የአፍሪቃ ፀጥታና የፀጥታ ጉባኤ | ዓለም | DW | 18.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍሪቃ ፀጥታና የፀጥታ ጉባኤ

አሸባብ- የምሥራቅ፤ ቦኮ ሐራም-የምዕራብ አፍሪቃን ሠላምና ፀጥታ እንደሚያናጉ ከተነገረ፤ ከተዘመተባቸዉም አስር ዓመት ደፈነ።ሁለቱ ቡድናት እና ብጤዎቻቸዉ ሌሎች አሸባሪ ቡድናት ሌላ ሥፍራ ካደረሱት ጥፋት በላይ አፍሪቃ ዉስጥ ማጥፋታቸዉን ለማወቅ አስር ዓመት የፈጀበት ምክንያት በርግጥ ሊያነጋግር ይገባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:26

የአፍሪቃ ፀጥታና የፀጥታ ጉባኤ

ቦኮ ሐራም ከሁለት ዓመት በፊት ያጋታቸዉን ልጃገረድ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ፤ በእጅጉ የናጄሪያ ፤በጣሙን የሐያሉ ዓለም መንግሥታት አለመቻላቸዉ ወይም አለመፈለጋቸዉ ናጄሪያዉያንን ለአደባባይ ሰልፍ ዉግዘት ዳግም ሲያሳድም የሐገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሌሼጎን ኦባሳንጆ ባሕር ዳር ዉስጥ ሥለ አፍሪቃ ፀጥታ ይመክሩ-ያወራሉ።የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ መንግሥታቸዉ የአፍሪቃን ፀጥታ ለማስከበር ሥላደረገዉ ጥረት-አስተዋፅኦ እዚያዉ ባሕር ዳር ዉስጥ ሲናገሩ የኢትዮጵያን ድንበር የጣሱ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች መቶዎችን ጨፈጨፉ፤።ከጣናዉ ጉባኤ በፊት አዲስ አበባ ላይም ሥለ አፍሪቃ ፀጥታ የመከረ ሌላ ጉባኤ ነበር-የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ።የሰሞኑ ጉባኤ፤የአፍሪቃ ፀጥታና የፀጥታ እጦት ያፍታ ዝግጅታችን ርዕስ ነዉ።

አፍሪቃ በደቡብ አፍሪቃ በኩል የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያን በ2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሥታስተናግድ «አሁን ተራዉ ለአፍሪቃ ነዉ» እያለች አዚማ- አቀንቅና ነበር-እዉቋ ኮሎምቢያዊት-ሊባኖሳዊት ድምፃዊት ሸኪራ ኢሳብል መባረክ-This time for Africa።ዘንድሮ በስድስተኛ ዓመቱ ደግሞ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ (Münchner Sicherheitskonferenz) አሁን ተራዉ የአፍሪቃ ፀጥታ ነዉ-አለ።ወይም ያለ መሠለ።«ለአፍሪቃና የአፍሪቃን ፀጥታ ቀዳሚ አጀንዳችን ማድረግ አስፈላጊ ነዉ።»

የጉባኤዉ አዘጋጅ ድርጅት የበላይ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር።የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ ከተመሠረተ ከ1930 ጀምሮ አዉሮጳ- አሜሪካ (ሰሜንና ደቡብ)፤ እስያ-ኦሺኒያን በተደጋጋሚ አዳርሶ ከብዙ ዉዝግብ፤ ጭቅጭቅ፤ ጉቦና ምልጃ በኋላ በ80ኛ ዓመቱ አፍሪቃ መድረሱ ብርቅ ሆኖ አፍሪቃዉያንን ብዙ አስደስቶ ብዙ አስቦርቆ ነበር።የሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ (MSC በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የሚል፤የሚያደርገዉ እንደ እግር ኳሱ የሚያዝናና ሳይሆን-የሚያሳስብ በመሆኑ እነሻኪራ የሚያቀነቅኑ-አፍሪቃዉያን የሚቦርቁበት ምክንያት የለም። ዓለማዉ የፀጥታ ሥጋትን በጋራ ማስወገድ በመሆኑ ሕይወት፤ ሐብት ንብረትን ከጥፋት ለማዳን ጠቃሚነቱ አያጠይቅም።

የጣና የፀጥታ ጉባኤ የቦርድ ሊቀመንበር የናጄሪያ የቀድሞ ጄኔራልና ፕሬዝደንት ኦሌሼጎን ኦባሳንጆ ትናንት እንዳሉት የሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ የአፍሪቃን የፀጥታ ችግር አጢኖ ከጣናዉ ጉባኤ ጋር ለመተባበር መወሰኑ በጣም ጥሩ ነዉ።«ዘንድሮ የወዳጅነታችንን ጥንካሬ የሚያመለክት እርምጃ ወስደናል።በተለይ ከሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ ጋር ያደረግነዉ ትብብር በጣም ጥሩ ነዉ።»

የጣና የፀጥታ ጉባኤ ከተመሠረተ-ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱ ነዉ።በየዓመቱ ደቡብ ጀርመናዊቱ ከተማ ሙኒክ ላይ የዓለም መሪ፤የጦርና የስለላ ሐላፊዎችን ከሚወያየዉ ግዙፍ ድርጅት ጋር ለመተወዋወቅ ወይም ለመተባበር አምስት ዓመት ፈጅቶበታልማለት ነዉ።የሙኒኩ ጉባኤ ራሱ የተጀመረዉ በ1963 ነዉ።ሥለ አፍሪቃ ፀጥታ የተናጋገረዉን የአዲስ አበባዉን «የዋና-ቡድን» ጉባኤ ያለዉን ስብሰባ የጠራዉ ግን በ53ኛ ዓመቱ ዘንድሮ-ባለፈዉ ሳምንት ነዉ።እስከ ዛሬ የት ነበር? ወይስ አፍሪቃ ፀጥታዋ የተከበረ ሠላማዊት ነበረች?

የጉባኤዉ አስተናጋጅ ድርጅት የበላይ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር እንደሚሉትቦኮ ሐራም እና አ-ሸባብን የመሳሰሉ አሸባሪ ደፈጣ ተዋጊዎች በአፍሪቃዉያንና አፍሪቃ ዉስጥ ያደረሱት ጥፋት፤ አልቃ ኢዳና ISIS አፍቃኒስትን፤ ኢራቅ፤ ወይም በድፍን መካከለኛዉ ምሥራቅ ካደረሱት የበለጠ ነዉ።«እዚሕ ጀርመን ብዙ ሰዉ ለማመን ይችገር ይሆናል።ይሁንና ቦኮ ሐራም እና ሌሎች አሸባሪ ቡድናት አፍሪቃ ዉስጥ የገደሉት ሰዉ ቁጥር፤ አል-ቃኢዳ አፍቃኒስታን ዉስጥ ወይም አዲሱ አሸባሪ ድርጅት ISIS መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ከገደሉት ይበልጣል።እነዚሕ እኛን አዉሮጳዉያንን በጣም የሚያሳስቡ አለመረጋጋቶች፤ሽብርና ሽብርን ወደ ዉጪ የመላክ ስጋቶች ናቸዉ።»

አሸባብ- የምሥራቅ፤ ቦኮ ሐራም-የምዕራብ አፍሪቃን ሠላምና ፀጥታ እንደሚያናጉ ከተነገረ፤ ከተዘመተባቸዉም አስር ዓመት ደፈነ።ሁለቱ ቡድናት እና ብጤዎቻቸዉ ሌሎች አሸባሪ ቡድናት ሌላ ሥፍራ ካደረሱት ጥፋት በላይ አፍሪቃ ዉስጥ ማጥፋታቸዉን ለማወቅ አስር ዓመት የፈጀበት ምክንያት በርግጥ ሊያነጋግር ይገባል።

የሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ «የዋና ቡድን» ያለዉን ስብበባ ከ2009 ጀምሮ ዋሽግተን (ሁለቴ)፤ ሞስኮ፤ ቤጂንግ፤ ዶሐ፤ ኒዉ ደልሒ፤ ቪየና እና ቴሕራን ዉስጥ አዘጋጅቷል።በዚሕ ሁሉ ጊዜ አፍሪቃ ከሶማሊያ እስከ ናጄሪያ፤ ከኮንጎ እስከ ማሊ፤ከአይቮሪኮስት እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሊቢያ በፖለቲካዊ ቀዉስ፤ በሽብር፤ ጦርነት ስትመሰቃቀል ነበር።አፍሪቃ የዋና ጉባኤተኞች ትኩረት ለመሳብ ግን ምናልባት እንደ ኳሱ ሌላዉ ዓለም ስለየፀጥታዉ መክሮ-ዘክሮ እስኪሰለቸዉ መጠበቅ ነበረባት እንበል ይሆን?

አዲስ አበባ ላይ ባለፈዉ ሐሙስና አርብ የመከረዉ የሙኒክ ጉባኤ «የዋና ቡድን» ስብሰባ አሸባሪነትን በጋራ ከመከላከል ቀጥሎ ልዩ ትኩረት የሰጠዉ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር እንዳሉት ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ነዉ።«ሁለተኛዉ ያዉ ከመጀመሪያዉ ጋር የተገናኘ ነዉ።የስደተኞች ጉዳይ።ምንም እንኳን ባሁኑ ወቅት አዉሮጳ ዉስጥ ትልቅ ርዕስ የሆነዉ የሶሪያዉንና የአፍቃኒስታኑን ቀዉስና ጦርነት የሚሸሹ ስደተኞች ጉዳይ ቢሆንም አፍሪቃ ያሉ ቀዉሶችና ግጭቶች እስካሁን ካሰደዱት በላይ ሕዝብ ሊያሰድዱ እንደሚችሉ መረዳት ይኖርብናል።የአፍሪቃን ሕዝብ ቁጥር መጨመርን ከግምት ካስገባን፤ የምጣኔ ሐብቱን ሁኔታ ካጤንን ከአፍሪቃ የሚሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር በጅግ ማሻቀቡ አይቀርም።»

ይሕ እዉነት ምናልባት የአዲስ አበባዉ ጉባኤ ለምን አሁን? ለሚለዉ ተደጋጋሚ ጥያቄ መልስ ይሰጥ ይሆናል።የአፍሪቃ ቀዉስ አምና ወይም ዘንድሮ አልተጀመረም።የአሸባሪዎች ጥቃት፤ ጥፋት ወይም ሥጋትም አዲስ አይደለም።ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ወይም ለመግባት የሚሞክሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ቁጥር ያየለዉ ግን በቅርቡ በጣሙን ሊቢያ ከፈረሰች በኋላ ነዉ።አዉሮጶች ስደተኛ እንዳይገባባቸዉ ገሚሶቹ ድንበራቸዉን ማጠራቸዉ፤ የተቀሩት የባሕር በራቸዉን ማስጠበቃቸዉ ዘላቂ መፍትሔ አልሆነም።የሶሪያ ስደተኞችን ከግሪክ ወደ ቱርክ ማጋዙም የስደተኞችን የመሰደጃ አቅጣጫ ከማስቀየር ባለፍ አስተማማኝ እርምጃ አይደለም።

በተለይ የአፍሪቃ ስደተኞችን ለመገደብ አይጠቅመም ።አብነቱ ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር በመተባበር ስደተኛዉ ከየሐገሩ እንዳይወጣ፤ ከወጣም እንዲመለስ የሚገደድበትን ሥልት መቀየስ ነዉ።ጉባኤዉ በዚሕ ረገድ ከተመዘነ ለምን አሁን የሚለዉ ጥያቄ መልስ ያገኛል።በአዲስ አበባዉ ጉባኤ ማግሥት ባሕር ዳርዳር ላይ የተደረገዉ ተመሳሳይ ጉባኤም የአፍሪቃን ፀጥታ በተመለከተ ተመሳሰይ ዉይይት ተደርጎበታል።

ጉባኤዉ የአፍሪቃዉያን ከመሆኑ ጋር የሶማሊያ፤ የሱዳን፤የጅቡቲና የኢትዮጵያ መሪዎች የበርካታ የአፍሪቃ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችና ባለሥልጣናት በመገኘታቸዉ ለአፍሪቃ ፀጥታ ላቅ ያለ ግምት ተስጥቶታል።ይሁንና መሪዎቹ ወይም ባለሥልጣናቱ በየዓመቱ በዚሕ ወቅት የጣንን ባሕር ትንፋሽ ከባሕር ዳር ሙቀት ጋር ሲያጣጥሙ በየሚወክሉት ሐገር ሕዝብ ላይ የሚጣለዉ አደጋ፤ ሽብርና ግድያ ማየሉ ነዉ እንቆቅልሹ።ዘንድሮም የተለየ አይደለም።

የጣና ጉባኤ የቦርድ ሊቀመንበር የናጄሪያዉ የቀድሞዉ ጄኔራል እና ፕሬዝደንት ኦሌሼጎን ኦባሳንጆ የሚመሩት ጉባኤ ባለፉት አምስት ዓመታት ለአፍሪቃ ሠላምና ፀጥታ ያበረከተዉን አስተዋፅኦ ባሕርዳር ላይ ሲዘረዝሩ ሐገራቸዉ በቦኮ ሐራም ሥጋት እንደተናጠች ነበር።ኦባሳጆ የሚያምኑትን ግን አልሸሸጉም።«እንደማምነዉ፤ ጉዳዩን በየትኛዉም መንገድ ብትመለከቱት ባለፉት ሁለት ቀናት ከተደረገዉ ጉባኤ የተረዳነዉ አፍሪቃ መሪዎችዋና ሕዝቧ የሚፈልጉትን ነዉ የምትሆነዉ።አፍሪቃ የማትሆነዉ መሪዎችዋና ሕዝቧ እንዲሆን ያላደረጉትን ነዉ።»

አብዛኞቹ የአፍሪቃ መሪዎች የሚያደርጉት ከአብዛኛ ሕዝባቸዉ ፍላጎት ጋር መጣጠም-መጣረሱን ከየሐገሩ የዕለት ከዕለት ፖለቲካዊ እዉነት መረዳቱ አይገድም።ኦባሳንጆ ያሉት፤ ናጄሪያዉያን ልጃገረድ ተማሪዎች በአሸባሪዎች የታገቱበትን ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር አደባባይ የወጣዉ ናጄሪያዊ ካሰማዉ ጥያቄና ቁጣ ጋር መቃረኑ ግን ሐቅ ነዉ።

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት አፍሪቃ ሠላምና ፀጥታዋን እንድታስከብር የሌሎች ትብብር አስፈላጊ ነዉ።አፍሪቃም ለሌሎቹ እንዲሁ።«ከኔጋር ትስማማላቸሁ።በክፍለ ዓለሚቱ የሠላምና የፅጥታ ሥጋት ሲያጋጥም እንደ መጀመሪያዎቹ ምላሽ ሰጪዎች ጠንካራ እርምጃ መዉሰድ የሚገባን እኛ ብንሆንም አፍሪቃ የሌላዉን ዓለም ድጋፍ ትፈልጋለች።ሌላዉ ዓለም አፍሪቃን እንደሚፈልገዉ ሁሉ።»

ብዙዎች የሚስማሙበት እዉነት ነዉ።ዓለም የጋራ ጠላት የሚለዉን በጋራ ለመከላከል በጋራ መቆም አለበት።ግን የጋምቤላን ሕዝብ ከእልቂት ለማዳን፤ የኦሮሚያን ሠላም ለማስከበር ዓለም አቀፍ ሠላም አስከባሪ ጦር ማስፈር ያስፈልግ ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic