የኢራቁ ጦርነትና የጀርመን ኩባንያዎች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢራቁ ጦርነትና የጀርመን ኩባንያዎች

የኢራቁ ውጊያ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎችንም ከሃገር እያስወጣ ነው ። በጦርነቱ ሃገር ለቀው እንዲወጡ ከተገደዱት ውስጥ የጀርመን ኩባንያዎች ይገኙበታል ።

ከሁለት ሳምንት ወዲህ ውጊያ ተጠናክሮ ከመቀጠሉ በፊት ኢራቅ የውጭ ባለሃብቶች ተስፋ የጣሉባት ለውጭ ኩባንያዎች በርዋን በሰፊው ከፍታ የምትጠብቅ ሃገር ነበረች ተረጋጋች ተብሎ የአሜሪካን ወታደሮች ሃላፊነቱን ለኢራቅ ጦር ኃይል አስረክበው ምርጫም ተካሂዶ መንግሥት ቢመሰረትም የሰላሙ ተስፋ ተስፋ ሆኖ የቀረ ነው የሚመስለው እንደገና ያገረሸው ጦርነት የዜጎችን ህይወት ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ ማመሰቃቀሉ ቀጥሏል እስከዛሬ በዚህች ምድር ያለቀው ህዝብ ሳያንስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብዙዎች ተገደልዋል ተሰደዋል። የኢራቅ ሰላም መደፍረስ ሃገሪቱን ከሌላ አቅጣጫም እየጎዳ ነው ባለፉት ዓመታት የውጭ ባለሃብቶች በኢራቅ የነበራቸውን ተስፋ በሃገሪቱም መታየት የጀመረውን ለውጥ ከነአካቴው ደብዛው እንዲጠፋ እያደረገ በመሄድ ላይ ነው ሰላም ከሌለ ሰርቶ መግባት ያለ ሰላም ልማት አይታሰብምና በሃገሪቱ ሰላም መልሶ እንዲሰፍን ዜጎች ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ በተለያዩ ስራዎች የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶችም ምኞት ነው «በአሁኑ ጊዜ በኢራቅ የሚሆነው እጅግ አሳዛኝ ነው በበኩሌ በአንድ ወቅት ላይ የሰከነ ሁኔታና ሰላም ይሰፍናል ብዮ ተስፋ ማድረግ ብቻ ነው የምችለው እናም ያኔ ሃገሪቱ በእርግጠኝነት መልካም እጣ ፈንታ ይገጥማታል »

ኢራቅ ውስጥ በግንባታ ስራ የተሰማሩት የምዕራብ ጀርመን የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው የቬስል ከተማ ባለሃብት ኤርስት ዮአሂም ትራፕ ናቸው ስለ ኢራቅ የሚናገሩት ከልብ ተነክተው ነው የኤፍራጥስና የጤግሮስ ምድር በሆነው በኢራቅ እጎአ 1950 ዎቹ አንስቶ ከልጆቻቸው ጋር የሚያስተዳድሩት የቤተሰብ

ኩባንያ አላቸው ትራፕ መጀመሪያ ኢራቅ የሄዱት እጎአ 1952 ነው ያኔ 17 ዓመት ጎረምሳ ነበሩ በወቅቱም ኢራቅ የሄዱት የአባታቸው አስተርጓሚ ሆነው ነበር ።ከዚያን ጊዜ አንስቶ በጊዜ ሂደት እየጠበቀ ያደገው ግንኙነት በኢራቅ ለመሰረቱት ኩባንያ ንግድ እጅግ ጠቃሚ ነበር

« በቀጣይነት እጅግ ጠቃሚው ጉዳይ በሃገር ውስጥ የሚያውቅህ ጥሩ አጋር ማግኘቱ ነው በሃገር ውስጥ ያለው ሥልጣን በሼኮቹ እጅ ነው ይህ ደግሞ ለምዕተ ዓመታት እና አሁንም በዚያ መንገድ ነው የሚካሄደው ስለዚህ አንድ ሰው ከሼኮቹ ጋር ጥሩና የሰከነ ግንኙነት ካለው ንግዱ አስተማማኝ ይሆናል »

በዚህ አግባብ ነበረ የትራፕ የግንባታ ኩባንያ በምዕራብ ኢራቅዋ የአንባር ክፍለ ግዛት አንድ ፕሮጀክት የጀመረው ኩብንያው ፕሮጀክቱን የጀመረው የተነገረውን ምክር በመስማት ነበር 77 ዓመቱ ትራፕ እንደሚሉት አሁን ያጋጠማቸው ግን ፍፁም ያልተጠበቀ ጉዳይ ነው

«ከሁለት ዓመት በፊት እዚያ ስንጀምር ሶሪያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው ይህ አካባቢ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው ተብለን ነበር ይሁንና አሁን መንግስትን የሚወጉት ISIS በመባል የሚጠሩት የሱኒ አማጽያን ተቆጣጥረውታል »

ኩባንያቸው የሚያካሂዳቸው ግንባታዎች በተለየ አሠራር በኢራቃውያን ሠራተኞች ቀጥሏል ጀርመናውያን መሃንዲሶች ግን በፀጥታ ችግር ምክንያት ከአካባቢው ወጥተዋል ዚመንስና ሌሎችም ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ደህንነታቸው አስተማማኝ ወደ ሆኑ ስፍራዎች አሽሽተዋል አለያም ኢራቅን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል አንባር በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ግጭት ከሚካሄድባቸው ሶስት ክፍለ ግዛቶች አንዷ ናት የተቀሩት ሁለቱ ኔኔቭ ሳላዲን ናቸው ።ሽቴፈን ቤህም በጀርመን የኢንዱስትሪና የንግድ ምክር ቤት የመካከለኛው ምስራቅ የሰሜን አፍሪቃ ጉዳዮች አዋቂ ይህንኑ አረጋግጠዋል ምክር ቤታቸውም በነዚህ አካባቢዎች የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱና ሠራተኞቻቸውንም እንዲያስወጡ እየመከረ ነው

«ህንዳውያንና ቱርካውያን ሠራተኞች መታገታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች አሉ ይህም አካባቢው በአሁኑ ጊዜ አስተማማኝ እንዳልሆነና በማናቸውም ጊዜ አደገኛ ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በጣም ግልፅ ምልክት ነው »

የጀርመን የኢንዱስትሪና የንግድ ምክር ቤት ኢራቅ ውስጥ ሁለት ቢሮዎች አሉት አንዱ የራስ ገዝዋ የኩርዶች ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በኤርቢል ሌላው ደግሞ በዋና ከተማይቱ በባግዳድ ነው የሚገኘው ኤርቢል በርካታ የጀርመን ኩባንያዎች የሚገኙባት ከተማ ናት የምክር ቤቱ ኢራቃውያን ጠበብት የጀርመን ኩባንያዎች አስተማማኝ የንግድ አጋር ሲፈልጉ እገዛ ያደርጉላቸዋል ።የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትንም በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ያማክራሉ ።የጀርመን የኢንዱስትሪና የንግድ ምክር ቤት እንደሚለው በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ ኢራቅ ወይም በባግዳድ አለያም በባዝራ ቁጥራቸው 30 የሚሆን የጀርመን ኩባንያዎች አሉ በሰሜኑ የኩርድ ግዛት ደግሞ 40 የጀርመን ኩባንያዎች ይገኙበታል ።ሽቴፋን ቤም እንደሚሉት ኩባንያዎቹ በተለይ በዋነኛት በመሰረት ልማት አገልግሎት ማለትም በግንባታ ሥራዎች በጤና አገልግሎት በኤሌክትሪክ ማመንጨትና ማሰራጨት ዘርፍ ነው የሚሰሩት ።የጀርመን ኩባንያዎች ኢራቅ ውስጥ በብዛት መሰማራት የጀመሩትም ከዛሬ ስድስት ዓመት ወዲህ ነው በቅርቡ ደግሞ ቁጥራቸው እየቀነሰ ነበር

« እና ያየነው ምንድነው የጀርመን ባለሃብቶች ኢራቅ ውስጥ የመስራት ፍላጎታቸው እያደገ የመጣው እጎአ 2008 አንስቶ ነው ኢራቅ ላይ ይበልጥ ማትኮራቸው ቀጥሎ በጣም ጥሩ ውጤትም አስገኝቶ ነበር ሆኖም ባለፉት ሁለት ዓመታት የፀጥታው መደፍረስ እየተባባሰ በመሄዱ ፍላጎቱ ቀንሶ ነበር »

ሌሎች የአረብ አገራት ጋር ሲነፃፀር በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ኢራቅ ጀርመን በብዛት የውጭ ንግድ ገበያ የምታካሂድባት ስድስተኛዋ ሃገር ነበረች በዚሁ ዓመት ጀርመን ወደ ኢራቅ የላከችው የውጭ ንግድ 1.3 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 1.77 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ።ይህ ጀርመን በዚሁ ዓመት ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገበያ ካቀረበችው 10 ቢሊዮን ዩሮ ንግድ ወይም ወደ ሳውዲ አረቢያ ከላከችው 9 ቢሊዮን ዩሮ ገበያ ጋራ ሲነፃፀር ግን ያን ያህል ብዙ የሚባል አይደለም ሆኖም ቤም እንደሚሉት በረዥም ጊዜ ሲታይ ኢራቅ የጀርመንን ትኩረት የሚስብ ገበያ

የሚገኝባት ሃገር ናት ይህም በርሳቸው አስተያየት ሃገሪቱ የጀርመን ባለሃብቶችን ትኩረት የሳበችውበነዳጅ ዘይት ሃብት ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሃገር በመሆንዋ ብቻ አይደለም

« ኢራቅ 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አላት ይህ ገንዘብ የተያዘው በመሠረተ ልማት መስክ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ነው ለጊዜው ግን ይህን ገንዘብ ሥራ ላይ ማዋል ምክንያቱም የኢራቅ ምክር ቤት በሃገሪቱ የጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓመተ ምህረት በጀት ላይ መግባባት አልቻለምና »

በዚህ የተነሳም ባለፉት ጥቂት ወራት የተገነቡት ካለፉት ዓመታት የተገፉ ያላለቁ ፕሮጀክቶች ናቸው በሃገሪቱ ብሄራዊ በጀት ላይ መስማማት ከተቻለ ግን በርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ መዋል ይጀምራሉ በዚህ ጊዜም የጀርመን ኩባንያዎች እጅግ አትራፊ የሆኑ ውሎች ያገኛሉ ይህን እድል የሚያገኙት ግን በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን አመቻችተው ያስቀመጡት ብቻ ናቸው

« አሁን በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ማለትም ስራው በቆመበትም ጊዜ እዚያው የቆዩት ሁኔታው በተወሰነ ደረጃ ሲረጋጋ ወዲያውኑ መመለስ ይችላሉ አዳዲሶቹ ግን በፀጥታው ችግር መባባስ ምክንያት ወደ ኋላ ማለታቸው ይቀጥላል ብዬ ነው የምጠብቀው »

ወደ 62 ዓመት ኢራቅን የሚያውቋት እርነስት ዮአሂም ትራፕ ቤም ያሉትን ነው የሚደግሙት ።ወደፊትም በኢራቅ ይሄ ሊሆን ይችላል ብለው መተንበይ አይፈልጉም

«የሚሆነውን ባውቅማ ኖሮ የኦባማ ድንቅ አማካሪ በሆንኩ ነበር የኢራቅ ህዝብና መሪዎቹ በርግጥ አስተዋዮች መሆናቸውን አውቃለሁ አገሪቱን አንድ የሚያደርግ መፍትሄ ፈልገው የተሻለች ሃገር ይገነባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ »

ይህ የኢራቅን ሰላም የሚመኙ ሁሉ ምኞት ነው ይሁንና በኢራቅ በልዩ ልዩ የኢንቬስትመንት ስራዎች የተሰማሩ የምዕራባውያን ሃገራት ኩባንያዎች በሃገሪቱ ለሚካሄደው ውጊያ በእጅ አዙርም ቢሆን አስተዋፅኦ በማድረግ ከመተቸት አላመለጡም ኩባንያዎቹ ከሚወቀሱባቸው ተግባራት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሃገሪቱ የሚያስገቧቸው የጦር መሣሪያዎች በተዋጊዎች እጅ እንዲወድቁ ማድረግ ይገኝበታል ይህና ሌሎችም ምዕራባውያን ኩባንያዎች ተጠያቂ ናቸው የሚባሉባቸው እርምጃዎች ሃገሪቱ ከጦርነት እንዳትላቀቅ ተብትበው ከያዟት መሰናክሎች ውስጥ እንደሚደመሩ ታዛቢዎች ይናገራሉ

የኢራቅ ውጊያ በጀርመን ኩባንያዎች ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ያስቃኛችሁ የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አበቃ አድማጮች ለአውሮፓና ጀርመን ዝግጅት ጥቆማ ጥያቄ እንዲሁም አስተያየት ካላችሁ በኢሜል SMS እንዲሁም በፌስ ቡክ ፃፉልን እናስተናግዳለን

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic