የአፍቃኒስታን ሁኔታና የዩናይትድ ስቴትስ መርሕ | ዓለም | DW | 16.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍቃኒስታን ሁኔታና የዩናይትድ ስቴትስ መርሕ

ግራቀኝ ስትላጋ ሰባት አመት ያስቆጠረችዉ ሐገር ዛሬም ከሰላም ሩቅ ነች።አፍቃኒስታን።ከእንግዲሕ ወዴት እንዴት ትጓዝ ይሆን?

default

የዉጪ ወታደሮች የሰኞዉን የጥቃት ሥፍራ ሲመለከቱ

አሸባሪ-አክራሪዎች እንደጠፉባት፣ የፀረ-ሽብር ዘመቻዉ ለድል እንደበቃባት፣ እየተፎከረ እየተነገረላት፤ በአሸባሪ-አክራሪ፣ ሸማቂዎች የመሞላቷ፣ በዉጊያ የመጥፋቷ ሐቅ እንደተመሰከረባት ሰባተኛ አመቷን አጋመሰች።አፍቃኒስታን።አዲሱ-የዩናይትድ ስቴትስ መስተዳድር የሚባል-የሚሆነዉ ተቃርኖ ላቃረጧት ሐገር ተቃራኒ የሚመስል ግን መንታ ሥልት ቀይሷል።ተጨማሪ ጦር ማዝመትን ከድርድር ፍንጭ የቀየጠዉ መንታ ሥልት ምንነት፣ የሚሰነዘርበት መንታ አስተያየት-እስከየትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ፣፧አብራችሁኝ ቆዩ።

===================================================================

ሥልጣን በያዙ-በሃያ-ሥምንተኛዉ ቀን ለመከላከያ ሚንስትራቸዉ ፃፉ።ፈጠኑ።ግን ከሴናተርነት ዘመናቸዉ ጀምሮ-ከሚያሳስባቸዉ ትላልቅ ችግሮች የአንዱ እንዴትነት፣ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የገቡትን ቃል ለመጠበቅ-የመወሰናቸዉን ፅናት ባንድ ምዕራፍ ጠቀለሉት።

«ታሊባን አፍቃኒስታን ዉስጥ የሽምቅ ጥቃቱን አጠናክሯል።አፍቃኒስታንን ከፓኪስታን ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር የመሸገዉ አል-ቃኢዳ ደግሞ የሽምቅ ዉጊያዉን ያበረታታል።እና አሜሪካንን ያሰጋል።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።የካቲት 18 2009።(ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ»

አፍቃኒስታን የሰፈረዉ ጦር አዛዥ ጄኔራል ዴቪድ ማክ-ኪማን ኦባማ በፈጣን ደብዳቤቸዉ የገለፁትን ችግር በገቢር ካዩት፣ ችግሩ እንዲቃለልቻቸዉ ለበላዮቻቸዉ አቤት ካሉ በርግጥ ዉለዉ አድረዋል።

ጄኔራሉ ምናልባት ከፕሬዝዳታቸዉ በላይ የሚያዉቁትን ችግር ለማቃለል የጠየቁት ሰላሳ ሺሕ ተጨማሪ ወታደር በሙሉ እንዲዘምት ፕሬዝዳቱ በርግጥ አል-ወሰኑም።ከቀዳሚያቸዉ የተሻለ መልስ ግን ሰጡ።አስራ-ሰባት ሺሕ እንዲዘምት አዘዙ።

===================================================

የምሥራቁ ባሕል፥ ሥልጣኔ-ሥይጣኔ፥ከምዕራቡ የሚገናኝ የሚወራረስባት ሐገር ልዩ-ጉጥ-ስርጓጉጧ፣ መታዋቂያ ሸጥ-ተረተሯዋ በሰዉ ላብ-ደም በተቦካ የሰዉ ሥጋ የተለሰነ-የሰዉ አጥንት የማጋረዉ እስኪመስል ድረስ እልቂት እየተዘራ-አስከሬን በሚታጨድበት ታሪክ የታከተ ነዉ።

በስድተኛዉ አመተ-አለም የገነነዉ ሜደስ የተሰኘዉ የፋርስ ሥርወ-መንግሥት ከደቡብ ከጥቁር ባሕር ግርጌ-እስከ አዘርበጃን፣ ያለዉን ሰፊ ግዛት አስገብሮ ወደ ሰሜን ፓኪስታንን አልፎ-የአፍቃኒስታንን ጫፍ እንደተቆጣጠረ-ታላቁ ሳይሩስ በመሠረቱት በፋርሶቹ የአቺሜድ ሥርወ-መንግሥት ተደመሰሰ።

አሌክሳንደር ታላቁ፣ ከአምስት መቶ አመተ-አለም ጀምሮ የባቢሎን፤ የአሰርያ፤ የፎኔሽያ፣ የሊሪያን ግዛቶችን የጠቀለለዉን የአቼሜድ ሥርወ-መንግሥትን አሸንፎ-የአለም ተረኛ ገዢነቱን ለማረጋገጥ በሰወስት መቶ-ሰላሳ ስድስት አመተ አለም ግድም አፍቃኒስታን እስኪቆጣጠር መጠበቅ ግድ ነበረበት።

ቱርኮች-አፍቃኒስታንን እስኪጠቀልሉ፤ ሞንጎሎች ከአፍቃኒስታንን እስኪሻገሩ ድረስ የየዘመናቸዉ የአለም ገዢነታቸዉ አጠያያቂ ነበር።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በ1839 ያዘመቱት ጦር ከአፍቃኖች ጋር ድፍን-ሰወስት አመት ተዋጋ።ብዙዉ አለቀ።ተሸነፈም።በ1878 ሌላ ጦር ዘመተ።ሁለት አመት ተዋጋ።ተሸነፈ።

ብሪታንያዎች ዉጊያዉ አልሆን ይበላቸዉ እንጂ በገንዘብ፤ በሥልጣን የተደለላቸዉ ጎሳ መሪ ያለበትን አካባቢ መቆጣጠር ግን በርግጥ ችለዉ ነበር።ብዙ ግን አልቆዩም።በ1919 ለቀዉ ወጡ።ሶቬት ሕብረት በ1979 ያዘመተቸዉ መቶ ሺሕ ጦር በከፈተዉ ዉጊያ ከስድት መቶ ሺሕ፥ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚገመት ሰዉ አልቋል።

ያየዚያ ዘመኑ የአለም ምርጥ ጦር-ግን በአስረኛ አመቱ ተዋርዶ ተሸንፎ ከመዉጣት ሌላ ምርጫ አልነበረዉም።ሽንፈቱ የዚያች-የዚያ ዘመኑ አለም ልዕለ-ሐይል ሐገር የመሰነጣጠቅ ንቃቃቷ ሥፋት፥ ምስክር የመጨረሻዋ መጀመሪያ እማኝ መሆኑ ነዉ የዘመኑ ጉድ።አፍቃኒስታን የወራሪ-ማፈሪያ፤ ያሸነፊ-መሸነፊያ፤ የገዳይ-መገደያ የመሆንዋ ታሪክ የደመቀባት አንድም በሕዝቧ እንቢተኝነት፣ ሁለትም በአለም ሁነት ግጥጥሞሽ እንጂ ልዩ ዛር፤ ቆሌ፤ ምትሕት ሥላላት አይደለም።

ጥንት-ድሮ የሆነባት ዘንድሮ ይደገምባታል ማለትም በርግጥ የዋሕነት ነዉ።የዚያኑ ያክል ታሪክ-እራሱን መድገሙን አለመረዳት ጅልነት ነዉ።ፕሬዝዳት ኦባማ ታሊባን አል-ቃኢዳዎችን ለማጥፋት ተየተከፈተዉን ዉጊያ ለመቀጠል፤ ተጨማሪ ጦር ለማስዝመት ሲወስኑ ከሜንዴስ-እስከ ሞንጎል-እንግሊዞች ነገስታት ከታላቁ ሳይሩስ እስከ ታላቁ አሌክሳንደር፣ ከብሬዥኔቭ-እስከ ዳግማዊ ቡሽ በየዘመናቸዉ ያደረጉትን ዘመኑ በሚፈቅደዉ ሥልት ከመድገም ሌላ-ሌላ በርግጥ አላደረጉም።

ተጨማሪ ጦር እንዲዘምት ባዘዙ-በሁለተኛዉ ሳምንት የድርድር ፍንጭ መስጠታቸዉ ግን በርግጥ የሳቸዉ ብቻ ካለፈም የጥቂት ቀዳሚዎቻቸዉ ሥልት ነዉ።

ድምፅ

«ጄኔራል ፔትረየሰን (መካከለኛዉ ምሥራቅና እስያ የሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር አዛዥ) ብትጠይቋቸዉ ኢራቅ የተገኘዉ ዉጤት በከፊል የተገኘዉ እስላማዊ አክራሪዎች እንላቸዉ ከነበሩ ሐይላት ጋር በተደረገ መቀራረብ እንደሆነ ይነግሯችኋል።እነዚሕ ሐይላት ከኛ ጋር ለመሥራት ፈቃደኞች የሆኑት ደግሞ የኢራቁ አል-ቃኢዳ በሚከተለዉ ሥልት በገለላቸዉ ነዉ።በአፍቃኒስታንና በፓኪስታን ግዛቶችም ተመሳሳይ እድል የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታን ከዘመተበት ከጥቅምት ሁለት ሺሕ አንድ እስካሁን በተቆጠረዉ ጊዜ ከሰባት ሺሕ የሚበልጡ ታሊባኖች፤ ወደ አምስት ሺሕ የሚሆኑ የመንግሥት ወታደሮች ሞተዋል።ሲያንስ አስራ-አንድ ሺሕ ሲበዛ ሰላሳ ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ከአንድ ሺሕ አንድ መቶ የሚበልጡ የአሜሪካ መራሹ ጦር ባልደረቦች፥መቶ ያሕል የኮንትራት ሰራተኞች ሞተዋል።በቢሊዮን የሚጠር ገንዘብ ተከስክሷል።

የአሸባሪ-ደፈጣ ተዋጊዎቹ ጥቃት ከጊዜ-ወደ ጊዜ እየጨመረ-የሚጠፋዉ ሕይወት መጠንም እያሻቃበ ነዉ።ዛሬ ብቻ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ባፈነዱት ቦምብ አስራ-ሁለት እራሳቸዉን አጥፍተዋል።ኦባማ በርግጥ በቀጥታ ከታሊባኖች ጋር ልደራደር አላሉም።በተዘዋዋሪ የጠቆሙት የድርድር ፍንጭ-መርሕ ከሆነ ግን የእልቂት ጥፋቱን ኡደት በመንታ-ብልሐት ለመቀነስ ያለመ ነዉ።

የታሊባንን ማንነት ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት የለንደኑ እስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር አንቶኒዮ ጊዩስቶሲ እንደሚሉት ግን ድርድሩ በጎ ተስፋ የማጫሩን ያክል የቀቢፀ-ተስፋም ምንጭም ነዉ ባይ ናቸዉ።

ድምፅ

«ድርድር ምናልባት ወደ ሰላም የሚያመራ ፖለቲካዊ ሥልት ነዉ።ግን ወደ ሌላ ብዙ ነገሮች ያጉዝም ይሆናል።በአፍቃኒስታን ሁኔታ ድርድሮች ብዙ ጊዜ ወደ ሁለቱም አቅጣጫ ሲያመሩ ተስተዉሏል።ድርድር በተለይ በሙጃሂዲያኖቹ እና በፓኪስታን ወገን ባሉት በሁለቱ ወገኖች የካቡልን መንግሥት ለማወክ ይዉል ይሆናል።ሥለዚሕ ታሊባን በተለይ ዋናዉ ታሊባን እንበል ሙላሕ ዑመር ድርድሩን ይፈልጉታል።እዉነተኛ ግባቸዉ ግን ግልፅ አይደለም።እኔ በግሌ አሁን ካለዉ መንግሥት ጋር ሥልጣን ለመጋራት ይስማማሉ ብዬ አላምንም።»

ፕሮፌሰሩ የፈሩለት የፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ የሚፈራ አይመስልም። ፕሬዝዳት ካርዛይ የኦባማን መግለጫ እንደሰሙ ያሰብኩት የደረሰ አይነት ነዉ-ያሉት።

ድምፅ

«ሠላም ሥለሚወርድበት ሁኔታ ከለዘብተኛ ታሊባኖች ጋር ድርድር እንዲደረግ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳት ተቀበሉት።ይሕ ጥሩ ዜና ነዉ።መንግሥታችን ይሕን አቋም ከያዘ ቆይቷል።የአል-ቃኢዳ አባላት ካልሆኑ፥ በሽብር ምግባር ከማይሳተፉ፥ ወይም በዉጪ ሐይላት ግፊት በገዛ ሐገራቸዉ ጦርነት ከማያራምዱ የታሊባን ሐይላት ጋር ተባብረን ለመስራት ዝግጁ ነዉ።»

ካርዛይ ታሊባኖች ጥቃት ካቆሙ መንግሥታቸዉ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ከዚሕ በፊት አስታዉቀዉ ነበር።ባለፈዉ ሕዳር በግዙፎቹ የአለም ዜና ማሰራጫዎች ብልጭ-ብሎ ወዲያዉ ድርግም አለ አለጂ የአፍቃኒስታን መንግሥትና የታሊባን ተወካዮች በሳዑዲ አረቢያ ሸምጋይነት ድርድር ጀምሩ ተብሎም ነበር።

ፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ ከሥልጣን እስከተሰናበቱበት ድረስ የካርዛይን ዲሞክራሲያዊነት፤ ብቃት፤ ብልሐት፣ ያላሞገሱ-ያለወደሱበት ጊዜ አልነበረም። ብዙዎች እንደሚሉት ግን ካርዛይ የሐገራቸዉን ሠላም፣ ለማስከበር፣ የደሐ-ሕዝባቸዉን ኑሮ ለማሻሻል፣ በሙስና የተዘፈቁ ሾሞቻቸዉን ለመቅጣት ብዙ የፈየዱት የለም።ያም ሆኖ ካርዛይ ያሉትን ያሉት ለሐገር-ሕዝባቸዉ ሰላም ደሕንነት አስበዉ ሊሆን ይችላል።የዚያኑ ያክል ግን ድርድሩን ከካቡል ያላለፈ ሥልጣናቸዉን ለማጠናከሪያ፤ ለማራዘሚያ፥ ከኦባማ መስተዳድር የቡሽን አይነት ድጋፍ ለመገብያነት አያዉሉትም ማለትም ያሳስታል።

ካርዛይ ለምንም ያዉሉት ለምን የድርድሩን ሐሳብ ሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራትም ሳይደግፉት አልቀሩም።ባለፈዉ ሳምንት አፍቃኒስታንን የጎበኙት የጀርመኑ መከላከያ ሚንስትር ፍራስ-ዮሴፍ ዩንግ ታሊባኖች መደራደር ከፈለጉ አመፅ-ብጥብጥን እንዲያወግዙ አሳስበዋል።ይሕ ሒደት የድርድሩን ጠንካራናነት አመልካች ነዉ።የአለም አቀፍ አሸባሪነት ጉዳይ አጥኚ አሕመድ ሰኢዲ እንደሚሉት ግን ከታሊባኖች ጋር መደራደር ዘበት ነዉ።

«ከሁሉ በፊት ድርድሩ አይቻልም።ምክንያቱም ለዘብተኛ የሚባል ታሊባን የለም።የታሊባኖች የወጊያ አላማ ርዕዮተ-አለማዊ ነዉ።መርሐቸዉ እራሳቸዉ በሚፈቅዱትና በሚረዱት እስልምና ላይ የተመሠረተ ርዕዮት ነዉ።

፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧

የሰላም ብልፅግናዋ ጅምር ጉዞዋ የተስፋ-ወሬ፣ ከዉጊያ፣ ግድያ-ድሕነት፣ ከአደንዛዥ እፅ ማዕከልነቷ እዉነት ጋር እንደተጣረሰባት፤ የለጋ-ዲሞክራሲያዊነቷን ሽፋንን የመሪዎችዋ-ብቃት-እጠት፤ የሙሰኛ፤ አምባገነናዊታቸዉ እዉነት እየበረቀሰባት-ግራቀኝ ስትላጋ ሰባት አመት ያስቆጠረችዉ ሐገር ዛሬም ከሰላም ሩቅ ነች።አፍቃኒስታን።ከእንግዲሕ ወዴት እንዴት ትጓዝ ይሆን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ-ቸር ያሰማን።

ZPR (Ö-Töne), Reuters,dpa,wikipedia

Negash Mohammed

►◄