የአፍጋኒስታን የተማረ ኃይል ፍልሰት | ዓለም | DW | 22.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍጋኒስታን የተማረ ኃይል ፍልሰት

አንድ ትዉልድ በእንቅስቃሴ ላይ ነዉ። ከአፍጋኒስታን ዛሬም በቀጣይነት ሰዎች እየፈለሱ ነዉ። አብዛኞቹ እዚያዉ በሀገራቸዉ ዉስጥ ሌሎቹ ደግሞ ወደጎረቤት ሃገራት ይፈልሳሉ። ገንዘብ ያላቸዉ ደግሞ ወደአዉሮጳ ለመሻገር ሲሉ በሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች እጅ ይገባሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:56
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:56 ደቂቃ

የአፍጋኒስታን የተማረ ኃይል ፍልሰት

እድሜያቸዉ በ20ዎቹ መካከል የሚሆነዉ አብደላ እና ሃሚዱላ የመልክዓ ምድር እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራቂዎች ናቸዉ። ግን ከሀገራቸዉ መዉጣት ይፈልጋሉ። ከካቡል፤ ከአፍጋኒስታን መዉጣት።

«ወደጀርመን መሄድ እፈልጋለዉ፤ እዚያ የተረጋጋ ነዉ። ይረዱኛል፤ ሥራም እዚያ አገኛለሁ።» ይላል አብዱላ በፈግታ።

«ሁኔታዉ እዚህ የተሻለ ቢሆን ኖሮ መሰደድ አንፈልግም ነበር። ማንም ቢሆን ሀገሩን ወድዶ ጥሎ አይሄድም። ግን ምን ማድረግ እንችላለን? ከዚህ ወጣ ስንል በማንኛዉም ሰዓት ቦምብ ሊፈነዳ ይችላል። ሥራም ማግኘት አልቻልንም።» የሚለዉ ደግሞ ሃሚዱላ ነዉ። እናም ቁርጥ ያለ አቋሙን ሲገልጽም፤ «እዚህ ሀገር ዉስጥ በየቀኑ እንደሚታየዉ በስደት ጎዳና ላይ ሆኖ መሞት ይሻላል።» ባይ ነዉ።

ሁለቱ ወጣቶች ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን አነጋግረዋል። ወደማያዉቁበት ሀገር ለመሄድ እያንዳንዳቸዉ 15 ሺህ ዶላር መክፈል ይኖርባቸዋል። በኢራንና ቱርክ በኩል አድርገዉ ወደግሪክ ከዚያም ወደባልካን ሃገራት በመጨረሻም ጀርመን ለመግባት ነዉ እቅዳቸዉ። ሪቻርድ ዳንዚገር ካቡል የሚገኘዉ በአፍጋኒስታን የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት IOM ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸዉ። በመላዉ ዓለም ስላለዉ የፍልሰትና የስደተኞች እንቅስቃሴ እንዲህ ይላሉ፤

«ስለጅምላ ስደት መነጋገር እንችላለን ነገር ግን ቁጥሩን መገመት ያዳግታል። አሁን አዉሮጳ የደረሱትን ቁጥር ማወቅ እንችላለን። ሰዎች በርካታ የአዉቶቡስ ትኬቶችን እንደሚሸጡ እናዉቃለን፤ ከአዉሮፕላን ማረፊዎያዎች እንደተረዳነዉ ከዚህ በፊት ወደቴህራን በርካታ በረራ አነበረም፤ አሁን ግን ብዙ ወጣቶችን የጫኑ አዉሮፕላኖች ወደኢራን ይገባሉ። ተመላሽ በረራዉ ግን እንደዛ አለመሆኑ ይህ ጥሩ ማሳያ ነዉ። እናም ስለጅምና ፍልሰት መናገር ብንችልም ቁጥሩን ግን መጥቀስ አንችልም።»

በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ባለፉት 9 ወራት ብቻ 80 ሺህ አፍጋናዉያን በአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት ጥገኝነት ጠይቀዋል። ከእነዚህ መካከልም 17 ሺህ ያህሉ ጀርመን ዉስጥ ናቸዉ። ጀርመን የገቡት አፍጋኒስታናዉያን እዚህ ለመድረስ በመንገድ ላይ ሳምንታትን ወይም ወራትን አሳልፈዋል። ስደቱ በአንድ በኩል ከሰቆቃ ሽሽት ነዉ በሌላ በኩል ደግሞ ገንዘብ ለማግኘት ነዉ። ኩንዱስ ላይ የሚካሄደዉ ጦርነት ስደቱን እንዳባባሰዉ በግልፅ ይታያል። በሰሜናዊቱ የአፍጋኒስታን ግዛት ዋና ከተማ የጀርመን ጦር ለ10ዓመታት ያህል ተቀምጦባታል። ባለፈዉ መስከረም ወር መገባደጃ ድንገት በታሊባን ታጣቂዎች እጅ ወደቀች። ሪቻርድ ዳንዚገር አደገኛ አዙሪት ነዉ ይላሉ።

«ቁጥሩ እየጨመረ ለመሄዱ የሚያስረዱ ግልፅ ማሳያዎች አሉን። ምናልባትም ወደአዉሮጳ ከገቡት መካከል አብዛኞቹ ከኩንዱዝ ሊሉ እንደሚችሉ የሚችል መረጃ ያስፈልገን ይሆናል።

ምክንያቱም አዉሮጳ አሁን ስለኩንዱዝ እየተነጋገረ ነዉ። ስደቱ የፀጥታ አለመኖርና የኤኮኖሚ ጉዳይ ነዉ። አንዱ ሌላኛዉን ያባብሳል። አንድ አካባቢ የተረጋጋ ካልሆነ የሥራ ዕድል የለም። ሥራ ከሌለ ደግሞ አካባቢዉ ለሰርጎ ገቦች ጥቃት የተጋለጠ ይሆናል። በዚህም ላይ ጀርመን ሁሉንም ትቀበላለች የሚለዉ እምነትም ስደቱን አባብሷል። በዚህ መሀል አፍጋኒስታን የሰዉ ኃይሏን እያጣች ነዉ። የመተማመኑ ነገር እየጠፋ ነዉ። በጣም ከባድ ችግር ነዉ።»

በየዓመቱ እስከ500 ሺህ የሚደርሡ ወጣቶች ከአፍጋኒስታን የሥራ ገበያ ወደዉጭ ይወጣሉ። ዓለም አቀፉ ጦር ከሀገሪቱ በመዉጣቱ በርካታ የሥራ ዕድሎች ተዘግተዋል። በዚያም ላይ ተባብሶ የቀጠለዉ አመፅም የኤኮኖሚ እድገቱን አደናቅፏል። ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ግን በጎን ወደምድረ ገነቷ አዉሮጳ ወጣቱን እያሻገሩ ዶላር ያፍሳሉ። ከሚሰደዱት መካከልም ተምረዉ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑት ይገኙበታል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ደግሞ ችግር ዉስጥ የተዘፈቀችዉን ሀገር በመገንባቱ አይሳተፉም። ከመኖሪያቸዉ ከሚፈናቀሉት አብዛኞቹ አፍጋኒስታናዉያን ድሆች ናቸዉ። ለእነሱ ጀርመን የሚደረስባት አይደለችም። ከ800 ሺህ የሚልቁ አፍጋናዉያን ከሀገራቸዉ ተሰደዋል። ወደ2,5 ሚሊየን የሚሆኑት በጎረቤት ፓኪስታን እና ኢራን ተጠግተዋል።

ዛንድራ ፒተርስማን/ ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic