የኢራንና የብሪታንያ ግንኙነት | ዓለም | DW | 24.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኢራንና የብሪታንያ ግንኙነት

ከአሜሪካኖቹ ኤምባሲ ፅሕፈት ቤት ጥቂት ራቅ ብሎ በ1970ዎቹ የተለጠፈ የሚመስለዉ መፈክር ዛሬም ይነበባል።«ያንኪዎች ወደ ሐገራችሁ ሒዱ»-ይላል።የቴሕራኑ ደግሞ «ሞት ለብሪታንያ» ማለቱ መዘንጋት የለበትም

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:34
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:34 ደቂቃ

የኢራንና የብሪታንያ ግንኙነት

የዛሬ-አራት ዓመት የለንደን እና የቴሕራን ፖለቲከኞችን ዛቻ፤ ፉከራ የሰማ ጦርነት ያልተለየዉ ዓለም «ከሌላ ጦርነት ሊሞጀር ነዉ» ብሎ አለመስጋት አይችልም ነበር። ትናንት ተቃራኒዉ ሆነ። የዋሽግተን፤ ለንደን፤ ብራስልስ ወዳጆች፤ በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ሰበብ ከቴሕራን ጋር የገጠሙትን ዉዝግብ፤ በሠላም ዉል ባረገቡ በወሩ ኢራንና ብሪታንያ አቋረጠዉት የነበረዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም ጀመሩ። ሁለቱ መንግሥታት አንዳቸዉ በሌላቸዉ ሐገር የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸዉን ትናንት በይፋ ከፍተዋል። ብሪታንያና ኢራን ለአራት ዓመታት የተዘጉ ኤምባሲዎቻቸዉን የከፈቱት፤ ዩንያትድ ስቴትስና ኩባ ከግማሽ ምዕተ-ዓመታት በላይ የዘጓቸዉን ኤምባሲዎቻቸዉን በከፈቱ በሳምንቱ መሆኑ ነዉ። ጥላቻ፤ ዉዝግብ፤ ዉጊያ፤ ጦርነት፤ እልቂት፤ ስደት ባጥለቀለቃት ዓለም የመግባባት፤ መቻቻል፤ የሠላም ብልጭታ ይሆን ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የቴሕራን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከኤምባሲዉ ፅህፈት ቤት የግቢ-በር ላይ የፃፉት መፈክር ዛሬም አልጠፋም። «ሞት ለታላቅዋ ብሪታንያ።» ይላል-በፋርስኛ። ያኔ የተዘጋዉ ኤምባሲ ግን ተከፈተ።«ይሕ ኤምባሲ ዳግም መከፈቱን በብሪታንያ መንግሥት ሥም ሳዉጅ ደስታ ይሰማኛል።»

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፊሊፕ ሐሞንድ «ዩኒየን ጃክ» የተሰኘዉን የብሪታንያ ባንዲራ ዳግም ሲሰቅሉ። በለንደን የቴሕራን ኤምባሲም ትናንትናዉ ተከፍቷል።

አያቶላሕ ሩሆላሕ ሆሜኒ የመሯቸዉ የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች በ1979 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩ ወዲሕ የኢራንና የምዕራባዉያን በጣሙን የአንጎ-አሜሪካ-ቴል አቪቭ ግንኙነት በጠብ-ቁርቁስ፤ በብቀላ-መጎሻሸም የተሞላ ነዉ።

ይሁንና የዋሽግተኝ ለንደን ጥብቅ ወዳጆች በ1953 ቴሕራን ዙፋን ላይ ያስቀመጧቸዉ ታማኝ አገልጋያቸዉ ንጉስ ሬዛ ሻሕ ፓሕሌቪ ሥልጣን መቀማታቸዉን ለመበቀል ዩናይትድ ስቴትስ የሞከረችዉን ዓይነት ቀጠተኛ እና ጠንካራ የሐይል እርምጃ ብሪታንያ ባለመዉስዷ እስከ 2011 ድረስ የለንደን ቴሕራኖች ጠብ ኤምባሲን ከሚያዘጋ ደረጃ አልደረሰም ነበር።

2009 ኢራን ዉስጥ የተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዉጤት የሐገሪቱን ፖለቲከኞች ዕሁለት ገምሶ ማወዛገብ ሲጀምር ግን ከቴል አቪብ እስከ ዋሽግተን የሚገኙ የቴሕራን ጠላቶችን ልዩ ትኩረት የሳበ፤ የቅርብ ክትትልና ዉዝግቡን የማቀጣጠል ፍላጎታቸዉን የቀሰቀሰ ነበር። ምርጫዉን አሸነፉ የተባሉትን የያኔዉ ፕሬዝደንት መሐሙድ አሕመዲነጃድን የሚቃወመዉ «አረንጓዴዉ ንቅናቄ» የተሰኘዉ ቡድን፤ ደጋፊዎቹን ላደባባይ ሰልፍ ማሳደም ሲጀምር የቱኒዝ-ካይሮዉ የነዉጥ-ለዉጥ ቴሕራንም የማሰለሱ ምልክት ተደርጎ ነበርም።

ዋሽግተኝ፤ ለንደን፤ ቴል አቪቭ ጥብቅ ወዳጆችና ተባባሪዎቻቸዉ የ32 ዘመን ጠላታቸዉ፤ የአያቶሁላዎቹ ሥርዓት፤ ሲነቃነቅ ዉድቀቱን ለማጣደፍ አመፅ፤ ሁከት ግጭቱን የማያራግቡበት ምክንያት አልነበረም።

ምዕራባዉያን መንግሥታት ይባስ ብለዉ በኢራን ላይ አዳዲስ ማዕቀብ ይጥሉ ገቡ። የኢራን የኑክሌር ሳይቲስቶች በቦምብ እየገያዩ፤ በጥይት እየተደበደቡ በተከታታይ የተገደሉትም በምርጫ ዉጤት ዉዝግቡ መሐል ነበር። ከ2010 እስከ 2012 በነበረዉ ሁለት ዓመት ዉስጥ ብቻ አምስት የኢራን ሳይንቲስቶች ተገድለዋል። የኢራን መንግሥት የሳይንቲስቶቹ ገዳይ- አስገዳዮች እስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ መሆናቸዉን በተደጋጋሚ አስታወቀ።

ምዕራባዉያን መንግሥታት ከስለላ እስከ ባለሥልጣኖቻቸዉ ዉግዘት፤ ከግዙፍ መገናኛ ዘዴዎቻቸዉ ዘገባ እስከ ዲፕሎማሲዉ ጫና ለተቃዉሞ ሠልፈኞቹ የሰጡት ድጋፍ በተጨማሪዉ ማዕቀብ፤ እና በሳይንቲስቶቹ ግድያ መጠርጠራቸዉ ሲታከልበት የአሕመዲነጃድ ደጋፊዎችን ለአፀፋ ሠልፍ አሳደመ፤ የቴሕራን ተማሪዎችን ደግሞ ለብቀላ ቴሕራን አዉራ ጎዳና ዘረገፈ።

1979 ዩናይትድ ስቴትስ ከሥልጣን የተወገዱትን የኢራን ንጉስ ሻሕን መደገፏ ያስቆጣዉ ተማሪ በቴሕራን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ከብቦ አሜሪካዊያንን ማገት የጀመረዉ ሕዳር ነበር። 1979። በሰላሳ-ሁለተኛ ዓመቱ ሕዳር ተራዉ የብሪታንያ ኤምባሲ ሆነ። 2011

ብሪታንያም ልክ እንደ አሜሪካ ኤምባሲዋን ዘጋች። በለንደን የቴሕራን ኤምባሲ እንዲዘጋ አዘዘች። የኢራን ዲፕሎማቶችን አባረረችም። የያኔዉ የብሪታንያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሔግ ማስጠንቀቂያ ደግሞ የሌላ ብቀላ፤ ምናልባትም የጦርነት ዝግጅት ይመስል ነበር።

«የኢራን መንግሥት ኤምባሲያችንን ከጥቃት ለመከላከል ማድረግ ያለበትን ባለማድረጉ ተጠያቂ ነዉ። ግልፅ ነዉ። ሌሎች ተጨማሪ ጠንካራ እርምጃዎች ይወሰዳሉ።»

ከዛቻ አለማለፉ በጀ። ኢራንና ምዕራባዉያን መንግሥታት ከርዕዮተ ዓለም፤ ከፖለቲካ ተቃርኖ፤ ከምጣኔ-ሐብት ሽሚያ ፍትጊያ አልፈዉ በኑክሌር መርሕ ግብር ሰበብ ሲወዛገቡ፤ ሲቆራቆሱ፤ ከኢራቅ እስከ ሊባኖስ፤ ከእስራኤል እስከ ፍልስጤም በተዘዋዋሪ ሲዋጉ ተከታዮቻቸዉን ሲያዋጉ ዓመታት አስቆጥረዋል።

የሶሪያዉ ጦርነት የርስ በርስ መልክና ባሕሪዉን ለዉጦ የዓለም ሐያላን እና የአካባቢዉ ተቀናኝ መንግሥታት ጉልበት መፈታተሺያ ሲሆንም የኢራንና የምዕራባዉያንን ነባር ጠብ ለማናር ሌላ ምክንናት ነዉ የሆነዉ። የየመን ጦርነትም እንዲሁ።

እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት(ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን የምዕራቡም፤ የምስራቁም፤ የፋርሱም፤ የዓረቡም፤ የአፍሪቃዉም ጠላት መሆኑ አምና ይሔኔ በአደባባይ ሲፈጋ ግን ቴሕራን፤ ዋሽግተን-ብራስልሶች በግልፅ ላለወጁት ትብብር በጋራ መቆም ግድ ነበረባቸዉ።

የብሪታንያዉ ኤምባሲ ትናንት ሲከፈት የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ «የሁሉን ትብብር» በማለት የገለፁት ይሕንኑ ሳይፈልጉ የመፈላለግን የዉዴታ ግዴታን ነዉ።

«እንደሚመስለኝ ይሕ አካባቢ ልዩ አቀራረብ ያስፈልገዋል። የፅንፈኝነት፤የሐይማኖት ሐራጥቆች ችግሮችና ሁከት ከዚሕ አካባቢ አልፈዉ ሁሉንም የሚያዉኩ ችግሮች ናቸዉ። እና የሁሉንም ልዩ ትኩረት ይሻሉ።»

ተዘዋዋሪዉ የዉዴታ ግዴታ ትብብር፤ የቴሕራን አዳዲስ ፖለቲከኞች ለዘብተኛ አቋም፤ የሩሲያና የምዕራባዉያን ጠብ መካረር የነዊልያም ሔግን ዛቻ፤ ሴራ፤ፉከራን ቀብሮ የቴሕራንና አምስት+አንድ የሚባሉትን ሐያላን መንግሥታትን ድርድር ለሰላማዊ ዉል አበቃ። ስምምነቱ በማዕቀብ የጫጫዉ የኢራን ምጣኔ ሐብት እንዲጠረቃ መጥቀሙ ብዙ ጊዜ ተብሏል። ብዙ ያልተባለዉ ለኢራን ሸቀጦቻቸዉን ለሚሸጡ፤ ከኢራን ነዳጅ ዘይት፤ ጋስ፤ ስጋጃና ሐር ለሚገዙ የምዕራባዉያን ኩባንዮች ና ነጋዴዎች ጠቀም ያለ ትርፍ የሚያስገኝ መሆኑ ነዉ።

ሕንዳዊ-ብሪታንያዊዉ የኢራን ጉዳይ ተንታኝ ሳሮሽ ዛይቫላ እንደሚሉት የበለፀጉት ሐገራት ነጋዴዎችን ቴሕራንን ማጨናነቅ የጀመሩት ስምምነቱ መፈረም-አለመፈረሙ በዉል ከመታወቁ ከብዙ ወራት በፊት ነበር።

«ባለፈዉ አንድ ዓመት ኢራን በሔድኩ ቁጥር የጃፓን፤የፈረንሳይ፤ የጀርመን፤ የብሪታንያ ብቻ የብዙ ሐገራት ነጋዴዎችን ሆቴሌ ዉስጥ አግኝቻለሁ።ሁሉም ማዕቀቡ ሲነሳ መነገድ እንዲችሉ ከኢራኖች ጋር ግንኑነት መፍጠር የሚፈልጉ ናቸዉ።»

የኑክሌር ጉዳይ ስምምነቱ ከተፈረመ ካንድ ወር ብዙም አልበለጠዉም።ሥምነቱ ከመፈረሙ በፊት ቴሕራንን ባጨናነቁት የምዕራባዉያን ነጋዴዎች ላይ ለመታከል ዲፕሎማቶች፤ሚንስትሮችና ጋዜጠኞች ወደ ቴሕራን እየጎረፉ ነዉ።የብሪታንያ መንግሥትም ኤምባሲዉን መክፈቱ፤ ሽሚያዉን ከዳር ሆኖ የሚመለከትበት ምክንያት ስለሌለ ነዉ።

ይሕ ማለት ግን የለንደን-በለንደን በኩል የዋሽግተን፤ ብራስልስ መንግሥታት ከኢራን ጋር ያላቸዉን ጠብ ሙሉ በሙ አስወገዱ ማለት አይደለም።የኑክሌር ጉዳይ ስምምነቱን አጥብቃ የተቃወመችዉ የምዕራባዉያን ዋና ወዳጅ የእስራኤልን አቋምን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትም አይፈልጉም። አይችሉምም።ኢራንም የ36 ዘመን ጠላቶችዋ በዋዛ ይለቁኛል ብላ አታስብም።

እንዲያዉም ብሪታንያ እና ኢራን የተዘጉ ኤምባሲዎቻቸዉን የከፈቱት ኢራን አዲስ ያሰራችዉን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል ባስመረቀች ማግስት ነዉ።ዘገቦች እንደጠቆሙት ሚሳዬሉ፤ ነገር ከተበላሸ ፤አንድም ወደ ቴል አቪቭ አለያም ወደ ሪያድ ወይ ወደ ሁለቱም መወንጨፍ ይችላል።አምስት መቶ ኪሎ ሜትር።

ኢራን አዲሱን ሚሳዬሏን ከማስመረቋ ቀደም ብሎ ደግሞ አንድ ሰዉ አልባ የሥለላ አዉሮፕላን (ድሮን) መትታ መጣሏን አስታዉቃለች።አዉሮፕላኑ የዩናይትድ ስቴትስ ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠረጠራል።

የቴሕራን-ምዕራባዉያን መደፋፈጥ፤ መኮራኮም፤ መጠላለፍ እንደቀጠለ ነዉ።የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፊሊፕ ሐሞንድ ትናንት እንዳሉት ግን ሌላዉ ቢቀር የዘመናት ጠላቶቹ ከመኳረፍ መነጋገርን መርጠዋል።

«ቀስበቀስ እና በጥንቃቄ መጀመር፤ ግንኙነታችንን ማዳበር አለብን።ከዚያ ምን ያሕል ርቀት መጓዝ እንደምንችል እናያለን።ባሁኑ ወቅት በመካከለችን ትልቅ አለመተማመን አለ።መሠረተዊ ያመለካከት ልዩነት አለን,ይሁንና አንዳችን በሌላችን ሐገር ያሉ ኤምባሲዎቻችን ዳግም መከፈታቸዉ አንዳችን ከሌላችን ጋር መነጋገርን የመምረጣችን ተምሳሌት ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ከአስር ቀን በፊት ሐቫና-ኩባ የሚገኘዉን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ሲከፍቱ ያስተላለፉት መልዕክትም ተመሳሳይ ነዉ።54 ዓመታት ያስቆረዉ የዋሽግተን ሐቫና ጠብ፤ ቁርቁስ ለሁለቱ ሐገራት ሕዝብ የፈየደዉ የለም የሚል።የቴሕራን ለንደን፤ የሐቫና ዋሽግተኑ ዕዉነት፤ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ እስከ ሩቅ ምሥራቅ፤ ከአፍሪቃ እስከ ምሥራቅ አዉሮጳ እስከሬን-መቅበር፤ ስደተኛ መቁጠር፤ ዛቻ፤ ፉከራ፤ ማድመጥ ለሰለቸዉ ዓለም የሠላም ሽዉታ መሆኑ አያጠያይቅም።

ያም ሆኖ ከአሜሪካኖቹ ኤምባሲ ፅሕፈት ቤት ጥቂት ራቅ ብሎ በ1970ዎቹ የተለጠፈ የሚመስለዉ መፈክር ዛሬም ይነበባል።«ያንኪዎች ወደ ሐገራችሁ ሒዱ»-ይላል።የቴሕራኑ ደግሞ «ሞት ለብሪታንያ» ማለቱ መዘንጋት የለበትም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic