የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት በምዕራቡ ዓለም ላይ የሰነዘሩት ወቀሳ | ዓለም | DW | 07.04.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት በምዕራቡ ዓለም ላይ የሰነዘሩት ወቀሳ

የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት ሀሚድ ካርዛይ ራሳቸውን በይበልጥ ከምዕራቡ፡ በተለይም ከዩኤስ አሜሪካ እያራቁ መጡ።

default

ካርዛይ በአሸባሪነት አንጻር በተጀመረው ትግል ላይ የሚተባበሩዋቸውን አጋሮቻቸውን በአፍጋኒስታን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚልም ይወቅሱዋቸዋል። ይኸው የካርዛይ አነጋገር በዩኤስ አሜሪካ እና በአንዳንድ ምዕራብ አውሮጳ ሀገሮች ውስጥ እንደ እምነት ማጉደል የታየ ሲሆን፡ይከው አሁን በካቡል እና በዋሽንግተን መካከል የተፈጠረው ልዩነት የሰላሙን ተልዕኮ መሳካትን ስጋት ላይ እንዳይጥል እና በአፍጋኒስታን እና በመላው ዓለምም ላይ ከፍተኛ መዘዝ እንዳያስከትል አስግቶዋል።

ዋሽንግተን እና ካቡል አንዱ ባንዱ ላይ በጭፍን የሚተማመኑበት ጊዜ ያበቃ ይመስላል። ሁለቱ ወገኖች በታሊባን፡ በሙስና እና በሱስ አስያዡ ዕጽ ንግድ አንጻር በተጀመረው ትግል ላይ እርስበርስ አቅም አልባነት ይታያል በሚል መወቃቀሳቸውን ቀጥለዋል። ከዚህ ሌላም የአፍጋኒስታን ፕሬደንት ምዕራቡ ዓለም በሀገራቸው ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶዋል በሚል በጥብቅ ወቅሰዋል። ለምሳሌ፡ያለፈውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ያጭበረበሩት እርሳቸው ሳይሆኑ የውጭ ዜጎች መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።
ካርዛይ ባለፉት ወራት በማንኛውም ተጽዕኖ አንጻር ደፍረው የሚታገሉ ነጻ ፖለቲከኛ አድርገው ማቅረብ ጀምረዋል።

Obama / Afghanistan / Bagram / USA / NO-FLASH

በካንዳሃር በመጨረሻ ለጎሳ ሽማግሌዎች ባሰሙት ንግግር ላይ ለምሳሌ በቅርቡ ይደረጋል የሚባለው የኔቶ ጥቃት ከርሳቸውና ከጎሳ አንጃ መሪዎች ስምምነት ሲያገኝ ብቻ ሊካሄድ እንደሚችል አስታውቀዋል። ካለነርሱ ስምምነት ጥቃቱ የሚደረግበት ሁኔታ የሀገሪቱን ህገ መንግስት እንደሚጻረር ከምክር ቤት እንደራሴዎች ጋር በህቡዕ ባደረጉት ግንኙነት ወቅት ሳይናገሩ እንዳልቀረ ተገልጾዋል።
የታሊባን መስተዳድር ከተገረሰሰ ከስምንት ዓመት በኋላ ይህ ዓይነቱ የፕሬዚደንቱ አነጋገር በህዝቡ ዘንድ ድጋፍ አግኝቶዋል። ይህን ካርዛይና ቡድናቸው በሚገባ ያውቁታል። ፕሬዚደንቱ ለህዝቡ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት ባለመቻላቸው አሁን በቃላት ለማስደሰት ይሞክራሉ። ብዙው የአፍጋኒስታን ህዝብ በአሳዛኙ የሀገሩ ሁኔታ ቅር ተሰኝቶዋል። በተለይ በምዕራቡ፤ በመጀመሪያ ደረጃም በዩኤስ አሜሪካ። ጸጥታ፡ ዴሞክራሲ እና የተሻለ ኑሮ እንደሚያገኝ ነበር ቃል የተገባለት፤ ከአስር ዓመት ከተጠጋ ጊዜ በኋላ የሚታየው ገሀዱ ሁኔታ ግን በፍጹም ከዚህ የተለየ ነው።
ይሁን እንጂ፡ ካርዛይ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ አይደለም ከከለላ ሰጪያቸው ኃይል ዩኤስ አሜሪካ አሁን ራሳቸው ማራቅ የያዙት። የቀድሞውን የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ እምነት የነበራቸው ካርዛይ ከአሁኑ ዴሞክራቶቹ አስተዳደር ያን ዓይነት ድጋፍ እንደሌላቸው ተገንዝበውታል። ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ካርዛይ ከፓኪስታን እና ከዋነኛ ተፎካካሪያቸው አብዱላ አብዱላ ጋር ቅርበት አላቸው በሚል የሚወቅሱዋቸውን ሪቻርድ ሆልብሩክን የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ልዩ ልዑክ አድርገው ሾመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ካርዛይ ድጋሚ የተመረጡበትን ሂደት ዩኤስ አሜሪካ ማጠያየቅዋ አስቆጥቶዋችዋል። ከአክራሪ ታሊባኖች ጋር ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ካርዛይ ያቀረቡት ሀሳባቸውም ከኦባማ አስተዳደር የፈለጉትን ድጋፍ አለማግኘቱን ተረድተውታል። በጠላቶቻቸውና በወዳጆቻቸው ዘንድ የነበራቸውን አመለካከት ማጣታቸውን ያወቁት ካርዛይ አሁን ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እየጣሩ ነው። በቃላት ብቻ ሳይሆን፡ ፔኪንግ እና ቴህራንን በመጎብኘት ባካባቢው ሌሎች ወዳጆችም እንዳሉዋቸው ለማሳየት ይፈልጋሉ። ይህ አደገኛ ፖለቲካ ነው። ምክንያቱም ካቡል ከሀምሳ ዓመት ገደማ በፊትም ኃያላኑን መንግስታት እርስበርስ ለማጋጨት ሞክራ ነበር፡ ይህ ርምጃዋ እስከዛሬ ድረስ የሚታይ መዘዝ አስከትሎባታል።
አፍጋኒስታኑ ፕሬዚደንት ዩኤስ አሜሪካ የፈለገችውን ያህል ብትወቅሳቸውም ከርሳቸው የተሻለ አማራጭ እንደሌላት ያውቃሉ። ዩኤስ አሜሪካ እና አፍጋኒስታን ከቃላቱ ጦርነት ይበልጥ ህዱኡ ዲፕሎማሲ እንደሚያዋጣቸው ሊያውቁ ይገባል። በዋሽንግተን እና በካቡል መካከል የሚፈጠረው ልዩነት የሰላሙን ተልዕኮ ከማሰናከል አልፎ፡ በአፍጋኒስታን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ዓለም ም ላይ አሳሳቢ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

ራትቢል ሻሜል

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ