቡ ወጣቶች ኤምባሲዉ አጥር ላይ ሲንጠላጠሉ አየሁ።ያ ዕለት ለኔ በጣም አስፈሪ ቀን ነዉ።»

የያኔዉ የኤምባሲዉ ባልደረባ ባሪይ ሮዘን።ወጣቶቹ 52 አሜሪካዉያንን አገቱ።የአጋች-ታጋች አስለቃቂዎች ድራማ ከ444 ቀናት በኋላ አብቅቷል።ሁሉም ታጋቾች ተለቀዋል።መዘዙ ግን ዛሬም በአርባ-ዓመቱ ቴሕራንና ዋሽግተኖችን እንዳወዛገበ ነዉ።

የኢራን አብዮት ከፈነዳ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ 6 ፕሬዝደንት ቀያይራለች።የኢራንን እስላማዊ አብዮተኞች ለማጥፋት ያልዛተ ፕሬዝደንት የለም።የኢራን እስላማዊ አብዮተኞችም «ትልቋ ሰይጣን» የሚሏትን አሜሪካንን ያለወገዙ «ሞት ለአሜካን»ን ያልፈከሩ-ያላስፈከሩበት ጊዜ የለም።

ኢራን ድብቅ የኑክሌር መርሐ-ግብር እንዳለት ከታወቀ ወዲሕ ደግሞ የሁለቱ መንግስታት ዉዝግብ

መልኩን ቀይሮ ኑክሌር ቦምብ-የመስራት አለማስራት ባሕሪ ይዟል።ዉዝግቡን በድርድር ለመፍታት የሞከሩት፣ከአዉሮጳና ከቻይና ኃያላን መንግስታት ጋር ተባብረዉ ከኢራን ጋር የተስማሙት ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ነበሩ።ኦባማ በትራምፕ ሲተኩ ግን የነበረዉ ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።

 «ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር የተደረገዉን ስምምነት ማፍረሷን ዛሬ አዉጃለሁ።ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረዉን ማዕቀብ ዳግም የሚያፀና ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ እፈርማለሁ።በጣም ከፍተኛ ደረጃ ያለዉን ምጣኔ ሐብታዊ ማዕቀብ ገቢር እናደርጋለን።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግንቦት 2018።ማዕቀቡም ዳግም ተጣለ።ዉግዘት፣ፉከራ፤ሽኩቻ፣ የእጅ አዙር ዉጊያዉም ከየመን-እስከ ፍልስጤም፣ ከሶሪያ እስከ ሊባኖስ ቀጠለ።

የቴሕራን መሪዎች እንደሚሉት በአሜሪካ-እስራኤሎች የሥለላ መረጃ፣ ከሶሪያ በስተቀር በአረቦች ገንዘብ የተደገፈዉን የኢራቅን ጦር ስምንት ዓመት ተዋግተዉ ድል አድርገዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ወርራ የባግዳድ ቤተ-መንግሥትን ለቴሕራን ወዳጆች ለማስረከብ ተገድዳለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅ ሳዑዲ አረቢያ የምትመራቸዉ የዓረብ መንግስታት በኢራን የሚደገፉ የየመን አማፂያን ለማጥፋት ያዘመቱት ጦር የመን ዉስጥ ይዳክራል።አራተኛ ዓመቱ።በኢራንና ሩሲያ የሚደገፉትን የሶሪያዉን ፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን ለማስወገድ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ 29 መንግሥታት በቀጥታም፣በተዘዋዋሪም፣በዲፕላሚስም፣በገንዘብም፣ በጦርም መዋጋት ከጀመሩ-ስምንት አመታቸዉ። እስካሁን አሸናፊ ካለ በሽር አል-አሰድ ናቸዉ።ከእንግዲሕስ? 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

                              

Audios and videos on the topic