የአፍቃኒስታን ምርጫና ጉዞዋ | ዓለም | DW | 07.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአፍቃኒስታን ምርጫና ጉዞዋ

የምርጫዉ ሒደት፤ነፃነቱ፤ አፎካካሪ፤ አሳታፊነቱም፤ ያዩ እንደመሰከሩት ፤ለእልቂት ፍጅት ማዕከሊቱ ታሪካዊት ሐገር አዲስ ታሪክ ነዉ።አፊቃኒስታን።ዘንድሮ አስራ-ሰወስት ዘመን የተዋጋባትን-የዉጪ ጦር ሸኝታ የአስራ-ዘመን ታሪኳን ለሚቀይር ሌላ ታሪክም ተሞሽራለች።

አምና፤ሐቻምና፤የዛሬ አስር ዓመት፤ ከዚያ በፊትም እንደኖረችበት፤ እንደለመደች እንደታወቀችበትም ያለፈዉ ሳምንትም ሚሳዬል፤ ቦምብ ጥይት እየተዘራባት እስከሬን፤ ቁስለኛ- እንደተወቃ-እንደተቆጠረባት አገባደድችዉ። አፍቃኒሲታን።ቅዳሜ ግን፤ ከ2001 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በለመደችዉ መሐል፤ ያለመደችዉ ሆነባት።ምርጫ።ምርጫ-ዉጤቱ የእልቂት፤ ፍጅት፤ የጥፋት ዉድመቷ ፍፃሜ ምልክት ነዉ ማለት በርግጥ ጅልነት ነዉ።የአስራ-ሰወስት ዓመታት መሪዋ-የመሪነት ሥልጣን ፍፃሜ መሆኑ ግን እርግጥ ነዉ።የምርጫዉ ሒደት፤ነፃነቱ፤ አፎካካሪ፤ አሳታፊነቱም፤ ያዩ እንደመሰከሩት ፤ለእልቂት ፍጅት ማዕከሊቱ ታሪካዊት ሐገር አዲስ ታሪክ ነዉ።አፊቃኒስታን።ዘንድሮ አስራ-ሰወስት ዘመን የተዋጋባትን-የዉጪ ጦር ሸኝታ የአስራ-ዘመን ታሪኳን ለሚቀይር ሌላ ታሪክም ተሞሽራለች።የታሪካዊዉ ምርጫዋ እንዴትነት፤ የአሮጌ መሪዋ ስንብት፤ የዉጪዉ ጦር ሽኝት ለምንነትን እየጠቃቀስን፤የአዲሱ ታሪኳ በጎ-መጥፎነትን እናጠያይቃለን።

የአንድ ሳምንቱን ቀን፤ ጥፋት፤-አስከሬንና ቁስለኛ ከሞላ ጎደል እንቁጥር።-በምርጫዉ ዋዜማ አርብ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በደረስ ጥቃት አንዲት ጀርመናዊት የፎቶ ግራፍ ጋዜጠኛን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።አንዲት ካናዳዊት ጋዜጠኛን ጨምሮ ከአሥር በላይ ቆስለዋል።

ከአርብ በፊት-ሐሙስ።በወዲያኛዉ ሳምንት እሁድ ሳር ኢ ፑል ከተባለዉ ግዛት የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ያገቷቸዉ የግዛቲቱ ምክር ቤት እጩ አባልና አስር ደጋፊዎቻቸዉ ሮብ ማታ መገደላቸዉ ተነገረ።ሮብ-ሌላ ጥቃት ተጨማሪ ሞት።አምስት-ሰዎች መገደላቸዉ ተስማ።ማክስኞ-ታጣቂዎች ካቡል የሚገኘዉን የአፍቃኒስታን ምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤትን ወረዉ-ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ይተጋተጉ ያዙ።አምስት ሰዓት ከፈጀ ዉጊያ በኋላ ካቡል-ለሞት ቆሌዋ-አምስት ዜጎችዋን ጭዳ-አደረገች።ሁለቱ ፖሊሶች፤ ሁለቱ የምርጫ ኮሚሽን ሠራተኞች፤ አንዱ የክፍለ ግዛት ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ነበሩ።

የተፎካካሪዎቻቸዉን፤የአስመራጭ መራጫቸዉን ሕይወት አካል ለቦምብ ጥይት የሚገብሩት ዕጩ ተፎካካሪዎች የምርጫ ዘመቻ፤ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ሐሚድ ካርዛይ የምረጡ ማሳሰቢያም እንደ-ዉጊያ፤ሽብር፤ ግድያዉ ሁሉ አላባራም ነበር።

«የአፍቃኒስታን ሕዝብ (ሆይ) ዕጩዎችሕን ለመምረጥ እንድትወጣ በድጋሚ አሳስባለሁ።ለዝናብ፤ ቅዝቃዜ፤ ለጠላቶችሕ ዛቻ-ግድያ ሳትበገር ድምፅሕን እንድትሰጥ።»

ከማክሰኞ በፊትም-አፍቃኒስታን ያዉ አስራ-ሰዎስት ዓመት እንደታወቀችበት እልቂት ፍጅት እንደነገሰባት ነበር።ምርጫዉ ሳምንት ሲቀረዉ ቅዳሜ የካቡሉን የምርጫ ኮሚሽን ቅጥር-ግቢን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤት ፍርስራሽ በወረቀት-ክሳይ፤ በደም ጎርፍ ያጨቀየዉ ጥቃት ከባዱ፤ አስፈሪዉም ነበር።

በጥብቅ የሚጠበቀዉን የምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤት የወረሩ አምስት የታሊባን ታጣቂዎች ባፈነዱት ቦምብና በተኮሱት ጥይት በርካታ ሰነዶችን አጋይተዉ ሁለት ሰዎች አቆሠሉ።ፀጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት አፀፋ አምስቱን ታጣቂዎች ገደሉ።በሳምንቱ ያ-በሳምንት ዉስጥ ሁለቴ በተከፈተበት ጥቃት የተቦዳደሰዉ ፅሕፈት ቤት-የመራና ያስተባበረዉን ምርጫ አፍቃኒስታን አስተናገደች።ቅዳሜ።ዕለቱ ዕለትም ከጥቃት አልተላቀቀችም።

አፍቃኒስታን የሰፈረዉ አሜሪካ መራሽ ዓለም አቀፍ ጦር እንዳስታወቀዉ የምርጫዉ ዕለት በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች ከአንድ መቶ ሠላሳ በላይ ጥቃቶች ደርሰዋል፤ወይም ተሞክረዋል።በጥቃቶቹ ቢያንስ ሰወስት መራጮጭ፤ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች-ጠፍተዋል።ከ40 የሚበልጡ ሠላማዊ ሰዎች ቆስለዋል።211 ድምፅ መስጪያ ጣቢዎች ምርጫ ሳይደረግባቸዉ ተዘግተዋል።አዉሮፕላን ማረፊዎች፤ አፍቃኒስታንን ከሌሎች ሐገራት በተለይም ከፓኪስታን ጋር የሚያገናኙ ድንበሮች ተዘግተዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ፖሊስና ጦር ሠራዊት በተጠንቀቅ ቆሟል።

ሞት፤ ሽብር-ጥፋትን የለመደዉ ሕዝብ ግን ድምፁን ለመስጠት እንደተፈራዉ አልፈራም።«ጥይት ቢዘንብም፤ ምድሩ በተቀበረ ፈንጂ ቢጋይም እኛ ወንዶችም ሴቶችም ድምፃችንን ለመስጠት መጥተናል።እኛ አፍቃኖች ልጁ ካዋቂ ሳንል በምርጫዉ መሳተፍ አለብን።»

አሉ ሐጂ ጉል አጋሕ።ፋጢማ ሞርታዛዪ አከሉበት።«ለሐገሬ (አፍቃኒስታን) የወደፊት ዕድል ዋስትና ለመስጠት ሥል መርጫለሁ።ድምፅ በመስጠት ሐገራችን እንገነባለን፤ ድምፅ በመስጠት ተሳትፏችንን እናሳያለን።»

የአፍቃኒስታን የወደፊት-ዋስትና!!!

የአፍቃኒስታን የእስካሁንም የወደፊትም ዘዋሪዎች፤ የዓለም ሐያላን ሰሞናዊ አብይ ትኩረት ሌላጋ ነበር።ክሪሚያ-ሞስኮ-ኪየቭ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከሐገራቸዉ ጥብቅ ወዳጅ የአዉሮጳ ሐያል፤ሐብታም አቻዎቻቸዉ ጋር ዘሐግ-ኔዘርላንድስ ዉስጥ ሩሲያን አዉግዘዉ ሮም-ኢጣሊያ ሲገቡ፤ የአዉሮጳ መሪዎች ከዘ-ሔግ ወደየርዕሠ ከተማቸዉ የተመለሱት ባፍታ ከተሻራኪነት ወደ «ጠላትነት»የተለወጠችዉን ሐያል ሐገር አፀፋ ለማወቅ አይን ጆሯቸዉን ሞስኮ ላይ እንደሰኩ ነበር።

ፕሬዝዳንት ኦባማ የልዕለ ሐያል ሐገራቸዉን ሐያል መሪዎችን እንደጠላት የሚያወግዙ፤የሚያስወግዙበትን ግን ደግሞ አንደማይደፈር ጠላት በስልክ የሚያናግሩበትን ሥልት-ቃላት በይደር አስቀምጠዉ የሐገራቸዉን ታማኝ ታዛዥ ትንሽ ግን ሐብታም ሐገር ገዢዎችን እንደደረጃቸዉ ለማነጋገር ከሮም ሪያድ ገቡ።

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ከሩሲያ አቻቸዉ ስርጌይ ላቭሮቭ ጋር ለመነጋገር ድንገት ለተያዘ ቀጠሮ ከአለቃቸዉ ተነጥለዉ ከሪያድ ወደ ፓሪስ ሲመለሱ፤ የአዉሮጳ መሪዎች ከኦባማ ጋር ዘ-ሔግ ላይ ከተለያዩ ጀምሮ ሞስኮ ላይ የተከሉትን አይን፤ ጆሯቸዉን ከሞስኮ ነቅለዉ ፓሪስ ላይ ተከሉት።መጋቢት ሃያ-ዘጠኝ።

የፓሪሱ ዉይይት ያለዉጤት ሲያበቃ ግን ኦባማ ወደሪያድ ሲሔዱ እንዳደረጉት ሁሉ የትልቅ ጠላታቸዉን ጉዳይ ቀዝቀዝ አድርገዉ የአፍሪቃ ትናንሽ ታማኝ፤ ታዛዥ፤ ተባባሪዎቻቸዉን የሚያስተናግዱበትን፤ በግልና በተናጥል የሚነግሩትን ይቀምሩ ገቡ። ፕሬዝዳት ኦባማ ለሪያድ ገዢዎች፤ የአዉሮጳ መሪዎች ብራስልስ ላይ ላስተናገዷቸዉ የፍሪቃ መሪዎች -የተናገሩትበት መንግድ፤ጊዜና ርዕስ ተቀራራቢ ይባል እንደሁ እንጂ በርግጥ የተለያየ ነዉ።

ጥቅል-ይዘት አላማዉ ግን ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች ከተጠቃች ከ2001 ጀምሮ የዋሽግተንና የብራስልስ ሐያል ሐብታም ፖለቲከኞች ጥቅማቸዉን ለማስከበር ትናንሽ ታማኝ ታዛዦቻቸዉን ለመያዝ እንዳዲስ ከቀየሱት ሥልት፤ አዲስ ከቀመሩት ብልሐት የራቀ አይደለም።

የሪያድ ፤ የካይሮ ገዢዎችና ብጤዎቻቸዉ፤ ከኢራቅ እስከ ሊቢያ እስከ ሶሪያ የሚገኙ ሐገራትን ባጠፋና በሚያጠፋዉን ጦርነት በመሳተፋቸዉ፤ አሸባሪዎችን በመዋጋት፤ ኢራንን የመሳሰሉ ሐገራትን ለማግለል በመተባበራቸዉ ከምዕራቡ ሐያል ዓለም አድናቆት ምስጋናዉ ተንቆርቁሮላቸዋል።

ከአንጎላ እስከ ዩጋንዳ ያሉ ገዢዎችም ከየሐገራቸዉ አልፈዉ በየአጎራባቾቻቸዉ ሠላም ለማስፈን፤ አሸባሪዎችን ለማጥፋት በመጣር መተባበራቸዉ ተመስግነዋል።በብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ አገለለፅ ምጣኔ ሐብታቸዉን በማሳደጋቸዉ ተወድሰዋል።

«ከዓለም ፈጣን የምጣኔ ሐብት ዕድገት ከሚታይባቸዉ ሐገራት የተወሰኑት አፍሪቃ ዉስጥ ናቸዉ።ለአዉሮጳ ጨምሮ ለወደፊቱ ለሥራ ዕድል ፤ለብልፅግናና ለመዋዕለ ነዋይ ፍሰት አፍሪቃ ጠቃሚ ናት።ሥለዚሕ ከአፍሪቃ ጋር ያለዉ ግንኙነት ጠቃሚ ነዉ።»

በቀዝቃዛዉ ጦርነት መጀመሪያ ከአዉሮጳ ቅኝ ተገዢነት ወደ ዕርዳታ ተቀባይነት የተለወጥችዉ አፍሪቃ፤ ባለፉት አስር፤አሥራ-ሁለት ዐመታት የአዉሮጳ ሕብረቱ ፕሬዝዳንት ሐርማን ፋን ሮምፖይ እንዳሉት ከዕርዳታ ተቀባቀባይነት ወደ እኩል ተሻራኪነት ተለዉጣለች።

ባለፉት አስራ-ሰወስት አመታት ምጣኔ ሐባታቸዉ ማደጉ፤ ሠላም ማስፈናቸዉ፤ ከምዕራባዉን ርዳታ ተቀባይነት ወደ አቻ ሸሪክነት አደጉ ከሚባላልላቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አብዛኞቹ ግን ባለፉት አስራ-ሰዎስት አመታት በጦርነት የምትዳክረዉ አፍቃኒስታን በቀደም ያደረገችዉን ዓይነት እንኳ ነጻ ምርጫ አያዉቁም።በፀረ-ሽብር ዉጊያ ተባባሪናቸዉ የተመሰገኑ የተወደሱና የሚወደሱት የሪያድ ነግሥታት፤የግብፅ ወታደራዊ ገዢዎች ደግሞ ምርጫ ሊያስተናግዱ ቀርቶ የተመረጠ መሪ የሚያስወግዱ ናቸዉ።

አፍቃኒታን ጋዜጠኞች ይገደሉባታል።የዚያኑ ያክል ሰባ-አምስት ቴሊቪዥን ጣቢያዎች፤ ከአንድ መቶ በላይ ራዲዮ ጣቢያዎች ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ጋዜጦች ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆነዉ ይዘግቡባታል።ከአፍሪቃ-ሰሜን-ምሥራቅ ጫፍ ግብፅ እስከ ደቡብ ምዕራብ ጠረፍ አንጎላ ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ የሆኑ መገናኛ ዘዴዎች ቢደመሩ በጦርነት የምትታደክረዉን የአዲት አፍቃኒስታንን አያክሉም።ባለፉት አስራ-ሰወስት ዓመታት ያቺን ሐገር የመሩት ሐሚድ ካርዛይ የሁለት ሺ ዘጠኙን ምርጫ ማጨበርበርን ጨምሮ በበርካታ ጥፋቶች ይወነጀላሉ።ሐገር-ሕዝባቸዉን የሚያጠፋዉን ጦርነት ለማስቆም ግን አቅም-ዉሳኔዉ የዋሽግተን ብራስልሶች እንጂ የካርዛይ አልነበረም። አይደለም።

የካቡሉ የሐገር ሽማግሌና የፖለቲካ አዋቂ መሐመድ አስፍ እንደሚሉት ደግሞ እኚያበ2001 አሜሪካኖች የሾሟቸዉ ካርዛይ የሚመሰገኑባቸዉ ብዙ እርምጃዎችንም ወስደዋል።

«ካርዛይ ካከናወኗቸዉ ተግባራት የፕረስ ነፃነትን ማስከበራቸዉ፤ የሴቶች እኩልነትን ማጠናከራቸዉ እና የመምረጥ መብትን ማስከበራቸዉ የሚጠቀሱ ናቸዉ።ይሕ ታላቅ እመርታ ነዉ።ካርዛይ ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ሲወዳደሩ አልመረጥኳቸዉም፤ ምክንያቱም ቃላቸዉን አላከበሩም ነበርና።»

ከእንግዲሕ በቃል አባይነት አይከሰሱም፤ ከካምፓላ እስክ ሉሳካ፤ ከካይሮ እስከ ኪጋሊ እንደተደረግ ወይም እንደተሞከረዉ ሕገ-መንግሥት ሽረዉ ሥልጣን ልያዝ ወይም የያዝኩትን አለቅም አላሉም።እሳቸዉን ለመተካት የሚፎካከሩት ዕጮዎችን መርሕ-ዓላማ ከሳቸዉ እደሚቃረን ቢያዉቁም የምርጫዉን ሒደት ለማወክ አልቃጡም።

እንዲያዉም በተቃራኒዉ ወንድማቸዉ ሳይቀሩ ከዕጩነት መገለላቸዉን ደግፈዉ ሕዝብ ለቀሪዎቹ ዕጩዎች ድምፅ እንዲሰጥ እንደገፋፉ ቅዳሜ-ደረሱ።ካርዛይን ለመተካት ከተፎካከሩት አስራ-አንድ ዕጩዎች አፍቃኒስታን እንደምትታወቅበት አንድም የቀድሞ የጦር አበጋዝ የለም።በምርጫዉ ያሸንፋሉ ተብለዉ የሚገመቱት ሁለቱ በካርዛይ ዘመነ ሥልጣን ሚንስትር የነበሩ ናቸዉ።

የቅድሞዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሕ አብዱላሕ ከዚሕ ቀደም በተደረጉ ሁለት ምርጫዎች ተወዳድረዉ የተሸነፉ ግን እዉቅ ፖለቲከኛ ናቸዉ።የትልቁ የአፍቃኒስታን ጎሳ የፓሽቱንና የታጂክ ቅይጥ ቢሆኑም-አስተዳደግ አስተሳሰባቸዉ ጎልቶ የሚነገረዉም ታጅክ መሆናቸዉ ነዉ።የአይን ሐኪም (ዶክተር) ናቸዉ።

አሽረፍ (አንዳንዶች አርሻፍ ይሏቸዋል) ጋኒ የገንዘብ ሚንስትር ናቸዉ።በምዕራቡ ትምሕርት የበሰሉ፤ አሜሪካ ዩኒቨርሲዎች ያስምሩ የነበሩ፤ አሜሪካ ዜግነታቸዉን መልሰዉ ሐገራቸዉ የገቡ ፖለቲከኛ ናቸዉ።አንዳዶድ አፍቃኒስታኖች በጦርነት ሲሰቃዩ አሜሪካ ይደላለቁ ነበር እያሉ ያሟቸዋል።ያም ሆኖ በፖለቲካዉ ብዙ ባይታወቁም በትምሕርታቸዉ የተከበሩ፤ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የፓሽቱን ጎሳ ተወላጅ በመሆናቸዉም ከፍተኛ ድምፅ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።የቀድሞዉ ፕሮፌሰር ከዑዝቤክ የሚወለዱትን የቀድሞ ዕዉቅ የጦር አበጋዝ ጄኔራል አብዱል ረሽድ ዱስታምንም ከጎናቸዉ አሰልፈዋል። የቀፍቃኒስታን ሕዝብ የወደፊት ፕዝዳንቱን ለመምረጥ መምረጥ ከሚችለዉ አስራ-ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ከስባት ሚሊዮን የሚበልጠዉ ወይም ወደ ስልሳ ከመቶ የሚጠጋዉ ድምፅ ሰጥቷል።

«ለምፈልገዉ ዕጩ ድምፄን እሰጣለሁ።በፈጣሪ ፈቃድ የሚያሳስበን፤ የሚያስፈራንም ነገር የለም።ታሊባኖችን ወይም አጥፍቶ ጠፊዎችን አንፈራም።»እያለ-እንደሳቸዉ፤ ወይም እንደዚሕኛዉ፤«ሔጄ ድምፄን እሰጣለሁ፤ታሊባንን ወይም ሌላ ጥቃትን አልፈራም።አመርጣለሁ።»

በቅዳሜዉ ምርጫ ለመሪነት የሚያበቃዉን ከሐምሳ ከመቶ በላይ ድምፅ የሚያገኝ ዕጩ መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።ባሁኑም ሆነ በወደፊቱ የመለያ ምርጫ የመሪነቱን ሥልጣን የሚይዘዉ መሪ ከመጀመሪያ ሥራዎቹ ትላልቆቹ ካርዛይንም፤ አሜሪካ መራሹን የዉጪ ጦርም በክብር መሸኘት ነዉ።ትልቁ ፈተናዉ ደግሞ የቀድሞዉ የአፍቃኒስታን የንግድ ሚንስትር አሚን ፋርሐንግ እንደሚሉት ሙስናን መዋጋት፤ የተሐድሶ ለዉጥን ገቢር ማድረግ ነዉ።

«በተጨባጭ ማለት የምፈልገዉ የወደፊቱ መሪ በሁለተኛዉ የአፍቃኒስታን አጠቃላይ ጉባኤ የደረስንባቸዉን ስምምነቶች ገቢር ማድረግ አለበት።ሙስናን መዋጋት፤መልካም አስተዳድርን ማስፈን፤የአደንዛዥ ዕፅ ምርትና ስርጭትን መዋጋት፤ የአፍቃኒስታን ምርትና ምጣኔ ሐብት እንዲያድግ ሕጋዊ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትን የማበረታት አለበት።»

ይሕን ለማድረግ አፍቃኒስታንን ማረጋጋት ግድ አለበት።አሜሪካ መራሹ ጦር የአልቃዲና አሸባሪዎችንና የታሊባን ደጋፊዎችን ለመዉጋት ከዘመተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባላባራዉ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠር የአፍቃኒ ዜጋ (ሲቢል፤ታሊባን፤ አሸባሪ፤ የመንግሥት ወታደር) እየተባለ አልቋል።ዛሬም መንገድ ዳር በተቀበረ ፈንጂ አስራ-ሰወስት ሰላማዊ ሰዉ ተገድለዋል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተሰዷል።ከሰወስት ሺሕ አራት መቶ በላይ የዉጪ ወታደሮች ተገድለዋል።

አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታንን ለቅቆ መዉጣቱን አብዛኛዉ የአፍቃኒስታን ዜጋ ይደግፈዋል።በ1989 የያኔዋ ሶቬት ሕብረት ጦር አፍቃኒስታንን ለቅቆ ሲወጣ፤-እንድ መምሕር እንድሚያስታዉሱት፤ አፍቃኖች ከኢድ አል-ፊጥርና ከኢድ-አል አደሐ በዓላት እኩል ነበር የፈነደቁ-ያከበሩት።የዋሁ ሕዝብ ከሌላ እልቂት ፍጅት-አለማምለጡን ለማወቅ ግን ብዙም አልቆየም።በቅዳሜዉ ምርጫ በሙሉ ስሜት የተሳተፈዉ፤ በአሜሪካ መራሹ ጦር መዉጣት የሚደሰተዉ ሕዝብ የዛሬ ሃያ-አምስት አመቱ የበጎ ተስፋ ቅጭት እንዳይደገም የወደፊቱ መሪ አበክሮ ሊሰራና ሊጥር ይገባዋል።

ካርዛይን የሚተካዉ መሪ ከታሊባኖች ጋር ተደራድሮ፤ ወይም ታሊባኖችን ከሕዝብ ነጥሎ በሐገሪቱ ሠላም ለማስፈን ካልጣረ-ጥረቱ እንዲሳካ ሃያሉ ዓለም ካልደገፈዉ ከጦርነት ዑደት ያልተለየችዉ ሐገር እንደ ኢራቅ ወደ «ሰዉ ቄራነት» ላለመለወጧ ምንም ዋስትና የለም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic