የአፍቃኒስታን ዉጊያና አዲሱ ዘመቻ | ዓለም | DW | 15.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍቃኒስታን ዉጊያና አዲሱ ዘመቻ

ፋርሶች፥ ሞንጎሎች፥ ቻይኖች፥ ሙስሊሞች፥ እንግሊዞች፥ ሩሲያዎች ሌሎችም በየዘመናቸዉ እየሔዱ ተመልሰወባታል።አፍቃኒስታን።አሜሪካኖች ከነተባባሪዎችዋ ከዘመቱባት ደግሞ ስምንት አመቷ።ዘመቻ ሙሽታራክ ብሪታንያዉ የጦር አዛዥ እንዳሉት «የስምንት አመቱ ሽምቅ ዉጊያ» የመጨረሻ መጀመሪያ ይሆን-ይሆን?

default

ሔልማንድ-አፍቃኒስታን

15 02 10

የዛሬ-ሰባት ስምንት አመት ማዛርኢሸሪፍ፥ ካቡል፥ ካንዳሐር፥ ቶራ ቦራ እና ሌሎች ብዙዎች እንደነበሩት ሁሉ መሰንበቻዉን የማርጃሕ መዳራሻ፥ የሔልማድ ዙሪያ-በቦምብ ሚሳዬል ጥይት አረር-እያረሩ ነዉ።አሜሪካ መራሹ ጦር ዘመቻ-ሙሸታራክ ያለዉን ጥቃት ቅዳሜ በመጀመረ-ማግሥት ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሰለቦች ሠላማዊ ሰዎች ሆኑ።እንደ ጦር ግንባሩ ወግ-ኮላተራል ዳሜጅ-የእግረ-መንገድ ጥፋት እንደማለት ነዉ-እየተባለ ዘመቻዉ ቀጥሏል።ዉጤቱ ነዉ-ናፋቂዉ።የዘመቻዉን አለማ ምክንያት እያነሳን ሥለ ዉጤቱ ጥቂት እንላለን-ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
ሔልማንድ-ግዛት የሠፈረዉ የብሪታንያ ጦር አዛዥ ጀምስ ካዋን ጦራቸዉን ወደ ዉጊያ ሲያዘምቱ ድል የእሳቸዉ እንደሚሆን የእርግጠኝነት ያሕል ነዉ-የተናገሩት።የድል ማግሥት እቅዳቸዉ ደግሞ አፍቃኒስታንን ዳግም መገንባት ነዉ።

«ታሊባንን ማዕከላዊ ሄልማድ ከሚገኙት ከአስተማማኝ ምሽጎቹ እናፀደዋል።በሔድንበት ሁሉ እዚያዉ እንቆያለን።በምንቆይበት ሁሉ እንገነባለን።የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አደጋ የማይደርስባቸዉ አይደለም»

ለአሜሪካኖች ሌሎች አጋሮቻቸዉም እንደዚያዉ ነዉ።ተጀመረ።-ዘመቻዉ። የአሜሪካዉ ባሕር ወለድ ቃኚ ጦር እንድ ጓድ የማርጃሕ ከተማ በስተግራ-ትቶ የኦፒየሙን ማሳ እየደፈላለቀ ሽቅብ-እየተጓዘ ነዉ።አላማዉ በከተማይቱን መዳራሻ መሽገዋል ብሎ የሚያስባቸዉን የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ለመክበብ ነበር።በጉዞዉ መሐል ግን-ድንገት ጥይት ያፏጭበት ያዘ። በደረትሕ ተኛ-ተኛ እያሉ ጮኩ።አዛዡ።

ወታደሮቹ-ለሽ አሉ-ትዕዛዝ አከበሩ።ከአሜሪካዎቹ ወታደሮች በስተቀኝ-በኩል የሚጓዙት የአፍቃኒስታን ወታደሮች ግን-የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ፍቶ አንሺ እንደተናገረዉ አንድም ትዕዛዙ አልገባቸዉም፥ ሁለትም አልሰሙትም ሰወስትም ለጠላት ጥቃት ፈጥኖ አፀፋ መስጠት እንጂ-ጊዜ መስጠቱን አልፈቀደቱትም።አካባቢዉን በአፀፋ ተኩስ አተረማመሱት።የአሜሪካዊዉ የጦር መሪ-አፍቃኖች ተኩስ እንዲያቆሙ መወትወት ነበረባ

Afghanistan US Soldaten Flash-Galerie

የአሜሪካ ወታደሮች

ቸዉ።

ዘመቻ-ሙሸታራክ ትብብር ወይም የጋራነት እንደማለት ነዉ ከመጀመሩ በፊት በዘመቻዉ የሚካፈሉት አስራ-አምስት ሺሕ ወታደሮች በቅጡ መደራጀት፥ መታጠቅ፥ መቀናጀታቸዉ፥የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች የሰፈሩበት አካባቢ ከሞላ ጎደል መታወቁ-በሰፊዉ ተነግሮ ነበር።የብሪታንያዉ የጦር አዛዥ ጄምስ ኮዋን እንዳሉት ደግሞ እጁን ያልሰጠ ታሊባን ፍፃሜዉ የፊጥኝ መቆራኘት ነዉ።

«እጃችንን የማይጨብጡ፥ እጆቻቸዉ ሲቆራኙ ያይዋቸዋል።ይሸነፋሉ።ከአፍቃኒስታን ወዳጆቻችን ጋር የእናንተ አዛዥ በመሆኔ እኮራለሁ።የጋራ ዘመቻ-ሙሽታራክ የደፈጣ ዉጊያዉ የመጨረሻ መጀመሪያ ይሆናል።»

በመጀመሪያዉ ግንባር የተሰለፈዉ የአሜሪካ ቃኚ ጦር አዛዥ ግን የጠላት ሐይል የመሸገበትን ሥፍራ፥ የወገን ጦር እራሱን አንድኖ-አድፍጦ አፃፋ የሚሰጥበትን ትክክለኛ ጊዜ ከማሰላሰል ይልቅ-የአፍቃኒስታን ባልደረቦቻቸዉን ተኩስ እንዲያቆሙ በትርጁማን በማግባባቱ ምግባር ነበር የተጠመዱት።

ብቻ ዉጊያዉ እንዲሕ ቀጠለ።የአፍቃኒስታኑ መከላከያ ሚንስትር አብዱል ረሒም ዋርዳክ እንዳስታወቁት በዉጊያዉ ሁለት ሺሕ የአፍቃኒስታን ወታደሮች ከተባባሪዎቹ ሐገራት ወዳጆቻቸዉ ጎን ተሰልፈዋል።የዘመቻዉ ሂደት ደግሞ መከላከያ ሚንስትሩ እንዳሉት በታቀደዉ መሠረት ቀጥሏል።

«አልፎ አልፎ አፀፋ ተኩስ ነበር።ከፍተኛ የሆኑ ፈንጂዎች በየሥፍራዉ ቀብረዋል።በርካታ ፀረ-ሰዉ ፈንጂ አጥምደዋል።ሥለዚሕ ቀስ እያልን መጓዝ አለብን።ቀስ እያልን ማለት ያን አካባቢ በማፅዳቱ ሒደት።ይሁንና እስካሁን ግስጋሴያችን በእቅዳችን መሠረት እየሔደ ነዉ።ግን እዚሕና እዚያ ያልተቀናጀ ተኩስ አጋጥሞናል።»

በጥንቃቄ የሚደረገዉ ዘመቻ የመጀመሪያ ሠለቦች ግን ሠላማዊ ሰዎች መሆናቸዉ ነዉ ዚቁ።ለትናንት አጥቢያ አስራ-ሁለት ሰዎች ተገደሉ። ዘመቻዉን በበላይነት የሚመራና የሚያቀነባብረዉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አዛዥ አሜሪካዊዉ ጄኔራል ስታንሌይ መክ ክርይስታል እንዳሉት ሰላማዊ ሰዎቹ የተገደሉት ጦራቸዉ የተኮሰዉ ሚሳዬል ኢላማዉን ስቶ መኖሪያ ቤቶች ላይ በማረፉ ነበር።

ዉጊያዉ ከመከፈቱ በፊት በሺሕ የሚቆጠር የአካባቢዉ ሕዝብ ቁሳቁሱን እየሸከፈ አስተማማኝ ወደላዉ ሥፍራ ተሰዷል።አንድ መቶ ሺሕ ከሚገመተዉ የአካባቢዉ ነዋሪ የተሰደደዉ ግን በጣም ጥቂቱ ነዉ።ሥደቱ ራሱ ሌላ ጣጣ አለዉ።የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ከሕዝቡ ጋር ተቀይጠዉ በየከተማዉ ይሸሸጋሉ ተብሎ ይፈራል።ፍራቸዉን ለማስወገድ በየአዉራጎዳዉ የሚደረገዉ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር የሚያስመርረዉ ሰዉ በያለበት ሆኖ የመጣዉን መጋፈ

Afghanistan / Helmand / Flüchtlinge

ሽሽቱም መከራ ነዉ-ሠላማዊዉ ሕዝብ

ጡን የሚመርጥ ብዙ ነዉ።

ዛሬ ግን ላንድ ግንባር የድል ቀን ነዉ።የተባባሪዎቹ ሐገራት ጦር ቢያንስ አስራ-ሁለት የታሊባን ሸማቂዎቹን መግደላቸዉን አስታዉቀዋል።የብሪታንያ ጦር ቃል አቀባይ ሜጄር ጄኔራል ጎርደን ሜሴንጀር እንዳሉት ጦራቸዉ ሌሊቱን በማርጃሕ ከተማ አጠገብ በከፈተዉ ጥቃት ባካባቢዉ የነበሩ ሸማቂዎችን አባርሯል።
«ታሊባኖችን ከነዚያ አካባቢዎች በርግጥ አስለቅቀናቸዋል።ይሁንና በቋሚነት ሥለመሸነፋቸዉ ወይም ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸዉን ሥለመፍታታቸዉ የሚጠቁም ምንም አይነት መረጃ የለንም።አሁንም አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ።ባካባቢዉ ያሉት ልጆች (ወታደሮችም) ሁኔታዉን በጥብቅ ይከታተላሉ።»

የደቡባዊ አፍቃኒስታን ሰፊ ግዛት ሔልማድ ታሊባኖች የሚቆጣጠሩት፥ የሚደራጁበት፥እንዳሻቸዉ የሚዘዋወሩበት፥ ከሁሉም በላይ ዋነኛ የገንዘብ ምንጫቸዉ የሆነዉ ኦፒየም በብዛት የሚመረትበት አካባቢ ነዉ።አሜሪካ መራሹ ጦር ሙለሕ መሐመድ ዑመር የሚመሩትን የታሊባን መንግሥትን በ2001 ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከሥልጣን ካስወገደ ወዲሕ ያን ግዛት በአዉሮፕላን-ሔሊኮብተር በስተቀር በእግረኛ ጦር ብዙም ደፍሮት አያዉቅም።

ቅዳሜ አንድ ያለዉ ዘመቻ ታሊባኖችን በዚያ በተጠንካራ ይዞታቸዉ-ሜዳ፥ በዚያ በከፍተኛ የገቢ ምንጫቸዉ ምድር ደምስሶ አካባቢዉን ለአፍቃኒስታን ጦር ለማስረከብ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ተጨማሪ ሰላሻ ጦር ለማዝመት ከወሰኑበት አንዱ ምክንያትም ታሊባኖችን ሔልማድን በመሰሳሉ አካባቢዎች መትቶ ወይም መሠረት አሳጥቶ-በ2001 ጦሩን ከአፍቃኒስታን ለማስወጣት ነዉ።

በቅርቡ ለንደን ላይ ተየተደረገዉ አለም አቀፍ ጉባኤ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ደግሞ የአፍቃኒስታን መንግሥትና መንግሥቱን የሚረዱት ምዕራባዉያን ሐገራት ለዘብተኛ ከሚባሉት የታሊባን ተዋጊዎች ጋር ይደራደራሉ።ለዘብተኛዉን ከአክራሪዉ ለመነጠል ታሊባን በቅጡ መደብደብ መዳከም አለበት።ታሊባንን ለማዳከም ደግሞ ጠንካራ ሐይሉ መመታት አለበት።መከላከያ ሚንስትር ዋርዳክ ታሊባኖች የሚኖራቸዉ አንድ ምርጫ ነዉ-ይላሉ
«ይሕን ጦርነት በአሸባሪነት ሥልት ማሸነፍ አይችሉም።እንደሚሸነፉ ሲያዉቁት ሌላ መንገድ ለመምረጥ ይገደዳሉ።በጣም ጥሩዉ መንገድ ደግሞ እርቅ ማዉረድ እና ዳግም ከሕብረተሰቡ ተቀላቅለዉ የፖለቲካዊ ሒደቱ አካል መሆን ነዉ።»
ዘመቻዉ በርካታ ወታደሮች በማሳተፉ፥ ብዙ የተጠና ብዙ የታቀደለት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንድምታዉ ለኔቶ አባል ሐገራት-በሙሉ፥ በተለይ ደግሞ ለፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር የአፍቃኒስታን ሥልት ወሳኝ ነዉ።ለፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ ደግሞ በሥልጣን የመቆየት አለመቆየታቸዉ መበየኛ ሊሆን ይችላል።

የዘመቻዉ ዉጤት የሚሠምረዉ፥እንደማይቀር ብዙ ጊዜ ብዙ የተነገረለት ድል ዳር የሚዘልቀዉ ደግሞ የሕዝብ ድጋፍ ካለዉ ነዉ።መከላከያ ሚንስትር ዋርዳክ ሕዝብ ከጎናችን ነዉ-ይላሉ።

«የዚሕ ሐገር ሕዝብ ሰወስት አስርት ባስቆጠረዉ ጦርነት ተሰላችቷል ብዬ አምናለሁ።ሕዝቡ መንግሥቱን መደገፍ ይፈልጋል።እስካሁን ድረስ እኛ ሕዝቡን (ነዋሪዎቹን) ከጥቃት መከላከል አልቻልንም ነበር።ከዚሕ በፊት የነበረዉ በተወሰነ አካባቢ ከአለም አቀፉ ሐይል ጋር በመተባበር ጥቃት እንከፍታለን።አካባቢዉን እናፀዳለን።ሌላ ጋ ሌላ አደጋ ሲፈጠር ይሕን አካባቢ ትተን ወደ ሌለኛዉ ሥፍራ እንሔዳለን።በዚሕ ምክንያት አንድ አካባቢ ቋሚ የፀጥታ ሐይል ሠፍሮ አያዉቅም።»

ግሪኮች፥ ፋርሶች፥ ሞንጎሎች፥ ቻይኖች፥ ሙስሊሞች፥ እንግሊዞች፥ ሩሲያዎች ሌሎችም በየዘመናቸዉ እየሔዱ ተመልሰወባታል።አፍቃኒስታን።አሜሪካኖች ከነተባባሪዎችዋ ከዘመቱባት ደግሞ ስምንት አመቷ።ዘመቻ ሙሽታራክ ብሪታንያዉ የጦር አዛዥ እንዳሉት «የስምንት አመቱ ሽምቅ ዉጊያ» የመጨረሻ መጀመሪያ ይሆን-ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
dw,agenturen
ሳንድራ ፔተርስማን/ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic