የኢራንና የዩናይትድ ስቴትስ የጠላትነት ቁንፅል ወግ | ዓለም | DW | 13.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢራንና የዩናይትድ ስቴትስ የጠላትነት ቁንፅል ወግ

ክሮከር ጄኔቭ ዉስጥ የኢራኑ ወጣት ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒይ ከላኳቸዉ የቴሕራን ባለስልጣናት ጋር የአፍቃኒስታኑን አክራሪ ገዢ ፓርቲ ታሊባንን እና አልቃኢዳን በጋራ ለማጥፋት ተስማምተዉ ተመለሱ።የአሜሪካ ጦር በጄኔራል ሱሌማንይ ትዕዛዝ ከኢራን በሚንቆረቆርለት መረጃ እየታገዘ የአልቃኢዳና የታሊባን ስልታዊ ይዞታዎችን ያወድመዉ ያዘ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:20

የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ማብቂያ የለሽ ሽኩቻ

ጥንታዊዉ፣ ታሪካዊዉ፣ ታላቁ  የፋርስ ሕዝብ  በ1951 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መሪዉን ሲመርጥ፣ ዴሞክራሲን የመቀበሉ፤ ሻሆችን (ነገስታትን) እንቢኝ የማለቱ ማረጋገጪያ ነበር። የዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት ጠበቆችነን ባዮቹ  የዋሽግተን መሪዎች ግን የፋርሶችን ጅምር ዴሞክራሲ በመፈንቅለ መንግስት ደፍልቀዉ ቄሳሩን አነገሱ።1953።ፋርሶች፤ እስልማዊ አብዮት ሲሉ፣ ዋሽግተኖች ለቅልበሳ አሴሩ።1979።ፋርሶች አሜሪካኖችን ሲያግቱ፤ ዋሽግተኖች ጦር አዘመቱ።ግን ከሰሩ።ፋርሶች ከኢራቆች ጋር ሲዋጉ፣ ዋሽግተኖች  የመንገደኞችን አዉሮፕላን አጋይተዉ 290 ተሳፋሪዎችን ገደሉ።1988።ፋርሶች-ከዓለም ሲስማሙ ፣አሜሪካኖች ስምምነት አፍርሰዉ ማዕቀብ ጣሉ።2018።ዘንድሮ።ዋሽግተኖች  ፋርሳዊ ጄኔራል ገደሉ።ፋርሶች ለብቀላ ሲተኩሱ የመንገደኞች አዉሮፕላን አንድደዉ 176 ተሳፋሪ ገደሉ።ታሪካዊቱ ግን ትንሺቱ ሐገር ዛሬም ለብቀላ ትዝታለች። ታሪክ አልባዋ ግን ልዕለ ኃያሊቱ ምድር፤ኢራንን ዳግማዊት ሰርቢያ፤ አፍቃኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ ወይም ሶሪያ ለማድረግ የታሪክ ቅርስን ጭምር ለማጥፋት ትዝታለች።የፋርስ አሜሪካኖች የጠላትነት አጭር ወግ ያፍታ ዝግጅታች ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች በተጠቃች ማግስት መስከረም 2001 የያኔዉ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ርያን ክሮከር ወደ ጄኔቭ የተጓዙት ከአዉሮጳ አቻዎቻቸዉ ጋር ለመምከር ወይም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ አልነበረም።
ክሮከር ጄኔቭ ዉስጥ የኢራኑ ወጣት ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒይ ከላኳቸዉ የቴሕራን ባለስልጣናት ጋር የአፍቃኒስታኑን አክራሪ ገዢ ፓርቲ ታሊባንን እና አልቃኢዳን በጋራ ለማጥፋት ተስማምተዉ ተመለሱ።የአሜሪካ ጦር በጄኔራል ሱሌማንይ ትዕዛዝ ከኢራን በሚንቆረቆርለት መረጃ እየታገዘ

የአልቃኢዳና የታሊባን ስልታዊ ይዞታዎችን ያወድመዉ ያዘ።
አሜሪካኖች ከቴሕራኖች የሚፈልጉትን እስኪበቃቸዉ ካገኙ፣ አፍቃኒስታንን ምንቅርቅሯን ካወጡ  ከአራት ወር በኋላ ኢራንን ከኢራቅና ሰሜን ኮሪያ ጋር ደርበዉ «የሰይጣን ዛቢያ» ይሏት ያዙ።«እንደዚሕ አይነት መንግስታትና አሸባሪ ተባባሪዎቻቸዉ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ በመታጠቅ የዓለምን ሰላም ለማናጋት የሰይጣን ዛቢያ ይዘዉራሉ።»
ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ።ጥር 2002።ቴሕራኖችም ከ1979 ጀምሮ እንደለመዱት አሜሪካን «ታላቋ ሸይጧን» እያሉ ያስፈክሩ ያዙ።ጨዋታዉም መፈረሰ። 
መስከረም 2001 ታሊባንና አልቃኢዳን ለማስመታት እንደ ጭንቅ ቀን-ወዳጅ ከአሜሪካኖች ያበሩት ጄኔራል ባለፈዉ ሳምንት በአሜሪካኖች ሚሳዬል ኢራቅ ዉስጥ ነደዱ።ጥር 3 2020።ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒይ።
የዓለም ቁጥር አንድ አሸባሪ መሆናቸዉን አስገዳዮቻቸዉ ለዓለም የነገሩት ግን ሰዉዬዉ ከተገደሉ በኋላ መሆኑ ነዉ ፌዙ።ፈርዶ መርመራ። 
«ጨካኙ አሸባሪ የአሜሪካኖችን ሕይወት እንዳያጠፋ ወሳኝ እርምጃ ወስደናል።የአሜሪካ ጦር በሰጠሁት መመሪያ መሠረት የዓለም አንደኛ አሸባሪ ቃሲም ሱሌይማኒን አስወግዶታል።ሱሌይማኒ የቁዱስ ኃይል አዛዥ አዛዥ በመሆኑ ከደረሱት ከፍተኛ ጥፋቶች ለተወሰኑት ተጠያቂ ነዉ።»

ከአራተኛዉ ዓመተ-ዓለም ጀምሮ ኢላሚቶች፤ሜዴስቶች፤የታላቁ ሳይሩስ አቻሜንዶች፤ ታላቁ አሌክሳንደር እና ሙስሊሞች፣ ከምስራቅ አዉሮጳ እስከ ቲቤት ሸለቆ ታላቅ ግዛት የመሰረቱለት ሐገር ታላቅ ሕዝብ  ፍልስፍናን ከሳይንስ፤ የጦር ዉጊያን ከስዕል ጥበብ፣ ኃይማኖትን ከስልጣኔ ለዓለም ካስተዋወቁ ጥቂት ጥንታዊ ሕዝብ አንዱ ነዉ።
ፋርሶች ስልጣኔያቸዉ ከተበለጠ፣ ክንዳቸዉ ከዛለ፣ ግዛታቸዉ ከተከፋፈለ በኋላ የደረጁት የብሪታንያና የሩሲያ ኃያላን ስልታዊዉን ግዛት ለመቆጣጠር በሚሻኩቱበት በ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ቴሕራን ፖለቲከኞች አዲሲቱ እና ቅኝ የመገዛትን ፍዳ ወድምታዉቀዉ ዩናይትድ ስቴትስ ጠጋ-ጠጋ ማለት ጀምረዉ ነበር።
የቴሕ

ራኖች ስልት ወደ አካባቢዉ ሰወስተኛ ተሻሚ ሐገር ከመጋበዝ በላይ ለኢራን እንደማይበጅ ያወቁ የመሰሉት የያኔዉ የብሪታንያ እዉቅ ዲፕሎማት ጆርጅ  ከርዞን በ1892 «ኢራን፣በቼዝ ሰሌዳ ላይ እንዳለች ቁራጭ ሜዳ ዓለምን ለመቆጣጠር  የሚሹ ኃይላት የሚጫወቱባት (የሚሻኮቱባት) ሥፍራ ናት» ብለዉ ነበር።
አላበሉም።
ከሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የዓለምን የአስገባሪነት ሥልጣን ከአዉሮጶች የተረከበችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከቀዳሚዎችዋ ቅኝ ገዢዎችም፣ ከተፎካካሪዎችዋ ኮሚንስቶችም እንደምትሻል ለማረጋገጥ የዴሞክራሲን ሥርዓትን አስፈላጊነት፣ የእኩልነት፤የነፃነት፣የፍትሕ፣ የሰብአዊ መብት መከበርን አስፈላጊነት ከያኔ እስከ ዛሬ እንደሰበከች ነዉ።
ከዋሽግተን መሪዎች እስከ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች እስከ ዲፕሎማቶች፣ ከጋዜጠኞች እስከ ከፊልም ተዋኞች የሚለፈፍ፤የሚወደስ፣ የሚነዛዉ ዲስኩር በሻሕዎች አገዛዝ የተሰላቸዉን፣ በሶቬት ሕብረትና በብሪታንያ ወረራ የተቆጣዉን የ1940ዎቹን ኢራናዊ ልብ የማያማልልበት ምክንያት በርግጥ አልነበረም።

ከ1905 ጀምሮ የሻሕዎችን ፍፁማዊ አገዛዝ ለመገደብ «ሕገ-መንግስታዊ አብዮት» የተባለዉን ለዉጥ ገቢራዊ ለማድረግ ሲታገል የነበረዉ የኢራን ሕዝብ ለመጅሊስ (ፓርላማ) ከፍተኛ ስልጣን በሚሰጠዉ ሕገ-መንግስት መሰረት በ1951 ለመጀመሪያ ጊዜ የምክር ቤት እንደራሴዎቹንና ጠቅላይ ሚንስትሩን በዴሞክራሲያዊ ሥራዓት መረጠ።
የዩናይትድ ስቴትስ፣የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ ይሁኑ የሩሲያ መንግሥታት ከፓትሪስ ሉቡምባ እስከ ቶማስ ሳንካራ፣ ከሳሳልቫዶር አያንዴ እስከ መሐመድ ሙሪሲ፣ በሕዝብ የሚወደዱ ወይም በሕዝብ የተመረጡ መሪዎችን ማስገደል ወይም ከስልጣን ማስወገዳቸዉ በሰፊዉ ይታመናል።
የምዕራብ-ምስራቅ፤ የጥንት ያሁን ኃያላን በሕዝብ የተመረጡ ወይም የሚወደዱ መሪዎችን እያስወገዱ ወታደራዊ ገዢዎችን ወይም

የመካከለኛዉ ምሥራቅ ዓይነት ነገስታትን በጦር ኃይል ጭምር  የሚደግፉበት ምክንያት፣  በሕዝብ የሚመረጡ መንግስታት የየሐገራቸዉን ሕዝብ ጥቅምና ሐብት ለኃያላኑ አሳልፈዉ ስለማይሰጡ ነዉ የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ጥቂት አይደሉም።
ትናተናዉ ሐሰት ወይም እዉነት ይሆን ይሆናል።
የኢራን ሕዝብ በ1951 የመረጣቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞሳድግሕ የብሪታንያ ኩባንዮች የሚቆጣጠሩትን የጋስና የነዳጅ ተቋማትን ለኢራን ሕዝብ ጥቅም ለመዉረስ ማሰባቸዉ የለጋ መንግስታቸዉ መጥፊያ፣ የጅምሩ ዴሞክራሲም ቅጭት መሆኑ አላጠያየቀም።
የዴሞክራሲ ሥርዓት አቀንቃኟ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ መሐመድ ሞሳድግሕን በመፈንቅለ መንግስት አስወግደዉ ጨቋኙን ሻሕ ፓሕሌቭን ባነገሱ በ60ኛዉ ዓመት አሜሪካኖች ይፋ ያደረጉት መረጃ በግልፅ አረጋግጧል። 
«መረጃዉ በዴሞክራሲዊ መንግድ በተመረጡት በኢራን ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞሳድግሕን ላይ የተደረገዉን መፈንቅለ መንግስት የሚያወሳ ነዉ።ሞሳዴግ የነዳጅ ኩባንዮችን ለመዉረስ መዘጋጀታቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ፣ለሶቭየቶች ድል ነዉ ብላ እንድታሰብ አድርጓታል። ስለዚሕ ገና እንደተመረጡ ከሥልጣን ለማስወገድ CIA ከMI6 ጋር ማሴር ጀመረ።»
የCNN ጋዜጠኛ እንዳነበችዉ።ከ18መቶዎቹ ማብቂያ ጀምሮ አሜሪካኖችን ለሚያደንቅ፣ አሜሪካኖችን ጠጋ-ጠጋ ላለዉ፣ እንደ አሜሪካኖች ዴሞክራሲን ለማስፈን ለታገለዉ ኢራናዊ  የአዲሱቱን ልዕለ ኃያል ሐገር ክሕደትን ለተከታዩ ትዉልድ  የማይተርክበት ምክንያት በርግጥ ሊኖር አይችልም።
የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ ሮቢን ራይትስ እንደሚሉት የ1979ኙ ኢስላማዊ አብዮት፣ አሜሪካን የሚጠላ ስርዓት ምሥረታዉም የ1953ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ክሕደት መዘዝ ነዉ።
 «ሥለዚሕ ጉዳይ በተለያዩ ሶስት መፅሐፍቶች አንብቢያለሁ።ይሕ በርግጥ አዲስ አይደለም።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ መረጃዎቹን በዝርዝርና በግልፅ መስጠቷ፣ መፈንቅለ መንግስቱ ምን ያሕል አስፈላጊ እንደነበር ማረጋገጡ ነዉ አዲሱ ነገር።እርምጃዉ ከ25 ዓመት በኋላ ያመጣዉን መዘዝ CIA አለመገመቱን ያረጋግጣል።»
የዋሽግተን መሪዎች የ19753ቱ እርምጃቸዉ ከ25 ዓመት በኋላ የሚያመጣዉን  መዘዝ ሊያስቡ ቀርቶ በዚያዉ በ1979 ቴሕራን ላይ የሚንተከተከዉ አብዮታዊ ስሜት ሳይቀዘቅዝ ከስልጣን የተባበሩትን ንጉስ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ጋብዘዉ ነበር።ግብዣዉን  ከንቀት የቆጠረዉ ኢራናዊ 52 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ዜጎችን አገተ።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ታጋቾቹን በኃይልም በዲፕሎማሲም ማስለቀቁ አልሆነላቸዉም።እንዲያዉ ያዘመቱት ጦር ተዋርዶ ተመልሷል።ይሁንና አሜሪካኖች ከዚያዉ አካባቢ ሌላ ጅል ታዛዥ አላጡም።የባግዳድ ገዢዎችን በቀጥታም በተዘዋዋሪም አባብለዉ መስከረም 1980 ኢራንን አስወረሩ።ከጦርነት የተማገዱት የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች ከ444 ቀናት በኋላ የአሜሪካ ታጋቾችን ለቀቁ።ጥር 1981።
የኢራቅ እና የኢራን ጦርነት በጋመበት በ1987 ማብቂያ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ኢራንን የሚወጋ የባሕር ኃይል ወደ አካባቢዉ አዘመተች።ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ባሕር ኃይል ስታዘምት የ1987ቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።
ኃምሌ 3 1988፣ የኢራን አየር መንገድ ንብረት የሆነዉ A 300 አዉሮፕላን 290 መንገደኞቹን አሳፍሮ ወደ ዱባይ ለመብረር ከባንዳር አዉሮፕላን ማረፊያ ተነሳ።ጉዞ ወደ ዱባይ።የበረራ ቁጥር 655 አብራሪ ከሃያ ዓመትት

በላይ እንዳደረጉት ሁሉ «አመሰግናለሁ።መልካም ቀን አሉ።» መሬት ላሉ ባልደረቦቻቸዉ። የካፒቴኑ መልዕክት ያ ግዙፍ አዉሮፕላን ካጨቃቸዉ 290 ሰዎች የተሰማዉ የመጨረሻዎቹ  ቃላት ይሆናሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።
አዉሮፕላኑ አፍንጫዉን ወደ ዱባይ እንደደገነ የአሜሪካ ጦር ከባሕር ያወነጨፈዉ ሚሳዬል ቀልቦ አጋየዉ።290ዉም አለቁ።አብዛኞቹ ኢራናዉያን ነበሩ።60ዎቹ ሕፃናት እና ልጆች ።
በ32 ሁለተኛ ዓመቱ ዘንድሮ አሜሪካኖች የገደሏቸዉን ከፍተኛ የጦር ጄኔራሉን ደም ለመበቀል የኢራን ጦር ካወነጨፈዉ ሚሳዬል አንዱ የዩክሬንን የመንገደኞች አዉሮፕላንን መትቶ ጣለዉ።ታሪክ ራሱን ደገመ እንበል ይሆን? 
ብቻ የዋሽግተን መሪዎች በ1988 የኢራንን የመገንደኞች አዉሮፕላን መትተዉ 290 ሰዎችን ለፈጁት የጦር አዛዦቻቸዉ የጀግና ሜዳሊያ ሲሸልሙ፣ የኢራን ጄኔራሎች ለጥፋቸዉ ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ ነን ይላሉ።
«ከአሜሪካ ጋር እየተዋጋን ነበር።አሁንም ጦርነት ላይ ነን።የዚች ሐገር ወታደሮች ነን።ለዚች ሐገር ለመሰዋት ዝግጁ ነን።በፈጣሪ እምላለሁ።ይሕን ከማይ እዚያ አዉሮፕላን ዉስጥ ሆኜ፣ አብሬ ተከስክስሼ ብቃጠል እመርጥ ነበር።»
የኢራን አብዮታዊ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሆሴይን ሳላሚ።
ከ1953 ጀምሮ ስር የሰደደዉ፤ በ1979 የመንግሥታት ጠብ የሆነዉ የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ፍጥጫ ከሊባኖስ እስከ የመን፤ ከኢራቅ እስከ ሶሪያ፤ ከኩርዶች እስከ ፍልስጤም ብዙ ሺ ሰላማዊ ሰዎችን ፈጅቷል።ለአዉሮፕላን መንገደኞችም ተርፏል።የአሜሪካ መሪዎች የኢራን-ኮንትራ ከሚባለዉ ቅሌት ዶሏል።
ሁለቱ ሐገራት ከሌሎች ኃያላን ጋር በመሆን በ2015፣ ኢራን የኒክሌር ቦምብ  እንዳትሰራ የሚያግደዉን ስምምነት ሲፈራረሙ የዘመናት ጠብ፣ቁርቁስ፣ ተዘዋዋሪዉ ጦርነት-ሽኩቻዉ የመወገዱ ተስፋ መስሎ ነበር።ነጋዴዉ ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐዉስን ከቆጣጠሩ በኋላ ስምምነቱን አፍርሰዉ ከ2012 ጀምሮ የተለፋበትን መገለባበጣቸዉ እንጂ ቀቢፀ ተስፋ።
የኢራን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በጅምር ከተቀጨ ከ1953 ወዲሕ አሜሪካኖች ቬትናምን፣ግሪናዳን፣ ፓናማን፣ኒካራጓን፣ ሊቢያን፣ ወርረዋል ወይም ደብድበዋል።አሜሪካና ተባባሪዎችዋ ሰርቢያን፣ ኢራቅን፣አፍቃኒስታንን፣ ሶሪያን፣የመንን አፍርሰዋል።ተረኛዋ ኢራን ትሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic