የኢራቅ ወረራና ብሌር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢራቅ ወረራና ብሌር

የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ብሪታንያ ያለተጨባጭ መረጃ እና ያለ በቂ እቅድ በጎርጎሮሳውያኑ 2003 ዓ,ም በተካሄደው በኢራቁ ጦርነት እንድትሳተፍ አድርገዋል ሲል ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ኮሚቴ አስታውቋል። ኮሚቴው ሰላማዊ አማራጮች በሙሉ ሳይሞከሩ ብሪታንያ በወረራው ለመካፈል መስማማቷን አጋልጧል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:46

የኢራቅ ወረራና ብሌር

«ሚስተር ብሌየር ወታደራዊዉ ርምጃ አልቃይዳ በብሪታኒያ እና በብሪታኒያ ፍላጎት ላይ ስጋቱን ከፍ እንደሚያደርገዉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዉ ነበር። በተጨማሪም ወረራዉ የኢራቅ መሣሪያም ሆነ አቅም ወደአሸባሪዎች እጅ እንዲገባ ሊያደርገዉ እንደሚችልም ተነግሯቸዉ ነበር። አሁን ኢራቅ ላይ የነበረዉ መመሪያ ባልተጨበጠ የስለላ መረጃ እና ቅኝት ላይ የተመሠረተ እንደነበር ግልፅ ሆኗል።»
በዛሬ 13 ዓመቱ የኢራቁ ወረራ የብሪታንያን ሚና የመረመረው አጣሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሰር ጆን ቺልኮት ከኢራቁ ወረራ በፊት የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ስለተሰጣቸው ማሳሰቢያ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የሰጡት መግለጫ ነበር። በተጀመረ በ7 ዓመቱ ይፋ የሆነው፣ የምርመራው ውጤት ቶኒ ብሌር ሃገራቸው በኢራቅ ወረራ እንድትካፈል ያደረጉት በቂ መረጃ ሳይገኝ እና ከወረራው በኋላም ሊሆን ስለሚችለው ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ መሆኑን አጋልጧል። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ሰኔ 15፣ 2009 ዓ,ም የዚያን ጊዜው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ምርመራዉ እንደሚካሄድ ባሳወቁት መሠረት ለዚሁ ተግባር የተቋቋመው ኮሚቴ በኅዳር 2009 ዓ,ም ነበር በይፋ ምርመራውን የጀመረው። አቶ ኢታና ሀብቴ በለንደን ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ የእስያ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናቶች ትምህርት ቤት የPHD ተማሪ እና የታሪክ ምሁር ናቸው። ኮሚቴው ምርመራውን የጀመረው ሁለት ጥያቄዎችን በማንሳት እንደነበረ ያስታውሳሉ።


መርማሪው ኮሚቴ ይፋ ያደረጋቸው ደብዳቤዎች እንደሚያስረዱት የሌበር ፓርቲው ብሌር በኢራቅ የመንግስት ለውጥ መደረጉን እንደሚደግፉ ለቡሽ ያረጋገጡላቸው ወረራው በመጋቢት 2003 ዓም ከመጀመሩ ከ8 ወራት አስቀድሞ ነበር። በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 28 ፣2002 ዓ,ም ብሌር ለቡሽ በጻፉት ሚስጥራዊ ደብዳቤ «ምንም ይሁን ምን ከጎንህ ነኝ»ሲሉ ቃል ገብተውላቸው ነበር ።ብሌር ለቡሽ ይህን ቃል እየገቡ ለብሪታንያ ህዝብ እና ለፓርላማው ግን በጦርነቱ የመካፈል ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ አልተደረሰም እያሉ ይናገሩ እንደነበረ ነው የምርመራው ውጤት ያጋለጠው። ብሌር የያኔው የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን ለሰላም አስጊ መሆናቸውን በማጉላት የህዝብ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉም እርግጠኛ መሆናቸውን ለወዳጃቸው ለቡሽ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸውላቸው ነበር። የሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች ማስረጃዎች ፣ የኒዩክልየር አቅም ለማዳበር የሚያደርጉት ሙከራ እና ከአልቃይዳም ጋር ያላቸው ግንኙነት ሲጨመር ህዙብን ለማሳመን እንደሚረዳም ሃሳብ አቅርበው ነበር። ከዚህ ሌላ ብሌር ወረራው ከመጀመሩ ከሁለት ወራት በፊት ከፍተኛ ሚኒስትሮቻቸውን ሳያማክሩ በግል 3 ብርጌድ ተዋጊ ጦር ለማዝመት መስማማታቸውንም የቺልኮት ዘገባ ይፋ አድርጓል ።በዚሁ ዘገባ መሠረት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሉዓላዊ ሃገር ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ ወረራ ለመካፈል ብሌር መወሰናቸው የመጨረሻው አማራጭ አልነበረም። የታሪክ ምሁሩ አቶ ኢታና ሀብቴ መርማሪው ቡድን የደረሰበት መደምደሚያ ሦስት ዋና ዋና ሃሳቦችን አካቷል ይላሉ።


ሳዳም አላቸው የተባለው ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ኢራቅ ውስጥ አልተገኙም። የማይቀር ስጋት ናቸው የተባሉት ሳዳም ሁሴንም እንደተባለው እንዳልሆኑ የምርመራው ውጤት አስታውቋል። በርግጥም ብሌር አይናቸውን ጨፍነው ያለ ተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትም ሆነ ያለ ኔቶ ይሁenta የገቡበት የኢራቁ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላስገኘም ።ኢራቅ የዘመተው የብሪታንያ ጦር ከ6 ዓመት በኋላ በ2009 ዓ,ም ሃገሪቱን ለቆ ሲወጣ ጦርነቱ ከ150 ሺህ በላይ ኢራቃውያን ፣4500 አሜሪካውያን እንዲሁም 179 ብሪታንያውያን ገድሏል። ብሪታንያ ብቻ ለጦርነቱ ከ12 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥታለች። በወቅቱ የብሌር ምክትል የነበሩት ጆን ፕሬስኮት ብሪታንያ በ2003 ዓ,ም በኢራቅ ያካሄደችው ወረራ ዓለም ዓቀፍ ህግን የጣሰ ነበር ሲሉ ባለፈው እሁድ ባወጡት ጽሁፍ አስታውቀዋል። አሁን ስለወረራው ሃሳባቸውን እንደቀየሩ የሚናገሩት ፕሪስኮት ህጋዊ መሆን አለመሆኑ ውይይት ሳይካሄድበት ወደ ጦርነት መገባቱ አግባብ አልነበረም ሲሉ ተችተዋል። የተቀድሞ የተመድ ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን የኢራቅ ወረራ ዋነኛ ዓላማ የመንግሥት ለውጥ ማድረግ እንደመሆኑ ህገ ወጥ ነው ብለው ነበር። ያኔ ሃሳቡን የተቃወሙት ፕሬስኮት አሁን ግን በታላቅ ሃዘን እና በንዴት ኮፊ አናን ትክክል ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ቶኒ ብሌር በአሜሪካ መራሹ የኢራቅ ወረራ ለተፈጸሙ ስህተቶች ከ9 ወራት በፊት ይቅርታ ጠይቀዋል ።በተለይ ሳዳም ከተወገዱ በኋላ ምን መደረግ እንደሚገባው በተገቢው ሁኔታ ላለመታቀዱም ጭምር። ይሁንና ባልተጨበጠ መረጃ እና በወጉ ሳይታቀድ ብሪታንያ 45 ሺህ ወታደሮችን ኢራቅ እንድታዘምት ያደረጉት ብሌር ለፍርድ

እንዲቀርቡ የሚጠይቁ ጥቂት አይደሉም ። እነዚህ ወገኖች «አሸባሪ » የሚሏቸው ብሌር በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ነው ፍላጎታቸው። ባሉት ማስረጃዎች ለስህተቱ ዋነኛውን ሃላፊነት ይወስዳሉ የሚባሉት ብሌርም ሆነ ሌሎች በወቅቱ የነበሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች በወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አቶ ኢታና ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ በርሳቸው አስተያየት በብሪታንያ የውጭ ግንኙነት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ሊያስከትል ይችላል።
ከጎርጎሮሳዊው 1997 እስከ 2007 ዓም ሥልጣን ላይ የቆዩት ቶኒ ብሌር ለድርጊቱ ሙሉ ኃላፊነትን እንደሚወስዱ ነው የገለፁት። የቺልኮት ዘገባ በወጣበት እለትም በሆነው ሁሉ እንደሚያዝኑ እንደሚጸጸቱ እና ይቅርታም እንደሚጠይቁ ብሌር ተናግረዋል ። ከዚህ ቀደም እንዳሉት በኢራቅ ወረራ ለመሳተፍ የወሰኑት አምነውበት ነው።
«ይህ የሀሰት፤ የማጭበር በር ወይም የመመሳጠር ሳይሆን ጉዳይ ሳይሆን ዉሳኔ ነዉ። መወሰን ነበረብኝ፤ አምኜበት በመጨረሻም ምክር ቤቱም ሆነ ካቢኔዉ ሊከተል የሚችለዉን መዘዝ ችላ አለማለቱ ትክክል ነዉ።»
ከ7 ዓመት በኋላ ይፋ የሆነው «በኢራቅ ወረራ የብሪታንያ ሚናን የመረመረው ዘገባ ለምዕራቡ ዓለምም ሆነ ለአፍሪቃ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብዙ ትምሕርት የሚሰጥ መሆኑን አቶ ኢታና አስረድተዋል ።
አድማጮች ለአውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን አስተያየት ጥቆማም ሆነ ጥያቄ ካላችሁ በኤሜል ፣በፌስቡክ በSMS እና በዋትስአፕ አድራሻዎቻችን እንዲሁም በደብዳቤ ላኩልን እናስተናግዳለን። በስልክም መልዕክቶቻችሁን መተው ትችላላችሁ ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic