የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ምርጫ እና አንደምታው | አፍሪቃ | DW | 08.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ምርጫ እና አንደምታው

የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት እየመሩ የሚገኙት ደቡብ አፍሪካዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ለመሪነት ቦታው በድጋሚ እንደማይወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ተተኪያቸውን ለመምረጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ መንፈቅ አለፈው፡፡ የህብረቱ ኮሚሽን ዕጩዎች የሚከራከሩበት መድረክ ለነገ አርብ ህዳር 30 አዘጋጅቷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:00 ደቂቃ

የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተዋል

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለነገ ያዘጋጀው የክርክር መድረክ በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው ተብሎለታል፡፡ የህብረቱን የወቅቱ ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ለመተካት እየተወዳደሩ የሚገኙ አምስት ዕጩዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከአምስቱ ዕጩዎች ውስጥ አራቱ በአሁኑ ወቅት አገራቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን ቀሪው የተባበሩት መንግስታት ልዩ ልዑክ ሆነው በመስራት ላይ ያሉ ናቸው፡፡

ከአምስቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለቱ ሴቶች ሲሆን ሁለቱም ምርጫውን ያሸንፋሉ የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አንደኛዋ የቦስትዋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒሎኖሚ ቬንሶን-ሞይቶይ ሲሆኑ ባለፈው ሐምሌ ኪጋሊ ላይ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ለመጨረሻ ዙር ካለፉ ሁለት እጩዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ሆኖም የሀገራቱን ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ባለማግኘታቸው መሪነቱን መጨበጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ከሐምሌው ጉባኤ በኋላ የምርጫ ውድድሩን የተቀላቀሉት ሌላኛዋ እንስት የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና ሞሃመድ ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቦትስዋና አቻቸው ተገዳዳሪ ሆነዋል፡፡ የአፍሪካ ኮንፌደንሺያል መጽሔት የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አንድሪው ዌየር ከአሚና ተቀባይነት ማግኘት ጀርባ ያለውን ምክንያት ያብራራሉ፡፡

“እርሳቸው እያገኙ ያሉት ድጋፍ ኬንያ እንደሀገር ለጉዳዩ እያደረገች ባለችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና ዝግጁነት ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ እንደምንረዳው ኬንያ ለጉዳዩ ትልቅ ክብደት ሰጥታለች፡፡ አባል ሀገሮች የእርሳቸውን ዕጩነት እንዲደግፉ ለማድረግ ብዙ ውለታዎችን ቃል ገብታለች ”ይላሉ።  

በሚኒስትርነት ከመሾማቸው አስቀድመው ኬንያን በአምባሳደርነት ያገለገሉት እና በተባበሩት መንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የሰሩት አሚና ለህብረቱ ሊቀመንበርነት እንደሚወዳደሩ ያሳወቁት ባለፈው መስከረም መጨረሻ ነበር፡፡ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አማካኝነት ይፋ የተደረገው የሚኒስትሯ ዕጩነት እንደ ምስራቅ አፍሪካ ማህብረሰብ እና ኮሜሳ ካሉ ቀጠናዊ ተቋማት ድጋፍ ያገኘው ወዲያውኑ ነበር፡፡ ለዚህም የፕሬዚዳንት ኬንያታ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እንደ አፍሪካ ኮንፌዴንሺያል አንድ ዘገባ ከሆነ ኬንያታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ለሊቀመንበርነት እንዲመረጡ ሰባት ሚኒስትሮችን ያቀፈ የማግባባት ዘመቻ የሚመራ ቡድን አቋቁመዋል።፡ ፕሬዝዳንቱ ከዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) ጋር በነበራቸው እሰጥ አገባ ወቅት የተጠቀሙትን አይነት የማግባባት ዘመቻ ለምርጫውም መጠቀማቸው ተነግሮላቸዋል፡፡

የኬንያታ ጥብቅ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት አሚና ከተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት በህብረቱ አማካኝነት በፍርድ ቤቱ ላይ ያሳዩትን አቋም ይበልጥ ያጠብቁታል ተብሎ ተገምቷል፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ ግን ኬንያም ሆነች ፕሬዝዳንቷ ከፍርድ ቤቱ ጋር በተያያዘ እንደቀድሞው የሚያሳስባቸው ነገር የለም ባይ ናቸው፡፡

“ኬንያ በዚያ ጉዳይ የነበረውን ሂደት ተወጥታዋለች፡፡ ፊት ለፊት ከመጋፈጥም ሸሸት ብላለች፡፡ የአይ.ሲ.ሲ ጉዳይ ለኬንያ ከአጀንዳዋ ውጭ ነው፡፡ ምክንያቱም በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈጽማችኋል በሚል በኡሁሩ ኬንያታ እና ዊሊያም ሩቶ ላይ የተከፈተው መዝገብ እንዳይቀጥል ተወስኗል፡፡ ስለዚህ እነርሱን በተመለከተ አንገብጋቢ ሁኔታ የለም” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማንም ይሁን ማን ዋናው ጥያቄው መሆን ያለበት “የፖሊሲ ለውጥ ይዞ ይመጣልን?” የሚለው መሆን እንዳለበት የሚከራከሩ አሉ፡፡ አንድሪው ዌየር ይህን መመለስ ከባድ እንደሆነ ይነገራሉ፡፡

“ለእኔ ከተጨባጭ የፖሊሲ ለውጦች ይልቅ ሊቀ-መንበሩ የሚሰሩት ስራ ያመዝንብኛል፡፡  ምክንያቱም መንፈሱን የሚወስነው እሱ ነውና፡፡ የአንድ ሀገር ፕሬዝዳንት ወይም ንጉስ እንደ ርዕሰ ብሔርነቱ የዚያን ሀገር ሁለንተናዊ አቅጣጫ እንደሚወስነው እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ደግሞ የመንግስቱን ተጨባጭ ስራ እንደሚያከናውነው ማለት ነው፡፡ [አሚና] ሞሀመድ በአህጉሪቱ ውስጥ የቀረውን የቅኝ ግዛት የመጨረሻ ርዝራዥ ለማስወገድ ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙዎችን እያነጋገረ ባለው የወቅቱ ትልቅ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ጉዳዩ ሞሮኮ ከምዕራብ ሰሐራ ጋር በነበራት ጸብ የራቀችውን የአፍሪካ ህብረት በድጋሚ ለመቀላቀል ማመልከቷ ነው” ሲሉ ተጠባቂ የሚሏቸውን የፖሊሲ ጉዳይ ይተነትናሉ፡፡

የሊቀመንበርነት ምርጫው በሚካሄድበት እና በጥር ወር በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው የመሪዎች ስብሰባ በፊት ኬንያ እና ሞሮኮ አሁን እያደረጉት እንዳለው አይነት የሰጥቶ መቀበል ስምምነቶች በብዛት እንደሚኖሩ የፖለቲካ ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡ ኬንያዊቷ እጩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለእርሳቸው ዕጩነት ላሳየችው ድጋፍ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ የተላከ የምስጋና ደብዳቤም አቅርበዋል፡፡      

ተስፋለም ወልደየስ         

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic