የአፍሪካ አውሮፓ ስብሰባ በሊቢያ | ኢትዮጵያ | DW | 30.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአፍሪካ አውሮፓ ስብሰባ በሊቢያ

ሊቢያ የአፍሪካና የአውሮፓ መሪዎችን ስብሰባ ለሁለት ቀናት አስተናግዳለች። በዚሁ የ8o ሀገራት መሪዎች ስብሰባ ላይ የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ ጠንከር ያለ 45 ደቂቃ የወሰደ ንግግር አድርገዋል።

default

45 ደቂቃ የፈጀውን የጋዳፊን ንግግር አንድ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት በማን አለብኝነት የተሞላ ሲሉ ነበር የገለጹት። ትላንት ተጀምሮ ዛሬ የተጠናቀቀው የአውሮፓና የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ትኩረት ያደረገው በኢኮኖሚ ትብብርና በስደተኞች ላይ ነው። ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚጎርፈውን ስደተኛ ለማቆም በእርግጥ አውሮፓውያኑ ድንበሮቻቸውን ዘግተው ጥብቅም መመሪያ አውጥተው እየተከላከሉ ቢሆንም ከአፍሪካውያን ትብብርን እንደሚሹ ነው ዛሬ በተጠናቀቀው የሁለቱ አህጉራት ስብሰባ ላይ የገለጹት። የኢኮኖሚው ጉዳይ ሰፊ ጊዜ ወስዶ መሪዎቹን አወያይቷል። አውሮፓውያኑ ከአፍሪካ ጋር ተባብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉ ሲያስታውቁ ከአፍሪካውያን በኩል በወቀሳና ማስፈራራት የታጀበ ምላሽ ነበር የገጠማቸው። በተለይም የስብሰባው አዘጋጅ ሀገር ሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ የመክፈቻ ንግግራቸው እንደአውሮፓውያኑ አገላለጽ ማን አለብኝነት እንደእሳቸው ግን ጠንካራ መልዕክት የሆነ ነበር። ጋዳፊ ምርጫዎች አሉን ተባብሮ ለመስራት ግን እኩልነት ይቀደም ባይ ናቸው።

ድምጽ

«እኛ አፍሪካውያን ሁለት ምርጫዎች አሉን። ከአውሮፓውያኑ ጎሮቤቶቻችንና ወዳጆቻችን ጋር በእኩልነት ተባብሮ መስራት። እዚህ ላይ በጥሬ ሀብት የበለጸገ ክፍለ ዓለም ያለን እንደመሆናችን መጠን አማራጮች አሉን።»

በእርግጥ የሞአመር ጋዳፊ የትላንቱ የመክፈቻ ንግግር በትላንቶቹ ቅኝ ገዢና ተገዢ ሀገራት መሀል ያለውን የከረመ ትኩሳት የቀሰቀሰ ነበር ተብሏል። ጋዳፊ አዲስ ግንኙነት እንፈልጋለን። ግንኙነቱ ግን በእኩልነት የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። አውሮፓውያን መልካም አስተዳደር፤ ሰብዓዊ መብት ይላሉ። አፍሪካ የምትፈልገው ፖለቲካ ሳይሆን ኢኮኖሚ ነውም ሲሉ ሞአመር ጋዳፊ ለአውሮፓውያኑ በግልጽ ነገሯቸው። አለበለዚያ አማሮጮቻችንን እንጠቀማለን። ፊታችንን ወደሌላ እናዞራለን።

ድምጽ

«ድሮ አውሮፓውያን ቅኝ ግዛት አድርገውን እንደነበር ሊዘነጋ አይገባም። ከአውሮፓውያን ጋር ትብብሩ ካልሰመረ እንደእነርሱ እኛም ምርጫ አለን። አፍሪካ ፊቷን ወደ ላቲን አሜሪካ፤ ሰሜን አሜሪካ፤ ቻይና፤ ህንድ ወይም ሩሲያ መመለስ ትችላለች።»

በሊቢያው የአፍሪካ አውሮፓ ስብሰባ ላይ የሱዳኑ መሪ ኦማር ሀሰን አልበሽርም አውሮፓውያኑ ላይ ጠንከራ ወቀሳ አቅርበዋል። አልበሽር በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የክስ ወረቀት ሲቆረጥባቸው አውሮፓውያን አቋማቸው ልክ አልነበርም ነው የሚሉት። የአውሮፓውያኑ ሁኔታ የአፍሪካ ህብረትና ሱዳን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሆነ የገለጹት አልበሽር ይህም በሁለቱ አህጉራት መሀል ሊኖር የሚችለውን ውይይትና ንግግር ዋጋ የሚያሳጣ ነው ብለዋል። የአፍሪካ ዋንኛ የልማት አጋርና ለጋሽ የሆነው የ27 ሀገራቱ ማህበር የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካውያን የገጠመው ብርቱ ፈተና ሊቢያ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል። በእርግጥ ህብረቱም አቋሙን ለአፍሪካውያኑ መሪዎች ከመግለጽ ወደ ኋላ አላለም። የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ኸርማን ቫን ሮምፑይ የአውሮፓ ተሞክሮ የሚሳየው የኢኮኖሚ ዕድገት ከመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጋር ሊነጣጠል ፈጽሞ አይቻለውም ብለዋል-እዚያው ትሪፖሊ ሊቢያ። ሮምፑይ ኢኮኖሚው ላይ እንተባበራለን ግን ሙስናን መታገስ የለብንም። የህግ የበላይነት መከበር አለበት። ግልጽነት ዋጋ ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬሌ የሊቢያው ስብሰባ እንደተጠናቀቀ በሰጡት መግለጪያ ለማሳየት የፈለጉት አውሮፓ በተለይም ሀገራቸው ጀርመን ከአፍሪካ ጋር ለመስራት እንደምትሻ ነው።

ድምጽ

«ይህ ስብሰባ የመቀራረብና የልውውጥ ነው። እዚህ ቦታ መገኘቴ ራሱ ጀርመን ለአፍሪካው አህጉር ያላትን ትኩረት የሚያሳይ ነው። ዑጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ ግልጽ የሆነው መልዕክት ጎረቤታችን የሆነችውን አፍሪካን በትብብር መደገፍ እንደምንፈልግ ነው። ትብብራችን በኢኮኖሚው ልውውጥ፤ በመሰረተ ልማት፤ በትምህርት፤ በግንባታ እንዲሁም ወጣቶቻችን የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ በማስቻል ይሆናል። አፍሪካ ትልቅ ችግር እንዳለባት ይታወቃል። እንደዚያውም ሰፊ ዕድል ያላትም አህጉር ናት። መጠነ ሰፊ ሀብት ተለግሳለች። ስለዚህ የአውሮፓ ህብረትም ሆነ የጀርመን መንግስት ከአፍሪካ ጋር ለመተባበር መፈለጋቸው ትክክለል ነው።»

በእርግጥ ስብሰባው ተጠናቋል። አፍሪካውያን ፖለቲካውን ትታችሁ በኢኮኖሚው ተባበሩን ይላሉ። አውሮፓውያን በድርሻቸው የምንደግፋችሁን በአግባቡ ለታሰበለት ዓላማ ማዋል አለባችሁ ሲሉ ይገልጻሉ። የሊቢያው የሁለቱ አህጉራት ስብሰባ ካንኩን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የከባቢ አየር ጉባዔ ላይም የጋራ አቋም እንዳልያዙ የታየበት ነበር። በአውሮፓውያኑ የተቀመረውንና የጋራ በሚል ሊወጣ የነበረውን የአቋም መግለጪያ አፍሪካውያኑ አልተቀበሉትም። አንድ አፍሪካዊ ዲፕሎማት ከአፍሪካውያን ይልቅ የአውሮፓውያኑን ጥቅም ያስቀደመ ብለውታል ተቀባይነት ያጣውን የአቋም መግለጪያ። አሁን አፍሪካውያን ምርጫዎች አሉን እያሉ ነው። በእርግጥ ቻይና ብራዚልና ህንድአሁን ላይ ብቅ ብለው ለአፍሪካውያን እንደ አማራጭ ቀርበዋል። ሰብዓዊ መብት፤ መልካም አስተዳደር፤ የህግ የበላይነት እንደ ቅድመ ሁኔታ የማያቀርቡ አማራጮች።

መሳይ መኮንን
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic