የአፍሪካ መሪዎች ዓጎዋን ቢሮክራሲ ተቹ | የጋዜጦች አምድ | DW | 14.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የአፍሪካ መሪዎች ዓጎዋን ቢሮክራሲ ተቹ

ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሚኖረዉ የንግድ ግንኙነት ላይ የተዘረጋዉ ቢሮክራሲያዊ አካሄድ ነዉ በሚል አምስት የአፍሪካ መሪዎች ቅሬታቸዉን ገለፁ። እነዚህ መሪዎች ቅሬታቸዉን ለመገናኛ ብዙሃን ያቀረቡት ትናንት በኋይት ኃዉስ ከፕሬዝደንት ጆርጅ ደ. ቡሽ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነበር።

ምንም እንኳን መሪዎቹ በአገራቸዉ ላሰፈኑት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከፕሬዝደንት ቡሽ ሙገሳ ቢቸራቸዉም ዩናይትድ ስቴትስ አፍሪካን አስመልክቶ በምትከተለዉ የንግድ ግንኙነት ደስተኛ አለመሆናቸዉን አልሸሸጉም።
በትናንትናዉ ዕለት ጆርጅ ቡሽ የቦትስዋና፤ ጋና፤ ሞዛምቢክ፤ ናሚቢያና ኒጀር ፕሬዝዳንቶችን በኋይት ኃዉስ ተቀብለዉ ሲያነጋግሩ መሪዎቹን በየአገራቸዉ ላካሄዱት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምስጋናን ነበር ያስቀደሙት።
ምስጋናዉን ቢቀበሉም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የንግድ ግንኙነት ለመጀመር አገራቸዉ ልትደርስበት የሚገባ የምጣኔ ሃብት እርከን መኖሩን በመቃወም ነዉ እነዚህ አምስት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጉዳዩን የተቹት።
ከፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ጋር የነበራቸዉን ስብሰባ እንደጨረሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም አገራቸዉ ለአፍሪካ የልማት እድል በሚሰጠዉ ህግ ማለትም ዓጎዋ መሰረት ምርቷን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መላክ ከመጀመሯ በፊት የለየላት ድሃ መሆን እንዳለባት ነዉ የተናገሩት።
ይህ ህግ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር በሚደረግ የንግድ ግንኙነት በተለይ ልብስና ጨርቃ ጨርቅን አስመልክቶ በዩናይትድ ስቴትስ የተዘረጋዉን ጋሬጣ ማጥፋት ችሏል።
በዉሉ መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ነፃ ምጣኔ ሃብታዊ መንገድ መከተላቸዉ፤ የህዝብ የነበሩ ንብረቶቻቸዉን ወደግል ማዞራቸዉ፤ በግል ንግድ ዉስጥ ያላቸዉ ጣልቃ ገብነት ከቀነሰና የዩናይትድ ስቴትስን የመሰለ ስርዓት መዘርጋታቸዉ ከተረጋገጠ የሚፈለግባቸዉን የጥራት ደረጃ በመጠበቅ ምርቶቻቸዉን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መልኩ መላክ ይችላሉ።
የቦትስዋናዉ ፕሬዝደንት ፌስቱስ ሞጌይ እንደገለፁት ይህን ሁሉ መርምሮ ለንግዱ ዉል የይለፍ ሰርተፊኬት የሚሰጠዉ አሰራር የአፍሪካ አገራትን ምጣኔ ሃብት በእጅጉ የሚጎዳ ነዉ።
ሞጌይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከሆነ አምስቱ ፕሬዝዳንቶች ይህን ጉዳይ አስመልክተዉ በተወያዩበት ወቅት በተለይ በእሳቸዉ አገር በኩል ያለዉን ቢሮክራሲ አምርረዉ በመቃወም ትችታቸዉን ለቡሽ አቅርበዋል።
ቡሽም የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸዉ ኮንደሌዛ ራይስ ጉዳዩን በጥልቀት መርምረዉ መፍትሄ እንደሚፈልጉለት ቃላቸዉን ሰጥተዋል።
መልካም አስተዳደርን፤ ዲሞክራሲን፤ የሰብዓዊ መብቶችን ማክበርንም ሆነ ነፃ የምጣኔ ሃብት ይዘትንና ፓሊሲን በተመለከተ ማንም መጥቶ ቢያየን የምናፍር አይደለንም ይላሉ ሞጌይ።
የእነሱ የጋራ ስጋት አንድ ነዉ የአንድ ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ። ይህ ሲነሳ ይላሉ ሞጌይ እናንተ የለየላችሁ ድሃ አገራት አይደላችሁም ልንባል እንችላለን። ሆኖም ግን እኛ ድሆች ነን።
የዓጎዋ ህግ ከመነሻዉ የተቀረፀዉ ከ1992 እሰከ 2000ዓ.ም. ለስምንት ዓመታት እንዲያገለግል ነበር። አሁን ግን ቡሽ ባደረጉት ማስተካከያ መሰረት እስከ 2007ዓ.ም. ድረስ እንዲዘልቅ ተደርጓል።
ከቅሬታቸዉ ባሻገር ደግሞ ይህ ዕቅድ ለጎስቋላዉ ህዝባቸዉ መጠነኛም ቢሆን አዎንታዊ ዉጤት እንደሚያስገኝና ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜም በመራዘሙ ደስተኞች ነን ይላሉ የቦትስዋናዉ መሪ።
የድሃ አገራትን የምጣኔ ሃብት ሁኔታን በማሻሻል ረገድ ዓጎዋ የሚያበረክተዉ አስተዋፅዖ እንዳለም ያምናሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ በመላክ ረገድ በሌሴቶ የታየዉ የኢንዱስትሪ እድገት የዓጎዋ ዉጤት ነዉ ባይ ናት።
በዚሁ ሳቢያም በጋና 1,000 የስራ ዕድል መፍጠር ሲቻል ማላዊም ወደ 70,000 የሚጠጋ አዲስ የስራ መስክ መክፈት ችላለች።
በአንፃሩ የልማት ቡድኖች ዩናይትድ ስቴትስ ገበያዋን ለተወሰኑ ምርቶችና አገራት ብቻ በማድረጓ በዚህ ዕቅድ መጠነኛ መሻሻል ነዉ የታየዉ ይላሉ።
በአፍሪካ የሚገኙ ቁልፍ የንግድ አጋሮቿም ናይጀሪያ፤ አንጎላና ጋቦንን ጨምሮ ዋነኛ የነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች ብቻ ናቸዉ።
ዓጎዋን መሰረት በማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ የምታስገባዉ ከነዳጅ ሻጩዋ ናይጀሪያ 66.3 በመቶ፤ ከደቡብ አፍሪካ 11.8 በመቶና ከጋቦን 8.3 በመቶ ነዉ።
ሌሎች ምርታቸዉን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚልኩ የአፍሪካ አገራት ዋናዎቹ ሌሴቶ፤ ኮንጎ፤ ማዳጋስካርና ኬንያ ናቸዉ።
የኋይት ኃዉስ መረጃ እንደሚያሳየዉ ባለፈዉ አመት ከሰሃራ በታች ላሉ አገራት ዩናይትስ ስቴትስ የምትልከዉን 25 በመቶ ከፍ ስታደርግ የዓጎዋ ህግ ከሚፈቅድላቸዉ አገራት ያስገባችዉ ደግሞ ወደ88 በመቶ ጨምሯል።
የትላንቱ ስብሰባ በኋይት ኃዉስ የተካሄደዉ ከመጪዉ ሐምሌ 11 እስከ 13 በዳካር ሴኔጋል ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገራት ጋር ያላት የንግድና የምጣኔ ሃብት ትብብር ላይ የሚወያይ ጉባኤ ዝግጅት ዋዜማ ላይ ነዉ።
ጉባኤዉ የሚኒስቴር መስሪያቤቶችን፤ የግሉን ዘርፍና የሲቪሉን ማህበረሰብ እንደሚያካትት ይጠበቃል።