የኢራቁ ምክርቤታዊ ምርጫና ፍጥጫ | ዓለም | DW | 05.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢራቁ ምክርቤታዊ ምርጫና ፍጥጫ

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከኢራቅ ጠቅልሎ ከወጣ በኋላ የመጀመሪያውን ምክር ቤታዊ ምርጫ ኢራቃውያን ረቡዕ፤ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2006 ዓም አከናውነዋል። በከፍተኛ ጥበቃ ነው የኢራቅ ምርጫ የተከናወነው። በኢራቁ ምርጫ ለመምረጥ ከተመዘገበው ነዋሪ ሲሦው ድምፁን መስጠቱም ተገልጿል።

ዘወትር የፈንጂ ጥቃት የሰው ሕይወት የሚቀጥፍባት፣ ብሎም ንብረት የሚያወድምባት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ የሽብር ቃጣና ከሆነች ሰነባብታለች፤ ኢራቅ። በዘመነ-ሣዳም ሁሴን በአሜሪካኖች ልዩ ድጋፍ የተደረገላት፣ በዘመነ-ሣዳም ሁሴን በአሜሪካኖች ድባቅ የተመታች፤ ዛሬ ግጭት የማያጣት ሀገር ሆናለች፤ ኢራቅ። በፈንጂ ጥቃት ስጋት ተሸብባም ቢሆን በእዚህች በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል በምትገኝ ጥንታዊት ሀገር ከ20 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ድምፅ ሰጥተዋል። ከ100 በላይ የፓርቲ ጥምሮች ከ9000 የማያንሱ ዕጩዎቻቸውን ለምርጫ አቅርበዋል። ተፎካካሪዎቹን 328 የምክር ቤት ወንበሮች ይጠብቃቸዋል።

ኧል ማሊኪ።

«በእዚህ አጋጣሚ መላው ኢራቃውያን በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ። ምክንያቱም ድምፁን የሰጠ የምርጫ መብቱን ያስጠብቃል፤ ያልሰጠ ያ መብት ይቀርበታል። እኔ በበኩሌ የምርጫ መብቱን ያጣ ዜጋ መሆን አልሻም።»

ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪ ድምፅ ሲሰጡ

ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪ ድምፅ ሲሰጡ

የምርጫ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ የተናገሩት የሺዓ እስልምና እምነት ዘርፍ ተከታይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪ ነበሩ። በመዲናዋ ባግዳድ ሆነም በአንዳንድ የሀገሪቱ አውራጃዎች ምርጫው በሚከናወንበት ዕለት ማንኛውም ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተጥሎበት ነበር። የዓየር ማረፊያው ሳይቀር ተዘግቶ ነው የዋለው። አሸባሪዎች በስፋት ይንቀሳቀሱበታል በተባለው የሀገሪቱ ትልቁ አውራጃ፤ አንባር ውስጥ ምርጫው በፀጥታ ስጋት የተነሳ ሳይከናወን ቀርቷል። በእርግጥ አንባር ቀደም ሲል ከኧልቃይዳ ነጻ ወጥታ ነበር። የኧልቃይዳው የቀድሞ መሪ ዖሳማ ቢን ላደን መገደሉ ከተነገረ ከሦስት ዓመታት በኋላም ቢሆን ግን ኢራቅ ዛሬም የስጋት ቃጣና ናት።

የኧልቃይዳው መሪ ዖሳማ ቢን ላደን ፓኪስታን አቦታባድ የተሰኘችው ከተማ ውስጥ በመሸገበት ቅፅሩ በዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ወታደራዊ ኃይል መገደሉ ከተነገረ ያሳለፍነው አርብ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁንም ድረስ ግን ኢራቅ ከኧልቃይዳ ደጋፊዎችና ጥቃት ነፃ የሆነችበት ጊዜ እምብዛም ነው። ተመራማሪና አሸባሪዎችን መልሶ የማጥቃት ሊቅ የለንደን ነዋሪው ጃፋር ሁሴን ኧልቃይዳ ከፓኪስታን ወጥቶ አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ቅርንጫፉን ዘርግቷል ይላሉ።

ምክር ቤታዊ ምርጫ በኢራቅ፤ ድምፅ ቆጠራ

ምክር ቤታዊ ምርጫ በኢራቅ፤ ድምፅ ቆጠራ

ጃፋር ሁሴን

«መላው ዓለምን ብትመለከት፤ ናይጀሪያ፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ ግብፅና ኢራቅ ውስጥ የሚሆነውን ብታይ ኧልቃይዳ ዓለምአቀፍ እንቅስቃሴው አልተዳከመም»

በእርግጥም ኧልቃይዳ ኢራቅን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ ይስተዋላል። የሶማሌው ኧልሸባብና የናይጄሪያው ቦኮ ሐራም የተሰኙት አሸባሪ ድርጅቶች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች አሁንም ድረስ አልተቋረጡም። በርካታ የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት የኧልቃይዳው መሪ ዖሳማ ቢን ላደን ተገደለ ቢባልም ምክትሉ አይማን ኧልዛዋሪ ፓኪስታን ውስጥ እንደ ቀድሞው አለቃው ሳይመሽግ አይቀርም ይላሉ። በእርግጥ ኧልዛዋሪ ከዕድሜው መግፋት አንፃር ኢራቅ ውስጥም ሆነ በተለያዩ ሃገራት ኧልቃይዳን አሰማርቶ የማስተባበር ብቃቱ ይኖረዋል? የደኅንነት ጉዳይ ተንታኞች ይጠራጠራሉ።

የጤግሮስ ወንዝ ዕይታ ከባግዳድ ሆቴል

የጤግሮስ ወንዝ ዕይታ ከባግዳድ ሆቴል

ሆኖም ኧልዛዋሪ ከትናንት በስትያ ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክቱ ኢራቅ የሚገኙ የኧልቃይዳ ታጣቂዎች ጎረቤት ሶሪያ ገብተው እርስ በእርስ በመዋጋት «የፖለቲካ ድቀት» ከማስከተል መቆጠብ አለባቸው ብሏል። ከእዚያ ወጥተውም ኢራቅ ውስጥ ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስቧል። የኢራቁ ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪ የሚከተሉት የሺዓ እስልምና እምነት ዘርፍ በኧልቃይዳ ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። የሺዓ እስልምና እምነት ዘርፍ በኢራቅ ጎረቤት ኢራን ውስጥ የበላይነት እንዳለው ይጠቀሳል። የአሁኑ የኢራቅ ጠቅላይ ሚንሥትር የቀድሞው የ«ኢስላሚክ ዳዋ ፓርቲ» መሪ ኑሪ ኧል ማሊኪና የፓርቲ አባላቶቻቸው በኢራቅ-ኢራን ጦርነት ወቅት የኢራን አብዮትንና የኢራኑ አያቶላህ ሮሁላህ ካሆሜኒን በይፋ ይደግፉ ነበር። አሁንም ድረስ ፓርቲው ከኢራን የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግለት ይነገራል።

የኧልቃይዳው መሪ ኧልዛዋሪ፤ የሶሪያው ፕሬዚዳንት አሳድን አሸንፎ ከሥልጣን ማስወገድ ማለት ከግማሽ በላይ የሆነውን የኢራን ሺዓ ደጋፊ አካል ማዳከም ነው ብሎ ያምናል። የሶሪያ መንግሥት ከአፍጋኒስታን እስከ ደቡብ ሊባኖስ የሺዓ የእስልምና እምነት ዘርፍ ሥልጣን ላይ እንዲወጣ መጣሩ መገታት አለበት በሚል ኧልቃይዳዎች እንደሚወጉት ይነገራል። ሆኖም ግን የኧልቃይዳ ታጣቂዎች ለጊዜው ኢራቅ ውስጥ ትኩረት አድርገው በሺዓ ተከታዮች የሚመራውን መንግሥት እንዲገረስሱ ኧልዛዋሪ አሳስቧል። ኢራቅ በዚህ ውጥረት ውስጥ ሆናም ነበር ሰሞኑን ምክርቤታዊ ምርጫውን ያካሄደችው።

የኢራቅ መራጭ ወታደሮች ለመምረጥ ተራ እየጠበቁ

የኢራቅ መራጭ ወታደሮች ለመምረጥ ተራ እየጠበቁ

በኢራቁ ምክርቤታዊ ምርጫ ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪም ሆኑ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ዓማር ኧል ሐኪም የምርጫ ውጤቱ ተቆጥሮ ሳይጠናቀቅ ገና ከወዲሁ በየፊናቸው ማሸናፋቸውን ይፋ አድርገዋል። የሺዓ ፓርቲዎች ጥምረት አባላት የሆኑት ዓማር ኧል ሐኪምና ሞክታዳ ኧል ሣዳር ጥምረት ውስጥ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንሥትር ኑሪ ኧል ማሊኪን መፎካከራቸው ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ለሚወዳደሩት ጠቅላይ ሚንሥትሩ ራስ ምታት ነው የሆነባቸው። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ከጥምረቱ ተጓዳኝ ለማግኘት ያዳግታቸዋል እየተባለ ነው። ኑሪ ኧል ማሊኪ ከወዲሁ አብላጫ ድምጽ እንዳገኙ እየተነገረ ቢሆንም በሥልጣናቸው ለመቆየት ግን የግድ ፊታቸውን ወደ ሱኒ ፓርቲዎች አለያም ኩርዶች ማዞር ይጠበቅባቸዋል።

የኢራቁ የቀድሞ መሪ ሣዳም ሑሴን በአሜሪካኖች ወታደራዊ ዘመቻ እጃቸው ከተያዘና በኋላ ላይም እዛው ኢራቅ ውስጥ በስቅላት ከተገደሉ ወዲህ የኢራቅን ሕዝብ በአንድነት አስተባብሮ መምራት ለባለሥልጣናቱ አዳጋች ሆኖ ነው የቆየው። ሀገሪቱ በሙስና የተዘፈቀች፣ ሥራ አጥ የሚበዛባት፣ በአንፃሩ ፖለቲከኞች ምጣኔ ሀብቱን በዋናነት እየዘወሩ ኪሳቸውን የሚያደልቡባት እንደደሆነች ይነገራል፤ ኢራቅ። በሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ይሁንታን ሳያገኝ ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ መንግሥት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መሰል ችግር ይስተዋልበታል።

ኢራቃዊት መራጭ የኢራቅን ሠንደቅ-ዓላማ ይዛ

ኢራቃዊት መራጭ የኢራቅን ሠንደቅ-ዓላማ ይዛ

ከ11 ዓመታት በፊት፤ ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን፣ 1995 ዓም ኢራቃውያን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሣዳም ሁሴን ሀውልትን «ፍሪዶስ» አደባባይ ላይ ሲከሰክሱ የቦረቁባት መዲና ባግዳድ ዛሬ የጠዋት ፀሐዩዋን የምትቀበለው በቦንብ ፍንዳታ ነው። አውቶቡሶች፣ መዝናኛ ስፍራዎችና ምግብ ቤቶች አንዳንዴም መሳጂዶች ውስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎች በአካባቢያቸው ያለውን ነገር ሁሉ ሲያነጉዱ ማየት በባግዳድ የተለመደ ክስተት ሆኗል።

እንዲያም ሆኖ ግን 21,5 ሚሊዮን ኢራቃውያን ከእዚህ ሁሉ ጉድ ያወጡናል ሲሉ እምነት ለጣሉባቸው የምክር ቤት ዕጩዎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል። እናስ ኢራቃውያን ከገቡበት ጉድ ይወጡ ይሆን? ይወጡ ይሆናል፤ ሆኖም ግን ያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይታሰብ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic