የኢራንና የምዕራባዉያን ስምምነትና እድምታዉ | ዓለም | DW | 06.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኢራንና የምዕራባዉያን ስምምነትና እድምታዉ

ኑክሌርን ለኢራን ያስተዋወቀችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።በ1950ዎቹ «አቶሚክ ለሠላም» በሚል መርሕ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢራን የሐይል ማመንጪያ ተቋም ማስገባት ጀምራ ነበር።የኑክሌር ተቋም ግንባታዉን ያቋረጠችዉ ደግሞ ማንም ሳይሆን እራስዋ ኢራን ነበረች

እነ ሳዑዲ አረቢያ የየመን ፖለቲከኞችን ጠብ አጡዘዉ ደሐይቱን ሐገር በቦምብ ሚሳዬል የማጋያታቸዉ ድፍረት፤የእኒያ ነባር ጠበኞች ነባር ጠብ የመናሩ ዉጤት መሆኑ አያጠያይቅም። ከፍልስጤም-እስራኤል እስከ ሊባኖስ፤ ከኢራቅ እስከ ሶሪያ፤ ከኮሪያ እስከ ዩክሬን፤ የዘለቀዉ የነባር ጠላቶች፤ ጠበኞችን የማጋጨት፤ ማጋደል፤ ማፋጀት ሴራ፤ ሽኩቻ፤ ሽሚያቸዉ በርግጥ ግሟል።የማጠፋፋታቸዉ ነባር ስልት ንረት የመን ላይ የሚያስከትለዉ ጥፋት መጠን ሲተነትን ግን ዋሽግተን-ብራስልሶች፤ ከቴሕራን፤ ሞስኮ ቤጂንጎች ጋር ጠብ ሽኩቻቸዉን ቢያንስ ላጭር ጊዜ እስወግደዉ ለጋራ ጥቅም እንደጨዋ ተደራድሩ። እንደ ብልሕ ተስማሙ ።

ኢራን፤ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ

አያቶላሕ ሩሑላሕ ሆሚኒ የመሯቸዉ የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች በ1979 (ዘመኑ በሙሉእንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የንጉስ መሐመድ ሬዛ ሻሕ ፓሕላቪን አገዛዝ አስወግደዉ የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስና ኢራን ያልተወዛገቡ፤ያልተዛዛቱ፤ ያልተሻኮቱ፤ ያልተጋደሉ ያላጋደሉበት ዘመን የለም።

ከታጋች-አጋችቾ ድራማ እስከ ኢራን-ኢራቅ ጦርነት፤ ከፍልስጤም-እስራኤል ግጭት እስከ እስራኤል ሊባኖሶች ዉጊያ፤ ከአሜሪካ መራሹ የኢራቅ ወረራ እስከ -ሶሪያ ጦርነት፤ አሁን ደግሞ በየመኑ ጦርነት አልፎ አልፎ በቀጥታ፤ ሁል ጊዜ በተዘዋዋሪ የየሐገሩን ወይም የየአካባቢዉን ተቀናቃኝ ሐይላትን መደገፍ፤ ጠበኞችን ማጋጨት፤ የተጋጩትን ማጋደል የቴሕራን ዋሽግተኖች ጥቅም ማስከበሪያ ሥልት ነዉ።ሰላሳ ስድስት ዘመን።

የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር የሁለቱ ሐገራትና የየወዳጆቻቸዉ ፖለቲከኞች የርዕዮተ-ዓለማዊ፤ ፖለቲካዊና ስልታዊ ጠላትነታቸዉ አንዱ ምክንያት እንጂ በርግጥ የጠላትነታቸዉ መሠረት አይደለም።መሠረታዊዉን «ጠላትነት» ለማባስ፤ ምናልባትም በቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ዘመን እንደተሞከረዉ ቀጥታ ጦርነት ለመለኮስ ግን በቂ ሰበብ ነበር።ነዉም።

ሩሲያ፤ ዩናይትድስ ስቴትስና ምዕራብ አዉሮጳ

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የወዳጅነት መንፈስ ተላብሶ የነበረዉ የሩሲያ፤የዩናይትድ ስቴትስና የምዕራብ አዉሮጶች ግንኙነት በሶሪያዉ ጦርነት ሰበብ መደፍረስ ጀምሮ፤ በዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ ምክንያት ወደ ቅጣት-ዉግዘት፤ ወደ ዛቻ ፉከራ ንሮ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመንን መልክና ባሕሪ ይዟል።

ቻይና፤ ዩናይትድ ስቴትስና ምዕራብ አዉሮጳ

ማኦ ዜዱንግ የመሯቸዉ የቻይና ኮሚንስቶች ሕዝባዊት ሪፕብሊክ ቻይናን ከመሠረቱ ከ1949 ወዲሕ የኮሚንስት ካፒታሊስቱን ጠብ የተቀየጠችዉ ቻይና ከዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ስቴትስ ከምትመራቸዉ መንግሥታት ጋር ሠላም ሆና አታዉቅም።

የቤጂንግ-ዋሽግተን-ብራስልስ ፖለቲከኞች ከኩሜንታግ-ኮሚንስቶች ዉጊያ፤ እስከ ታይዋን-ቻይናዎች ግጭት፤ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር ጦርነት እስከ ቬትናም መወረር፤ ከሲኖ-ጃፓን እስከ ሲኖ-ሕንድ ዉዝግብ የዘለቀዉ ጠብ ዛሬም በኮሪያ ልሳነ ምድር ዉጥረት ሰበብ ሞቆ እየቀዘቀዘ ለሑዋይ-አፐል የንግድ ሽኩቻ ተርፏል።

ኢራን፤ ምሥራቅና ምዕራቦች

የኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ ምዕራባዉያን መንግሥታት፤ የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ISIS የተሰኘዉን አሸባሪ ቡድንን በጋራ ለመዉጋት ያልተፈራረሙት ስምምነት፤ ያላወጁት ግንባር ፈጥረዋል።ወይም ለመፍጠር ተገደዋል።ለነባር መርሕ፤ አቋም ተገዢዎች ግር የሚያሰኘዉ «ትብብር» ግን ለጊዚያዊ ጥቅም ከመቻቻል ባለፍ የአያቶላሕ ሆሚንዋን ትልቅ ሰይጣን ከፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽዋ የሰይጣን መዘዉር (ዛቢያ)ጋር የሚያስታርቅ አይደለም።

ከ1979 ጀምሮ ዋሽግተን፤ ለንደን ብራስልሶች ፊታቸዉን ያዙሩባት ኢራን ሠልፏን ከምሥራቆቹ ጋር አለማስተካከል አትችልም ነበር።የዲፕሎማሲ፤የጠመንጃ ቤንዚን ሽያጩ ወዳጅነት በሶሪያና በዩክሬን ጦርነቶች ሰበብ የምስራቅ-ምዕራቦቹ ልዩነት ሲሰፋ ይበልጥ ተጠናክሯል።

ድርድርና ዉጤቱ

በየዘመኑ፤በየአካባቢዉ፤ በየምክንያቱ የሚወዛገቡ፤ የሚሻኮቱ፤ የሚዛዛቱ፤ እንዳዴም የሚጋጩት ተቀናቃኝ መንግሥታት በጠብ ቁርቁሳቸዉ መሐል እንደ ፖለቲካዉ ወግ ድርድርን አላቆሙም።በተለይ የኢራን የኑኬሌር መርሐ-ግብር የየዉዝግብ ጠቡ አቀጣጣይ ከምሱር ከሆነ ወዲሕ እየተቀጣጡ፤እየተዛዛቱእየተጋደሉ፤ እያጋደሉም ደርድሩን አላቋረጡም።እስራ-ሁለት ዓመት።

ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ተስማሙ።ሉዛን ሲዊዘርላንድ።«ዛሬ ወሳኝ እርምጃ ወስደናል።ለአጠቃላዩ የጋራ የድርጊት መርሐ-ግብር በሚረዱ ቁልፍ ጉዳዮች መፍትሔዎች ላይ ተስማምተናል።ከዚሕ ያደረሰን የሁሉም ወገኖች ፖለቲካዊ ፅናት፤መልካም ፈቃድና ብርቱ ሥራ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ሁሉም መልዕክተኞች ላሳዩት ያላሰለሰ ፅናት እናመስግናቸዉ።ይሕ (ስምምነት) ከዚሕ ቀደም ለተደረገዉ የመጨረሻ አጠቃላይ የድርጊት መርሐ ግብር መሠረት የሚጥል ነዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ወይዘሮ ፌደሪካ ሞሕግሪኒ።ኢራኖች በአደባባይ ፈነደቁ።ማዕቀብ ሊነሳ ነዉ።መሪዎቻቸዉን አወደሱ።እንዲሕ እንደ ድሕረ-1979ኙ የኢራን አብዮት የመሪና የርዕዮተ-ዓለም ለዉጥ ከማምጣቱ፤ በዉጤም የቴሕራን ዋሽግተኖች ወዳጅነት በጠላትነት ከመለወጡ በፊት ኑክሌርን ለኢራን ያስተዋወቀችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።በ1950ዎቹ «አቶሚክ ለሠላም» በሚል መርሕ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢራን የሐይል ማመንጪያ ተቋም ማስገባት ጀምራ ነበር።

የኑክሌር ተቋም ግንባታዉን ያቋረጠችዉ ደግሞ ማንም ሳይሆን እራስዋ ኢራን ነበረች።የመጀመሪያዉ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሪ አያቶላሕ ሩሑላሕ ኾሚኒ የኑኬሌር ተቋሙ ጦር መሳሪያ ሊመረትበት እንደሚችል ሲያዉቁ «እንዲሕ አይነት መሳሪያ በእስልምና ሐራም ነዉ» ብለዉ አስቆሙት።ከሆሚኒ ሞት በሕዋላ ግን የኾሚኒ ተከታዮች እስራኤልን ጨምሮ ብዙ ሐገራት ያን አጥፊ ቦምብ መታጠቃቸዉን ሲሰሙ የመሪያቸዉን ዉግዘት አፍርሰዉ ለሠላም ያሉትን የኑክሌር መርሐ ግብር ቀጠሉ።

ከምዕራባዉያን ጋር ወትሮም ያልቀዘቀዘዉ ጠብ-ሽኩቻም ባሰ።ባለፈዉ ሳምንት ግን ጠቡ ባይጠፋ በረደ።በቀደም ቴሕራን ሲገቡ-ከአዉሮፕላን ማረፊያ እስከ መሐል ከተማ ሕዝባቸዉ በሆታ-እልልታ-የተቀበላቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጀዋድ ሳሪፍከሉዛን ከመነሳታቸዉ በፊት «ማንም የማይፈልገዉን አንፈልግም» አሉ።ከሁሉም በላይ ከተፈለገ ክብርን በጠበቀ ድርድር የማይፈታ ችግር የለም።

«እርምጃዎቻችንን ገቢር ሥናደርግ በእስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን ላይ ምንም አይነት ማዕቀብ አይኖርም።ይሕ በኔ እምነት ታላ ቅ እመርታ ነዉ።ለማንም የማይጠቅመዉን፤ለአዉደማዊ ጦር መሳሪያ አጋጁ ስምምነት የማይጠቅመዉን፤ጉዳዩ ለሚመለከታቸዉ ወገኞች፤ ለማንም የማይጠቅመዉን ዑደት አቁመናል።በዚሕ ሒደት መጨረሻ በድርድርና ክብርን በጠበቀ ግንኙነት ችግሮችን ማስወገድ ፤ አድማስን መክፈት፤ እና ወደፊት መራመድ እንደምንችል እናሳያለን።»

ከዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ቀኝ አክራሪዎቹ የቲፓርቲና የሪፕብሊካን ፓርቲ አባላት በሰምምነቱ አለመደሰታቸዉ አይቀርም።የዋሽግተን መሪዎች ደስታ ግን ከቴሕራን ፖለቲከኞች ያነሰ አይደለም።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ።«ዛሬ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከወዳጆችዋና ተባባሪዎችዋ ጋር ሆና ከኢራን ጋር ታሪካዊ መግባባት ላይ ደርሳለች።ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ከሆነ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ ያግዳታል።እንደ ፕሬዝዳንትና የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥነቴ የአሜሪካንን ሕዝብ ፀጥታና ደሕንነት ከማስጠበቅ የበለጠ ሐላፊነት የለብኝም።ይሕ የመግባቢያ ስምምነት ከመጨረሻዉ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ከደረሰ ሐገራችንን፤ ወዳጆቻችንን እና ዓለማችንን ይበልጥ አስተማኝ ያደርጋቸዋል።»

ከሶማሊያ እስከ የመን፤ ከደቡብ ሱዳን እስከ ኬንያ፤ከኮንጎ እስከናይጄሪያ፤ ከማሊ እስከትሪፖሊ፤ ከጋዛ እስከ ሲና፤ ከሶሪያ እስከ ኢራቅ፤ ከአፍቃኒስታን እስከ ከዩክሬን ከጦርነት፤ ሽብር ፀረ ሽብር ግድያ ሌላ በጎ ነገር ለማይሰማዉ ዓለም ሥምምነቱ የሩቅ እና ትንሽም ቢሆን በርግጥ ተስፋ ነዉ።

ተስፋ እዉን መሆን አለመሆኑ የሚታወቀዉ ደግሞ የኢራንም፤የዋሽግተንም ፖለቲከኞች በየፊናቸዉ እንዳሉት ገቢራዊ ሲሆን ነዉ።በሎዛኑ ድርድር-ስምምነት የተካፈሉት የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሎራ ፋቢዮስ እንዳሉት ግን ተደረራዳዊዎች ከዚሕ ስምምነት መድረሳቸዉ ራሱ ታላቅ እርምጃ ነዉ።«ይሕ ስምምነት ያለምንም ጥርጥር መልካም ጉዳዮችን ያካተተ የመሠረት ድንጋይ ነዉ።ይሁንና አሁንም ብዙ ሥራ ይቀረናል።ምክንያቱም እስከ ሰኔ ሠላሳ ብዙ ነገሮችን ማጠናቀቅ አለብንና።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይን ማየር በፋንታቸዉ ድፍን አስራ-ሁለት ዓመት አላላዉስ ያለዉ እንቅፋት ተወገደ ነዉ-ያሉት።የስምምነቱ አስደሳችነት አያጠራጥርም።

«(ስምምነቱ) አንድ ታላቅ ርምጃ ወደፊት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም።አሁን የተወገዱት እንቅፋቶች እስካሁን ሁነኛ ስምምነት እንዳይደረግ ቢያንስ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ሁሌም አደናቃፊ የነበሩ ናቸዉ።እንደሚመስለኝ እስካሁን ያለዉ ዉጤት አስደሳች ነዉ።»

ከዩናይትድ ስቴትስ፤ከፈረንሳይ እና ከጀርመን ጋር አምስት ሲደመር አንድ የተሰኘዉ ቡድን የሚያስተናብራቸዉ የብሪታንያ፤ የሩሲያና የቻይና ፖለቲከኞችም በስምምነቱ መደሰታቸዉን አልሸሸጉም።የአንዲት ሐገር አንድ መንግሥት ፖለቲከኞች ግን በስምነቱ ተከፍተዋል።የዩናይትድ ስቴትስና የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት የቅርብ ወዳጅ የእስራኤል ፖለቲከኞች።ቃል አቀባይ ማርክ ሬጌቭ እንዳሉትማ ስምምነቱ ወደ አደገኛ አቅጣጫ የሚያጉዝ ነዉ።

«ይሕ የመግባቢያ ዉል ወደ በጣም፤በጣም አደገኛ አቅጣጫ የሚያመራ እርምጃ ነዉ።ኢራን በጣም ዉድ ከሆነ የኑክሌር መዋቅሯ ጋር እንድትቀጥል የሚያደርግ ነዉ።ከኢራን የኑክሌር አንዱንም እንኳ አያዘጋም።ኢራን ዩራኒየም ማብላላቷን፤ በሺሕ የሚቆጠሩ ማብላያዎችዋን እንደያዘች እንድትቀጥል የሚያደርግ ነዉ።ከዚሕ በተጨማሪ ኢራን የተሻለ ማብላያ እንዲኖራት የምታደርገዉን ምርምር እንድትቀጥል የሚፈቅድ ነዉ።»

በ1972 የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ሞስኮ ድረስ ተጉዘዉ ከያኔዉ የሶቬት ሕብረት መሪ ሊዮኒድ ቭሬዥኔቭ ጋር የመጀመሪያዉን የሥልታዊ ጦር መሳሪያ እነሳ ስምምነት ተፈራርመዋል።ሶልት አንድ።በ1987 የያኔዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ዋሽግተን ድረስ ተጉዘዉ ከያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ጋር የኑክሌር ጦር መሳሪያ ዉል ተፈራርመዋል።ዉል ስምምነቱ ለዓለም ሠላም አደገኛ ከነበረ ካሁኑ ስምምነት ይልቅ የያኔዉ ሲበዛ አደገኛ በሆነ ነበር።አልሆነም።ካንዲት ደካማ ሐገር ጋር የተደረገዉ ያሁኑ ስምምነት ፕሬዝዳንት ኦባማ እንዳሉት ከእስካሁኑ አስጊ የሚሆንበት ሰበብ ምክንያት በርግጥ ግራ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic