የኢራን ባለስቲክ ሚሳይል እና የአባይ ወንዝ ድርድር | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 10.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢራን ባለስቲክ ሚሳይል እና የአባይ ወንዝ ድርድር

የኢራን እና የዩናይትድ ስቴትስ ፍጥጫ የሚሳይል ድብደባ አስከትሏል። ግብፅ፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ጉዳይ አዲስ አበባ ውስጥ በዝግ ያደረጉት ስብሰባ ያለስምምነት ጠናቋል። በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ከመጉላላት እና ከአካል ጉዳት ባሻገር የተማሪዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል። አስተያየቶችን አሰባስበናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:08

ሳምንታዊ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት

የኢራን ባለስቲክ ሚሳይል ጥቃት

የኢራን ዩናይትድ ስቴትስ ፍጥጫ የፈጠረው ስጋት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ በጉልህ ነበር ያስተጋባው። ኢራን ለተገደሉባት ጄነራሏ የምትወስደው የበቀል ርምጃስ እስከምን ይደርስ ይኾን? የበርካቶች ስጋት የወለደው ጥያቄ ነበር። ኢራን የበቀል ርምጃዋን ስትጀምር የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው አጸፌታ የምትሰነዝረው ኃይለኛ በሚባለው ጦር ሠራዊቷ እንዳልኾነ ገልጠዋል። ይልቁንም አጸፌታው ጠንከር ያለ ማዕቀብ በመጣል ነው ማለታቸው ለጊዜውም ቢኾን ብዙዎችን አረጋግቷል። 

ልክ የዛሬ ሳምንት ዐርብ ማለዳ። ኢራቅ መዲና ባግዳድ ከሚገኘው አየር ማረፊያ ተሽከርካሪዎች እየወጡ ነበር ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት። ዩናይትድ ስቴትስ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ እና አብረዋቸው የነበሩ የሒዝቦላ ታጣቂ ቡድን አመራርን ተሽከርካሪዎቹ ውስጥ እንዳሉ ከሰው አልባ ጢያራ በተወነጨፉ ሚሳይሎች ገደለች። መግደሏንም በፕሬዚደንቷ በኩል ለዓለም ይፋ አደረገች። ግድያውን የፈጸምኩት የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማት ላይ ሊደርሱ የተቃጡ ጥፋቶችን ለማስቆም ነውም አለች። 

ቁጣ በመላ ኢራን እና ወዳጆቿ ዘንድ ነደደ። ኢራን ዋነኛ የጦር አበጋዟን ነው የተነጠቀችው። እናም በአጭር ጊዜ የበቀል ጥቃት እንደምትሰነዝር ዛተች። ዝታም አልቀረች። ረቡዕ ማለዳ ላይ ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ይዞታዎችን በባለስቲክ ሚሳይሎች ለ22 ጊዜያት ደበደበች። 

ኤፍ ሲ አርሰናል በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ስም የቀረበ ጽሑፍ፦ «የሚገርመው» ሲል ይንደረደራል።  «የሚገርመው 22 ሮኬት አስወንጭፋ 1 ወታደር ላይ እንኳን ጉዳት አላደረሰችም፤ አርፋ ብትቀመጥ የተሻለ ነው። አለሁ አለሁ ማለት ለሳዳምም አልበጀ አቅምን ማወቅ ትልቅነት ነው» ሲል ይጠናቀቃል። 

«ኢራን ምን ያህል ጠንካራ ናት?» በኃይሉ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ያሰፈረው አጭር ጥያቄ ነው። ኢራን የኒውክሌር አረር በማብላላት የጦር መሣሪያ ሳትሠራ አትቀርም የሚል ስጋት በዩናይትድ ስቴትስ እና በኃያላኑ ሃገራት መካከል ይንጸባረቃል። ኢራን ኢራቅ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠፈሮች ላይ ያስወነጨፈችውን ጨምሮ የተለያዩ አይነት የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችም ባለቤት ናት። 

ለአብነት ያኽል ሶመር ክሩዝ ሚሳይል የተባለው የኢራን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይል 7 ነጥብ 24 ሜትር ርዝመት አለው። ይህ ሚሳይል የኢራን አብዮት 40ኛ ዓመት ከመከበሩ አራት ዓመት ቀደም ብሎ ነበር ለዓለም ይፋ የተደረገው። ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሉ እስከ 3,000 ሜትር ርቀት ተጉዞ የተፈለገለትን ዒላማ መምታትም ይችላል።

 

ስለዚህ እና ሌሎች የኢራን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎች የሚያብራራ ፎቶግራፍ ያያዘችው ፌቨን ቲ የተባለች የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የ ኢራን ቦልስቲክ ሚሳኤል ኢትዮጵያ ድረስ የመወንጨፍ አቅም እንዳለው ባየን ጊዜ» የሚል ጽሑፍ እና በድንጋጤ ዐይኑ የተጎለጎለ ምስል ትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች። ሚሳይሉ ምን ያህል ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚችል በዓለም አቀፍ ጥናቶች እና እቅድ ማዕከል የሚሳይል ስጋትን የሚተነትነው ክፍል  ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል። 

በእርግጥ የድረ ገጽ መረጃው እንደሚያመለክተው ይህ ሚሳይል ከተወነጨፈ በኋላ የሚሸፍነው ርቀት ከኢራን ቴህራን አዲስ አበባን አቋርጦ የኬንያ ሞያሌ መድረስ የሚችል ነው። ፌቨን ቀጠል አድርጋም፦ «አልፎ ተርፎ ኢራን በነዚህ ሚሳኤሎች ልታደባያቸው ካሰበቻቸው የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ሰፈሮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ሃገራችንን አካባቢ እንዳሉ ባወቅን ጊዜ» ስትል በመጻፍ የሚሮጡ ሁለት ሰዎች ምስልንም አያይዛለች።  ጽሑፏን የምታጠቃልለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ «እምቢ ለጦርነት» በሚል ሐሽታግ በሰፈረ መልእክት ነው። 

ላስታና፣ ሰቆጣ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ያሳዝናል፣ደግሞ፣አሜሪካ፣አገር፣ልታፈርስ፣ነው?» ሲል ጠይቋል። ናቲ አበበ ደግሞ እዛው ፌስ ቡክ ላይ ባሰፈረው አጠር ያለ ጽሑፍ፦ «ኢራን ከአሜሪካ ጋር?» ሲል ጠይቋል። «አይጥ ከድመት ገር እየተጫወትች ነው» ሲልም ከሳቅ ጋር ጽሑፉን ቋጭቷል። አብዱሰላም ሰዒድ በአንጻሩ ትዊተር ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፦ «ይዞ መፎከር ይልሃል እንደ ኢራን! ጀግና ሀገር » ብሏል። 

የኢራን ዩናይትድ ስቴትስ ፍጥጫ ወደ ለየለት ግጭት የሚያመራ ኸኞነ ዳፋው በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ የውጭ ሀገር ሊተርፍ ይችላል እየተባለ ነው። አንዳንድ ሀገራት ለጥንቃቄ በሚል ከወዲሁ ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ዳር ዳር እያሉ መኾናቸው ተገልጧል። በርካታ የእስያ ሃገራት ዜጎቻቸው ከኢራን እና ኢራቅ እንዲወጡ እያሳሰቡ ነው። በርካታ ዜጎቿ በአረብ ሃገራት የሰው ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩባት ፊሊፒንስ ዜጎቿ ከኢራቅ በአፋጣኝ መውጣት ግዴታቸው እንደኾነ አሳስባለች። በርካታ ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት እንደሚኖሩ ይታወቃል። 

ትናንት ማምሻውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቶሌዶ ውስጥ በምርጫ ዘመቻቸው ያሰሙት ንግግር በሚል አጠር ያለ የቪዲዮ ምስልም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት እየተንሸራሸረ ነው። ፕሬዚደንቱ እንዲህ አሉ፦ «ስለ የዓለም የኖቤል ሽልማት አንድ ነገር ልንገራችሁ። ስምምነት አድርጌ አንዲት ሀገርን አድኜያለሁ። እናም የዚያች ሀገር መሪ ያቺን ሀገር በማዳኑ አሁን የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝቷል። ለራሴ ለመኾኑ ከዚያ ጋር የሚገናኝ ምን ነገር አለ? አልኩ» በርካታ ሰዎች ንግግሩን በተለያየ መንገድ በመተርጎም አስተያየት እየሰጡ ነው። 

የዓባይ ወንዝ ድርድር

ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ለሦስትዮሽ ያደረጉት አራተኛ ዙር ስብሰባ የተጠናቀቀው ረቡዕ እና ሐሙስ እለት በዝግ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ነው። በስብሰባው ሁለተኛ ቀን ሐሙስ ማምሻው ላይ ሃገራቱ ከስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን የሚጠቅሱ ጽሑፎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ላይ ተሰራጭተዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ ፦«የህዳሴው ግድብ ድርድር ያለስምምነት ተጠናቀቀ» በሚል ርእስ ሐሙስ ዕለት አስነብቧል። ስለድርቅ ብያኔ እና የግድቡ የውኃ ሙሊት ሒደት ላይ ሃገራቱ አለመስማማታቸው ተገልጧል።

ግብፅ ግድቡ ከ12 እስከ 17 ዓመት እንዲሞላ ሐሳብ ማቅረቧን ኢትዮጵያ ከ4 እስከ 7 ዓመት ማለቷ እና መስማማት አለመቻሉን በማኅበራዊ መገናኛ አውታር የተንሸራሸረው ጽሑፍ ይገልጣል። 

አሰፋ ሙሉ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ በሰጠው አስተያየት፦ «ውይይት ነው እንጂ በአባይ ድርድር የለም» ብሏል። ተመስገን ዘነበ የድርድሩ ውጤት ከመነገሩ ቀደም ብሎ በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚከተለውን ጽፏል። «ምን ዋጋ አለው በሌለ ነገር መደራደር? የአባይ እራስ ጣና በትልቅ በሽታ ወስጥ ሆኖ ከየት በሚመጣ ውኃ ነው የሚደራደሩት?» ሲል ጠይቋል።  ልጅ አለማየሁ አስፋው ደግሞ እዛው ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፦ «ያሳዝናል አፍሪቃ ሁሌም የዓለም ባንክ የሚታዘብላት አህጉር» ሲል ቁጭቱን አንጸባርቋል። 

በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሄድ መለስ በሚለው ግጭት እና አለመረጋጋት እጃቸው አለበት የተባሉ ተማሪዎች እና መምህራን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ከፍተና አመራር ላይ የቅጣት ርምጃዎች እየተወሰዱ መኾናቸው ተሰምቷል። ዓሊ ሞሐመድ ቴሌግራም ላይ ባቀረቡት ጥያቄ፦ «ኢትዮጵያ ወዴት እየመራች ነው?» ብለዋል። 

«ሁሴን ነኝ ከአጋሮ» ያሉ የቴሌግራም ተከታታያችን ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተመለከተ ዘለግ ያለ መልእክት አስተላልፈዋል። «ይድረስ ለኢትዮዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙሉ» ሲል የሚንደረደረው ጽሑፋቸው ተማሪዎች በብሔር እና በሃይማኖት ሳይለያዩ በሰላም መማር እንዳለባቸው መክረዋል። ለዓመታት በዩኒቨርሲቲ ትምህርት የለፋ ተማሪ መገደል ተማሪዎችን ሊከነክን እንደሚገባም አሳስበዋል። «ይኽ ከተመቻቹ በእዉነት መማር በጣም ያሳዝናል» ሲሉም አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።

  

የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ተማሪዎችን ማባረር ጀምረዋል። ብራሃኑ ትርሳማብ በሚል ስም የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፦ «ችግር ፈጣሪዎችን እየለዩ መለየት ጥሩ ነዉ» ብለዋል።  በወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥፋተኛ የተባሉ 335 ተማሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። አንድ መምህር ከሥራ የተሰናበቱ ሲሆን 14 ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ጉዳይ ደግሞ እየታየ እንደሆነ ተገልጧል። ጅማ ዩኒቨርሲቲ 31 ለሚኾኑ ተማሪዎቹ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ሲሆን፤ 20 ተማሪዎችን ደግሞ ከአንድ ዓመት እሰከ እስከመጨረሻው ከትምህርት የሚያግድ ቅጣት ማስተላለፉ ተገልጿል። 

ከሰሞኑ አስራ አምስት ተማሪዎችን እንዳገደ የገለጠው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ያሬድ ማሞን ከኃላፊነታቸው ማንሳቱ ሐሙስ ዕለት ተዘግቧል።  በዛው ሐሙስ ቀን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች እና የጸጥታ ኃይላት መካከል ግጭት መከሰቱም ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች