የአፍሮ-ቻይና ጉባኤ | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.11.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የአፍሮ-ቻይና ጉባኤ

«የምዕራባዉያን የገዢ ቡድናት ሥለ እኛ ሁኔታ የሚያዉቁት የለም።ደግሞ በዚሕ ላይ እነሱ የሌላዉን ጉዳይ የራሳቸዉ ያደርጋሉ።ቻይናዎች ግን ካንተ ጋር ነዉ የሚሠሩት።

ጉባኤዉ

ጉባኤዉ


የአፍሪቃና የቻይና መሪዎች ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ያደረጉት ጉባኤና የደረሱበት ሥምምነት አወንታዊም፣ አሉታዊም አስተያየት አስተከትሏል።ጉባኤዉ የአፍሪቃና የቻይናን ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ብዙዎች ይናገራሉ።የምዕራብ ሐገራት ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ግን ቻይና አምባገነን የሚባሉ መሪዎችን ሳይቀር ለጉባኤዉ መጥሯትዋ ምጣኔ ሐብታዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባሻገር ለሰብአዊ መብት መከበርና ለመልካም አስተዳደር መመስረት ሥፍራ አለመስጠቷን አመልካች ነዉ።።

በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርስቲ የቻይና የዉጪ መርሕ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ ዚዊንግ ባጭር፣ ግልፅ ቋንቋ ሁሉንም አሉት ትናንት።«ቻይና ደገሰች ሁሉም ታደመ።» ከድፍን አፍሪቃ- አምስቱ ሲቀሩ አርባ-ሥምንቱ የድግሱ ታዳሚዎች ነበሩ።ከአርባ ሥምንቱ የአፍሪቃ ሐገራት አርባ አንዱ በመራሔ መንግሥት ወይም በርዕሠ=ብሔር መወከላቸዉ ደግሞ ድግሱ በርግጥ ሁሉንም አፍሪቃዊ ያጓጓ-ያሳተፈ መሆኑን መስካሪ ነዉ።

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር የአፍሪቃ አቻዎቻቸዉን ወክለዉ ለጉባኤተኞች እንደነገሩት የቤጂንጉ ድግስ ብዙ የአፍሪቃ ታዳሚዎችን ያጓጓ-ያሳተፈበት ምክንያት የጋራ ጥቅምና ትብብር ነዉ።

«ቻይና እና አፍሪቃ የቆየ ትብብርና መደጋገፍ አላቸዉ።የቻይና-አፍሪቃ ወዳጅነት ደግሞ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አለዉ።በአዲሱ ዘመን ቻይናና አፍሪቃ ለትብብር ጠንካራ መሠረት የሚሆኑ የጋራ የልማት ግብ እና የተሳሳረ ጥቅም አላቸዉ።»

ዛሬ የታተመዉ የቻይና የኮሚንስት ፓርቲዉ ልሳን ፒፕለስ ዴይሊ ጋዜጣ በርዕሠ-አንቀፁ እንደፃፈዉም ጉባኤዉ ቻይናና አፍሪቃ የነበራቸዉን የቆየ ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነዉ።

ቤጂንግ ባንድ ጊዜ በርካታ የሐገራት መሪዎች ጉባኤ ሥታስተናግድ ቻይና የኮሚንስቱን ርዕዮተ-አለም መከተል ከጀመረች እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ከ1949 ወዲሕ ባለዉ ታሪኳ የመጀመሪያዉ ነዉ።ጉባኤዉና ከጉባኤዉ ተሳታፊዎች ከአስሩ ጋር የተፈራረመችዉ የአንድ-ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የንግድ ሥምምነት ቻይና እያደገ የመጣዉን ምጣኔ ሐብቷን ለመደጎም የሚኖረዉ ፋይዳ ብዙዎች እንደሚሉት ቀላል አይደለም።

ቻይና እስካሁን ለአፍሪቃ የምትሰጠዉን የልማት ርዳታ በእጥፍ አሳድጋ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ መወሰኗ ደግሞ ለአፍሪቃዉያን መልካም ዜና ነዉ።እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከግምት የማይገባዉ ቻይና እና የአፍሪቃ የንግድ ልዉዉጥ ባለፉት ሰወስትና አራት አመታት እየተንቻረ ነዉ።የቻይናዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዌን ጂባኦ ለጉባኤተኞች እንደነገሩት ደግሞ በሚቀጥሉት አራት አመታት ዉስጥ ቻይና ከአፍሪቃ ጋር የምታደርገዉን የንግድ ልዉዉጥ በአመት ወደ አንድ መቶ ቢሊዮን ከፍ ለማድረግ አቅዳለች።

የቻይና እና የአፍሪቃ መሪዎችን የደረሱበትን ሥምምነትና ዉል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ሳይቀሩ ለሁለቱም ወገኖች በተለይ ለአፍሪቃ የሚጠቅም በማለት አወድሰዉታል።የምዕራብ ሐገራት ፖለቲከኞች፤ የመብት ተሟጋቾችና አስተንታኞች እንደሚሉት ግን ቻይና በሰብአዊ መብት ረጋጭነታቸዉ የሚታወቁ የአፍሪቃ መሪዎችን ሳይቀር ለጉባኤ መጋበዝዋ ከጥቅሟ ባሻገር ለሕዝብ መብት ደንታ እንደሌላት የሚያመልክት።

የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳት ዩዌሪ ሙሳቬኒ ግን ምዕራቡን በማያገባዉ ይገባል ባይ ናቸዉ።
«የምዕራባዉያን የገዢ ቡድናት ሥለ እኛ ሁኔታ የሚያዉቁት የለም።ደግሞ በዚሕ ላይ እነሱ የሌላዉን ጉዳይ የራሳቸዉ ያደርጋሉ።ቻይናዎች ግን ካንተ ጋር ነዉ የሚሠሩት።አንተ ሐገርሕን ትወክላለሕ፣ እነሱ ደግሞ የራሳቸዉን ጥቅም ይወክላሉ።እና በቃ በሥራሕን ትሠራለሕ።»