1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ የፀጥታው ምክር ቤት ውክልና ጉዳይ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12 2017

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን መሪዎች ጋር በአህጉሩ ጸጥታ እና ደህንነት፣ በሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ፣ በዓለም የገንዘብ ተቋማት አወቃቀር ፍትሐዊነት እንዲሁም አፍሪካ ሕብረት በፀጥታው ምክር ቤት የፖለቲካ ውይይት ላይ ሊኖረው ስለሚገባ የፖለቲካ ውክልና ያለውን ቁርጠኝነት መነጋገራቸውን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4m6Sx
አዲስ አበባ በተደረገዉ በ8ኛዉ የአፍሪቃ ሕብረትና የተመድ የጋራ መድረክ ላይ የአፍሪቃ የዉክልና ጉዳይ ተነስቷል
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የአፍሪቃ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት።አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ዉክልና እንዲኖራት ሕብረቱ በተደጋጋሚ ጠይቋልምስል Solomon Muchie/DW

የአፍሪካ የፀጥታው ምክር ቤት ውክልና ጉዳይ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ የአፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ውክልና አልባ መሆን "በቅርቡ ይስተካክላል" የሚል እምነት ስለመኖሩ ፍንጭ ሰጡ።በ8 ኛው የአፍሪካ ሕብረት - የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ የትብብር መድረክ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት ጉቴሬዥ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት መሄን አለባቸው የሚለው በአብዛኛው የድርጅቱ አባል ሀገራት መግባባት መኖሩን ገልፀዋል።ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ የተገቢነት ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል ያሉ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ በራሱ ትልቅ ፈተና ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን መሪዎች ጋር በአህጉሩ ጸጥታ እና ደህንነት፣ በሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ፣ በዓለም የገንዘብ ተቋማት አወቃቀር ፍትሐዊነት እንዲሁም አፍሪካ ሕብረት በፀጥታው ምክር ቤት የፖለቲካ ውይይት ላይ ሊኖረው ስለሚገባ የፖለቲካ ውክልና ያለውን ቁርጠኝነት መነጋገራቸውን ገልፀዋል። አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አልባ መሆኑ "በቅርቡ ይስተካከላል ብለን ተስፋ እናድርግ" ሲሉ በድርጅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል። 

 

"የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው በአባል ሀገራት መካከል መግባባት አለ። የዚህ ማሻሻያ ዋና ጉዳይ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል መሆን እንዳለባቸው በአብዛኞቹ አባል ሀገራት ዘንድ ስምምነት መኖሩ ነው"

ቀጣይነት ያለው ግጭት የአፍሪካ መረጋጋት ፈተና መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ አዳራሽ ምረቃት ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሊኖረው የሚገባን ቋሚ ውክልና በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም አንፀባርቀዋል።

ለመሆኑ ለአፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውክልና ማግኘት ምን ፋይዳ አለው የሚለውን የጠየቅናቸው ስማቸውን ትተው ሀሳባቸውን የገለፁ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ዲፕሎማሲ ተንታኝ ተከታዩን መልሰዋል።

"በጸጥታው ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት እንድን ሀገር የተለየ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አይሰጣትም። የተለየ ፖለቲካዊ ጥቅም አይሰጣትም። ስለዚህ ከምዕራባዊያን ወይም  ከሌላ ፍላጎት ያለው ቡድን ከመደፈቅ የሚያድነን አይሆንም" 

ዋና ፀሐፊ ጉተሬሽ አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ አስታዉቀዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ አዲስ አበባ ዉስጥ በተደረገዉ የድርጅቱና የአፍሪቃ ሕብረት ስብሰባ ላይ ተካፍለዋልምስል William Volcov/ZUMA Press Wire/picture alliance

 

የተባበሩት መንግሥታት ይህንን የአወቃቀር ማሻሻያ ካፀደቀው ሀገራቱ ምን ሊሠሩ ይችላሉ? '

በመጀመርያ ደረጃ አፍሪካ እንደ አህጉር ምን ያህል ጠንካራ ማንነት አላት? ምክንያቱም የሚወከሉት ሀገራት አፍሪካን እብደ አህጉር ያላትን ጉዳይ በብቸኝነት እንዳይወሰንበት የማድረግ ፋይዳ ነው የሚኖረው። ከዚህ አንፃር በዚህ ደረጃ ልናምናቸው የምንችላቸው ሀገራት አሉ ወይ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው"

 

የትኞቹ የአፍሪካ ሀገራትስ ሊወከሉ ይችሉ ይሆን የሚለውም ሌላኛው ጥያቄ ነው።

"እነ ግብጽ፣ ናይጀርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ምናልባት ኬንያ ፣ ጋና አከባቢ ነው ሊሆን የሚችለው" ። 

ዋና ፀሐፊው ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር በሰጡት መግለጫ ስለ አፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ሁኔታ፣ ስለ ኢትዮጵያ እና መሰል ዝርዝር ጉዳዮች ያሉት ነገር የለም፣ ለጋዜጠኞችም የጥያቄ እድል ባለመስጠታቸው የድርጅቱን አቋም ለመረዳት አልተቻለም። ለመሆኑ በፀጥታው ምክር ቤት እንደ አህጉር መወከል ይቻላልን? የሚለውንም ባለሙያውን ጠይቀናል።

8 ኛው የአፍሪካ ሕብረት - የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ የትብብር መድረክ ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ተደርጓል
የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ጋር ተነጋግረዋልምስል Simon Maina/AFP

 

"ከአፍሪካ የሚወከሉ ሀገራት ምናልባት የሀገራቸውን ብቸኛ ፍላጎት ሊያራምዱበት ይችላል" 

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ እና ጊዜያዊ አባላት የሚሳተፉበት አግባብ ለረጅም ጊዜ የተገቢነት ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል ያሉት የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኙ፣ የፀጥታው ምክር ቤት በራሱ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ አወቃቀሩን ለማሻሻል መሞከር በራሱ ትልቅ ፈተና ነው ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ