1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ እና አሜሪካ መሪዎች ጉባኤ

ረቡዕ፣ ኅዳር 28 2015

የአፍሪካ እና የአሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ በመጪው ሣምንት በዋሽንግተን ዲሲ ይካሔዳል። ለሶስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ የፖለቲካ፣ ሰብዓዊ መብት እና የኤኮኖሚ ጉዳዮች ለውይይት የሚቀርቡበት ነው። የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ እና የአጎዋ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟሉ የአፍሪካ አገራት የንግድ ሚኒስትሮች በሥምምነቱ አተገባበር ላይ ውይይት ያደርጋሉ።

https://p.dw.com/p/4KcBI
Afrika Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የአፍሪካ እና አሜሪካ መሪዎች ጉባኤ

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ እና የአፍሪካ ሹማምንት በመጪው ሣምንት በአጎዋ የንግድ ሥምምነት አተገባበር ላይ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል። አርብ ታኅሳስ 7 ቀን 2015 የሚደረገው የሚኒስትሮች ስብሰባ የአጎዋ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟሉ የአፍሪካ አገራት የንግድ ሚኒስትሮች፣ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ኃላፊዎች ጭምር የሚሳተፉበት ነው። የኤኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር፣ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ እና መዋዕለ ንዋይ ማስፋት፣ ቀጠናዊ የንግድ ትሥሥሮችን መደገፍ የሚቻልባቸው መንገዶች ለውይይት የሚቀርቡበት እንደሆነ ለጉባኤው የተዘጋጀው መርሐ ግብር ያሳያል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት ሸቀጦቿን በአጎዋ ሥምምነት መሠረት ለአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድሏን ኢትዮጵያ ከታኅሳስ 23 ቀን 2014 ጀምሮ አጥታለች። የአፍሪካ የእድገትና የንግድ ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) ተብሎ ከሚጠራው ሥምምነት በመታገዷ ለሸቀጦቿ አማራጭ ገበያ ለማፈላለግ የተገደደችው ኢትዮጵያ ዕድሉን መልሶ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራትም እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም። 

በብሪታኒያው የልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ በደቡብ አፍሪካ ከተፈረመው የግጭት ማቆም ሥምምነት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ የግብይት ሥምምነት የመመለስ ዕድሏ መልካም ፍንጭ እንዳሳየ ቢታዘቡም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ግን አላጡትም። የአሜሪካ መንግሥት ጦርነቱ ሲጀመር ከነበረው አኳያ በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ መለሳለስ ማሳየቱን የገለጹት ዶክተር ቀልቤሳ እጅግ በአጭር ጊዜ ባይሆንም ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል የነበራትን ዕድል መልሳ ልታገኝ እንደምትችል ጠቁመዋል። ይሁንና ዶክተር ቀልቤሳ እንዳሉት በኦሮሚያ ክልል ዳግም ያገረሸው ደም አፋሳሽ ግጭት ተጨማሪ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን
ለጉባኤው የአሜሪካው ፕሬዝደንት 49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪማኅማትን ጋብዘዋል። የማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሱዳን እና ጊኒ መሪዎች ጭርሱን ግብዣ አልተላከላቸውም።ምስል Kevin Dietsch/Getty Images

በደቡብ አፍሪካ በተፈረመው የግጭት ማቆም ሥምምነት ጋብ ያለው ጦርነት ተጽዕኖ ያሳደረው በአጎዋ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ጭምር ነበር። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም በተካሔዱ ሰልፎች ውግዘት ከደረሰባቸው መካከል ኋላ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥትን ከህወሓት በማደራደር ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ወገኖች አንዷ የሆነችው አሜሪካ ነበረች። ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሑሴን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የመሻሻል አዝማሚያ ማሳየቱን ተናግረው ነበር።

በንግድ ልውውጥ እና በኤኮኖሚ ዘርፎች ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ያላት ግንኙነት ትልቅ ባይሆንም ዶክተር ቀልቤሳ እንደሚሉት በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ዳፋ ግን ሌሎች ጉዳዮችን ጭምር የሚያበላሽ ነው። "ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ትልቅ የንግድ ግንኙነት የላትም። ወይም ከአሜሪካ ካፒታል ገበያ በቀጥታ ገንዘብ አታገኝም። በተዘዋዋሪ ግን ዋና ዋና የገንዘብ ፍሰት ቧምቧዎች ከሞላ ጎደል ማብሪያ ማጥፊያው ከአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ስላለ [የሁለቱን አገሮች ግንኙነት] ጠቃሚ የሚያደርገው ያ ነው" ሲሉ ዶክተር ቀልቤሳ አስረድተዋል።

የአጎዋ የንግድ ሥምምነት ላይ የሚደረገው ውይይት በመጪው ማክሰኞ የሚጀመረው የአፍሪካ እና የአሜሪካ መሪዎች ጉባኤ አንድ አካል ነው። በዚህ ጉባኤ 49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪማኅማት ተጋብዘዋል። የማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሱዳን እና ጊኒ መሪዎች ጭርሱን ግብዣ አልተላከላቸውም።

USA-Afrika-Gipfel in Washington
የአፍሪካ እና አሜሪካ መሪዎች ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔደው ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሳሉ ነው።ምስል Reuters

በዚህ ጉባኤ ከባቢ አየር ለውጥን፣ አፍሪካ እና አሜሪካ የወደፊት የንግድ እና መዋዕለ ንዋይ ግንኙነትን የተመለከቱ ውይይቶች ይደረጋሉ። ሰላም፣ ጸጥታ፣ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የሲቪክ ድርጅቶችን የተመለከቱ ጉዳዮችም ውይይት እንደሚደረግባቸው የጉባኤው መርሐ ግብር ያሳያል። ይኸ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔደው ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሳሉ ነው።

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ኻሚላ ሐሪስ "ይኸ ጉባኤ አሜሪካ ለአፍሪካ አጋሮቻችን ያላትን ዘላቂ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ጉባኤው በመከባበር፣ የጋራ ጥቅሞች እና እሴቶች መርኅ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ኤኮኖሚያዊ ግንኙነታችንን ማጎልበት የጉባኤው አንድ ዓላማ ይሆናል" ብለዋል። ይኸ አሜሪካ ለአፍሪካ አጋሮቿ አላት የሚባለው ቁርጠኝነት ግን ለበርካታ ልሒቃን የሚዋጥ  አይደለም። እንዲያውም ቻይና በአፍሪካ ያላትን ተደማጭነት ለመገዳደር የሚደረግ የምዕራባውያኑ ጥረት አንድ አካል ሆኖ ይቀርባል። ይኸን ትችት ግን የአሜሪካ ሹማምንት የሚቀበሉት አይደለም።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን "አሜሪካ የተሻለ [የዕድገት] ሞዴል ማቅረብ ትችላለች ብለን እናምናለን። ይሁንና አፍሪካውያን እንዲመርጡ እየጠየቅን አይደለም" ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል። በአሜሪካ የንግድ መሥሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ አሩን ቬንካታራማን ባለፈው ዓርብ በሰጡት ጋዜጣዊ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር በንግድ እና መዋዕለ ንዋይ፣ ኢነርጂ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በእርሻ ንግድ እና ዲጂታል ኤኮኖሚ ዘርፎች ከአፍሪካ አገሮች ጋር የመተባበር ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል። ይሁንና ኃላፊው እንዳሉት የግሉ ዘርፍ ከፍ ያለ ሚና እንዲኖረው ትሻለች።አሩን ቬንካታራማን "የግሉ ዘርፍ በአሜሪካ እና የአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ሚና ለማፋጠን ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የሁለትዮሽ ንግድ እና መዋዕለ ንዋይ እንዲጎለብት ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር ከአፍሪካ መንግሥታት ጋር መስራት የአሜሪካ መንግሥት ሚና ነው" ብለዋል።

በዋሽንግተን በሚካሔደው የሶስት ቀናት ጉባኤ የኢትዮጵያ መሪዎች ከልዕለ ኃያሏ አገር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት የሚያደርጉበት ዕድል የሚፈጥር ይመስላል። ይሁንና ይኸ ጥረት ብርቱ ድርድሮች እና ጊዜ የሚሹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶክተር ቀልቤሳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት የሚከተለው አሰራር እና የተቋማቱ የተለያየ ሚና የሚያሳድሩት ተጽዕኖ መኖሩ አይቀርም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ