የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ዉሳኔ | የጋዜጦች አምድ | DW | 11.01.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ዉሳኔ

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት የወሰደዉን ስብሰባ በትናንትናዉ እለት ጋቦን ዉስጥ ሲያጠናቅቅ በተለይ የወቅቱ የአህጉሪቱ ችግሮች ያላቸዉን ሶስት አበይት ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበትን የመፍትሄ ኃሳብ አሳልፏል።

የተለያዩ አገራት መሪዎች የተሳተፉበት ይህ አህጉራዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረዉ ስብሰባ የአፍሪካ አገራት በአህጉሪቱ በየማዕዘኑ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ባስቸኳይ ማብረድ ካልቻሉ ግጭቶቹ እየሰፉ ለአካባቢዉና ለጎረቤት አገራትም አደጋ እንደሚሆኑ ማሰብ እንደሚገባ ተነጋግረዋል።
በስብሰባዉ ወቅት ከፍተኛዉን ትኩረትና የዉይይት ሰዓት የወሰደዉ በአይቮሪኮስት፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎና በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል ዳርፉር በመካሄድ ላይ የሚገኘዉ ግጭት ነበር።
ከሌሎቹ አቻዎቻቸዉ ከኮንጎዉ ጆሴፍ ካቢላና ከሩዋንዳዉ ፓል ካጋሜ ጋር በመሆን በየአገሮቻቸዉ ስላሉት መፍትሄ አልባ ግጭቶች ለመነጋገር የአይቮሪኮስቱ ላዉረንት ጋባግቦም ረጅም ሰዓት በወሰደዉ ዉይይት ተሳትፈዋል።
የአህጉሪቱ መሪዎች በአይቮሪኮስት ያለዉን ዉጥረት ለማርገብ ለፕሬዝዳንቱ እንደ አንድ አማራጭ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በአገሪቱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ህዝባዊ ዉሳኔ ይሰጥ የሚል ነዉ።
በአገራቸዉ በሚካሂዱት ጦርነትና ግጭቶች ባላቸዉ ሚና ሳቢያ ከአህጉሪቱ መሪዎች በተደጋጋሚ ወቀሳ የቀረበባቸዉ ገብግቦ በአሁኑ ስብሰባ ይገኛሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።
ባለፈዉ ወር የአይቮሪኮስት ባለስልጣናት አወዛጋቢዉን የህገ መንግስታቸዉን 35ኛ አንቀፅ በማስወገድ ማሻሻያ ለማድረግ ተስማምተዋል።
የአንቀፁ ፍሬ ነገር በአገሪቱ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ወላጆቻቸዉ አይቮሪኮስታዊ መሆን አለባቸዉ የሚል ሲሆን ይህም አብዛኛዎቹን ቅይጥ ዜግነት የያዙ እንደ አላሳኔ ኡታራ ያሉትን ያገሪቱን ታዋቂ የፓለቲካ ሰዎች እንዳይሳተፉ የሚያግድ ነዉ።
የኤኮኖሚ ጠበብት እንደሆኑ የሚነገርላቸዉ ኡታራ ከዚህ በፊት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ የታገዱት እናታቸዉ የቡርኪናፋሶ ተወላጅ ናቸዉ በሚል ነበር።
ጠበቃቸዉ ያቀረቡት የዉርሰ ዘር ህክምና ምርመራ ዉጤት ግን የኡታራ እናት አይቮሪኮስታዊ መሆናቸዉን የሚያሳይ እንደሆነ ነዉ የሚናገሩት።
ከ16.8 ሚሊዮን የአይቮሪኮስት ህዝብ መካከል አንድ አራተኛ የሚሆነዉ የዉጪ ዝር ቅይጥ እንዳለዉ የሚታወቅ ሲሆን አይቮሪኮስታዉያን የሚለዉ የተዛባዉ የአገሪቱ ብሄራዊ መተዳደሪያ እነዚህን ዜጎች የአገሪቱን መታወቂያ እንዳይዙና መሬት እንዳይኖራቸዉ ያግዳል።
የገባግቦ ተቃዋሚዎች ይህን መሰሉ መሻሻል በአለም ከፍተኛ ካካዎ አምራች በሆነችዉ አገር እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኗል በማለት ላላፉት ሁለት አመታት ሲቃወሟቸዉ ቆይተዋል።
የ15ቱ አገራት መሪዎችም የተባበሩት መንግስታት በአይቮሪኮስት ጉዳይ ላይ ያሳለፈዉን ዉሳኔ በመጥቀስ የጦር መሳሪያ እገዳ በአስቸኳይ እንዲጣልባት የጠየቀ ሲሆን ይህም እገዳ ለሌሎች ተጨማሪ እገዳዎች መንገድ የሚከፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በተጨማሪም መሪዎቹ የተባበሩት መንስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት የሰላም አስከባሪ ጦሩን በአይቮሪኮስት ካለዉ በበለጠ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ዲሞክራቲክ ኮኖጎን በተመለከተም በተለይም ምስራቃዊዉ የአገሪቱ ክፍል በአማፅያን ቁጥጥር ስር የመሆኑ ሁኔታ መሪዎቹን ያነጋገረ ግዳይ ነበር።
ኮንጎ ወታደሮቼ ላይ አማፅያን ለሚያደርሱት ጥቃት ከሩዋንዳ ድጋፍ ያገኛሉ ስትል በተደጋጋሚ ክስ አቅርባለች።
ሩዋንዳም በበኩሏ በምስራቅ ኮንጎ መሽገዋል የምትላቸዉን የሁቱ አክራሪዎች ትጥቅ በማስፈታት ሰበብ ወታደሮቿን ወደኮኖጎ እንደምትልክ ተናግራለች።
ቡድኑ በምስራቃዊ ኮንጎ ዉስጥ መገኘቱን የተገነዘቡት የአፍሪካ መሪዎችም የአካባቢዉ ዋነኛ የደህንነት ችግር መሆኑን በማመን የአፍሪካ ህብረት ጠንከር ያለ እርምጃ መዉሰድ እንደሚኖርበት ተስማምተዋል።
ለዚህም እንደመፍትሄ ያቀረቡት የአለም አቀፍ ህብረተሰብን ድጋፍ በመያዝ ኮንጎ የሁቱ አማፅያንን ትጥቅ ለማስፈታት እንድትችል ከጎኗ መቆምን ነዉ።
በሱዳን መንግስትና በአማፅያኑ መካከል በቅርቡ የተፈረመዉ የሰላም ዉል በምዕራቡ ክፍል በዳርፉር ያበረደዉን ግጭት ለማስቆም እንደ አንድ የመፍትሄ ምንጭ ሊያገለግል ይችላል ባይ ናቸዉ።
የአፍሪካ መሪዎች የሱዳንን መንግስት ጦሩ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት ወደኋላ እንዲመልስና በፊት የነበበት ግዛት ላይ እንዲያሰፍር ባለፈዉ ወር ጠይቀዉት ነበር።
በመቀጠልም መሪዎቹ አማፅያኑ ሁኔታቸዉን በማሳወቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያከብሩ ተማፅነዋቸዋል።
ሆኖም የመሪዎቹ ጥረት የአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ቢሆንም አለም አቀፉ ህብረተሰብ ከነ ችግሮቻችንን ይተወን ማለታቸዉ እንዳልሆነም ሳይገልፁ አላለፉም።
በርካታ የአፍሪካ አገራት ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ለመላክ ይተባበራሉ የአፍሪካ ህብረት ዋነኛዉ ችግር ግን ያንን ማንቀሳቀስ የሚያስችል የገንዘብ እጥረት ነዉ።
በአሁኑ ስብሰባቸዉ የአህጉሪቱ መሪዎች በተለይ በሶስቱ አገራት ችግሮች ላይ ለማተኮር የፈለጉት የአገራቱ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ፤ የምጣኔ ሃብትና የህዝብ አሰፋፈር ሁኔታ በአህጉሪቱ ልማት ላይ ያለዉን ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት እንደሆነም ገልፀዋል።


ተዛማጅ ዘገባዎች