የአፍሪካ መሪዎች ደረጃ | ኢትዮጵያ | DW | 21.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአፍሪካ መሪዎች ደረጃ

የሞሪሺየሱ መሪ ከአፍሪካ የአንደኝነትን ደረጃ አግኝተዋል።የኤርትራው ኢሳያስ አሳያስ አፈወርቂ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

default

የአፍሪካ መሪዎች

ደረጃው ሃምሳ ሁለቱን የአፍሪካ መሪዎች በቅደም ተከተል አስቀምጧል። ከ ኤ እስከ ኤፍ ብሎም ከዚያ ያነሰ ውጤት ተሰጥቶአቸዋል። የኔሽን ሚዲያ ግሩፕ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የአፍሪካ መሪዎች የደረጃ ሰንጠረዥ የተለያዩ መመዘኛዎችን ያካተተ ነው። መሪዎቹ ምን እንደሰሩ፤ ምን እንደበላሸባቸው፤ የትኛው ጋ መጥፎ ደረጃ እንዳላቸው በዝርዝር አሳይቷል። ይህን ደረጃ ለመስጠት የተመሰረተው የሚዲያ ግሩፕ አባልና የአፍሪካ ሪቪው ከፍተኛ ተመራማሪ ሳማንታ እስፑን፤ የተለያዩ መለኪያዎችን ተጠቅመናል ይላሉ።

«መሪዎቹ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገቡትን ውጤት ለመገምገም ሞክረናል። የተለያዩ መለኪያዎችን ተጠቅመናል። የዲሞክራሲ ተሳትፎንና የሰው ልጅ የኑሮ ደረጃን የሚለካው የምህ ኢብራሂም ሰንጠረዥ፤ የህግ የበላይነትን፤ የዲሞክራሲ ደረጃን፤ የመንግስትን አሰራር፤ የፖለቲካ ተሳትፎን፤ ነጻው ፕሬስ የሚሰራበትን ከባቢ ሁኔታን፤ በዓለም ዓቀፉ ትራንስፓረንሲ ተቋም የሚወጣውን የሙስና ደረጃን እንዲሁም ጤናን፤ የትምህርት አቅርቦትንና ዓመታዊ ገቢን የሚያሳየውን የሰው ልጅ የኑሮ ሁኔታ ዕድገት መለኪያን ነው በመመዘኛነት የተጠቀምናቸው።»

በአፍሪካ የመሪዎች ደረጃ ውጤት ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡት ወይም ኤ የተሰጣቸው 5 መሪዎች ናቸው። የሞሪሺየሱ ሰር አኖርድ ጁግናውት ኤ+፤ የኬፕቨርዲው ፔድሮ ፒሬስ፤ የቦትስዋናው ያን ካማህና የጋናው ጆን አታ ሚልስ ኤ ሲያገኙ የናምቢያው ሉቃስ ፓሃምባ ኤ-፤ ተሰጥቶአቸዋል። የደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ ቢ+ ነው ያገኙት። በዚህም ውጤታቸው ከ1-6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የኢትዮዽያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በእርግጥ የመጨረሻው የሆነውን ኤፍ ውጤትም አላገኙም። ከ52 መሪዎች 39ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

«በሰጠነው ደረጃ አቶ መለስ ዜናዊ ጥሩ ውጤት አላስመዘገቡም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህም መኃል በዲሞክራሲ በኩል ያላቸው ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው። የፕሬስ ነጻነትን ፈጽሞ የሚያከብሩ አይደሉም። በሙስና ረገድ የተሰጣቸው ደረጃ በጣም ወደታች የወረደ ነው። የሰውልጅ የኑሮ ሁኔታን በሚለካው ደረጃ ላይም ቦታቸው ዝቅ ያለ ነው። በእርግጥ መልካም የሰሩትም አለ። ሆኖም በአብዛኛው ያገኙት ውጤት ዝቅተኛ ነው። አማካይ ሳይሆን ከአማካይ በታች ነው ያገኙት።»

በእርግጥ ይህ የደረጃ ሰንጠረዥ ጠቀሜታው አጠቃላይ ግንዝቤን ከመፍጠር ያለፈ ሊሆን አይችልም ይላሉ የአፍሪካ ሪቪው ከፍተኛ ተመራማሪ ሳማንታ እስቱን

«እንደ ተመራማሪ ይህ የወጣው ሰንጠረዥ የየሀገሩን ሁኔታ በተሻለ መልኩ ለመረዳት ያስቸለኛል። ስለየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ የተወሰነ ግንዛቤ ይሰጠኛል። የየሀገሩ ህዝብ በምን ሁኔታ እንዳለ፤ መሪዎቹ ምን እንደሰሩ ለማወቅ የሚረዳ ነው። በእርግጥ ለለጋሽ ሀገሮች ፖሊሲ እንዲቀረጽ የሚያደርግ ዓይነት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አልጠብቅም። እነሱ የራሳቸው መለኪያዎች አሏቸውና። ቢሆንም የተወሰነ መነሻ ሊሰጣቸው ይችላል። ዋናው ግን አጠቃላይ በሆነ መልኩ አፍሪካውያን እንዴት እንደሚሰሩና ደረጃቸው የት እንደሆነ ለማሳየት ነው። »

ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ ይፋ ባደረገው የደረጃ ሰንጠረዥ የምስራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች ወደታች ተቀምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 39፤ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ሼክ ሸሪፍ 48፤ የሱዳኑ መሪ ኦማር ሸሰን አልበሽር 51ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ 52ኛ ደረጃን ይዘዋል። ሸዋዬ ለገሰ ሂሩት መለሰ