የኢህአዴግ ስልጣን ሽግግር ከመለስ እስከ አብይ | ኢትዮጵያ | DW | 29.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢህአዴግ ስልጣን ሽግግር ከመለስ እስከ አብይ

ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በታሪኩ ሶስተኛ የሆኑትን ሊቀመንበር ከትላንት በስቲያ መጋቢት 18 መርጧል፡፡ አዲሱ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩን ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢህአዴግ ላለፉት አምስት ዓመታት የገባበት የአመራር መዋዠቅ በወፍ በረር ምን ይመስላል?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:33

የኢህአዴግ ስልጣን ሽግግር ከመለስ እስከ አብይ

ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም ንጋት፡፡ኢትዮጵያውያን ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የሀገሪቱን መሪ ህልፈት በመገናኛ ብዙሃን ተረዱ፡፡ በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አመራሮች ዘንድ ከተፈጠረው የ1992ቱ ክፍፍል በኋላ “ ስልጣኑን ሁሉ ጠቅልለዋል” በሚል ሲተቹ የነበሩት የአቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት በግልጽ የጎዳው ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን ነበር፡፡ የኢህአዴግ አስኳል ተደርጎ በሚወሰደው ሕወሓትም ላይ ያሰረፈው በትር ደግሞ ከሁሉም ከፍቷል፡፡ በርሳቸው ምትክ ገዢው ፓርቲ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ከውጭ ጉዳይ ሚንስትርነቱ ጋር ደርበዉ የያዙትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ወደ መሪነት ቦታ አመጣ፡፡ 

ከደርግ ጋር በነበረው ዉጊያ ያልተሳተፉት እና ለወታደራዊ ጉዳዮች ባዳ የሆኑት አቶ ኃይለማርያም የሀገሪቱ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሆኑ፡፡ በመስከረም 2005 ዓ.ም በተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤትም የገዢውን ፓርቲ ሊቀመንበርነት ተረከቡ፡፡ የእርሳቸው መመረጥ ተፈርቶ የነበረውን የስልጣን ሽሚያ ምስቅልቅል አስቀርቷል፡፡ነገር ግን በትጥቅ ትግል ውስጥ በተሳተፉ የጦር ሰዎች ቁጥጥር ስር ያለው የሀገሪቱ ጦርን እና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ላይ ያላቸው ስልጣን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም፡፡ 

“ሀገሪቱን በትክክል ማን ነው የሚመራት?” የሚለው ጥያቄ በሰው ዘንድ እንዲመላለስ አቶ ኃይለማርያምም የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተደጋጋሚ በሰጧቸው መግለጫዎች እርሳቸው “የመለስ ውርስ (ሌጋሲ)” አስፈጻሚ መሆናቸውን መናገራቸውም ይህን ጥርጣሬ አበርቶታል፡፡ ምናልባት ከቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲቀጥሉ እና የራሳቸውን ካቢኔ ሲመሰርቱ ጡንቻቸውን ያፈረጥሙ ይሆን ሲሉ ተስፋ ያደረጉ ነበሩ፡፡ 

ሀገር አቀፍ ምርጫው በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም ተካሄዶ ገዢው ፓርቲ እና አጋሮቹ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፋቸው ታወጀ፡፡ አቶ ኃይለማርያምም ከሁለት ወር በኋላ ገዢው ግንባርን ለሁለት ዓመት ተኩል እንዲመሩ ተመረጡ፡፡ ከአቶ መለስ በተረከቡት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር እንደሚቀጥሉ ታወቀ፡፡ በ2008 ዓ.ም መስከረም ወር የተሰበሰበው የተወካዮች ምክር ቤትም የሚጠበቀውን የማጽደቅ ሚናውን ተወጣ፡፡ 

ከምርጫው በኋላ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የስልጣን ዘመን ግን መቶ በመቶ ድጋፍ ያገኘ የአንድ ገዢ ፓርቲ መሪ የሚጋጥመው አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከውርስ የተላቀቀ ስልጣናቸውን በተቆናጠጡ በወሩ በኦሮሚያ ክልል የፈነዳው ተቃውሞ ሀገሪቱን የማትወጣበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከተታት፡፡ እርሳቸውም ሆኑ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ነው ያሏቸውን ለመስጠት ቢውተረተሩም ደም አፋሳሹ ተቃውሞ አንዴ ሞቅ፣ ሌላ ጊዜ ጋብ እያለ ቀጠለ፡፡

ህዝባዊው ተቃውሞው የአማራ እና የደቡብ ክልልን ሲያዳርስ መንግስታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ፡፡ አስር ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት መልሷታል በሚል ቢነሳም ተቃውሞ እዚህም እዚያም መፈንዳቱ አላባራም፡፡ የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ የሚሞቱትም ሰዎች ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ መጣ፡፡ በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ለ17 ቀናት በስብሰባ ተጠምዶ የከረመው የኢህዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “የማያዳግም እና መሰረታዊ መፍትሄዎችን” ይዞ እንደሚመጣ ቃል ተገባ፡፡  ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሳይጠበቅ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው  መላ ቅጡ የጠፋውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ይበልጥ አወሳስቦት ቁጭ አለ፡፡

በየካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡት አቶ ኃይለማርያም እስካሁን በይፋ ያስተላለፉት የገዢው ፓርቲ የሊቀመንበርነት ስልጣናቸውን ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ዘመናቸውን የመቋጨት እንኳ ዕድል ያላገኙት አቶ ኃይለማርያም እርሱንም በይፋ ለማስረከብ ለመጪው ሰኞ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡ ተተኪያቸው ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገላትን ሀገር “ወዴት ይወስዷት ይሆን?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ


 

Audios and videos on the topic