የአፍሪቃ የውስጥ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 17.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ የውስጥ ንግድ

የአፍሪቃ ሃገራት በመካከላቸው የረባ ንግድ ለማካሄድ አለመቻላቸው አንዱ ትልቁ የልማት ችግር ነው።

መሰናክሎቹ ብዙዎች ናቸው። በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ተቋም ዩንክታድ ውስጣዊው ንግድ እንዲስፋፋ አዲስ ባቀረበው ዘገባው አሳስቧል። እርግጥ የአካባቢ የንግድ ማሕበራት መሰናክሎቹን ለማስወገድ ለዓመታት ሲሞክሩ መቆየታቸው አልቀረም። የረባ ውጤት አይታይ እንጂ!

ችግሩን በአንድ ምሳሌ ለመግለጽ ዶቼ ቬለ በስልክ ባነጋገረው የናይጄሪያ ገበሬ በኤማኑዌል ኤድራ ሁኔታ ላይ እናተኩር። ገበሬው ለም በሆነው በናይጄሪያ ማዕከላዊ አካባቢ በጆስ ድንች ሲያመርት ከሰላሣ ዓመታት በላይ ሆኖታል። እርሱ እንደሚለው አካባቢው በምዕራባዊው አፍሪቃ ታላቁ የድንች ምርት ቦታ እንደመሆኑ መጠን ገበያው ጥሩ ነው። ብዙ ገዢዎችም ከየቦታው ይጎርፋሉ።

ሆኖም ችግሩ ከአገር ሻገር ሲል ነው የታየው። ናይጄሪያዊው ገበሬ ከአንድ ዓመት በፊት በጎረቤቲቱ ቤኒን ድንች በጣም ተፈላጊ መሆኑን ይሰማል። እናም የጭነት መኪና ተከራይቶ ድንቹን በመጫን 1 ሺህ ኪሎሜትር ርቃ ወደምትገኘው የቤኒን ዋና ከተማ ወደ ኮቶኑ ያመራል። ታዲያ ገና የናይጄሪያን ግዛት ጨርሶ ሳያልፍ ነበር የነገሩን ከባድነት መመልከት የቻለው። በየቦታው በፖሊስና በወታደሮች እንዲቆም በመደረግ ጊዜ ሲያባክን ጉቦም መክፈል ግድ ይሆንበታል። በርሱው አነጋገር ድንበሩ ላይ ሲደርስ ደግሞ ችግሩ እንዲያውም የባሰ ነበር።

«በየቦታው ጉቦ መክፈል እገደዳለሁ። እናም ይህን መሰሉን ንግድ ከእንግዲህ እንደገና አልሞክረውም። ከናይጄሪያ የተነሣነው 129 ቁምጣ ድንች ጭነን ነበር። ግን ገና ከመድረሳቸን በፊት አብዛኛው ድንች ይበላሻል»

እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች የክፍለ-ዓለሚቱን ንግድ መስፋፋት አግደው እንደሚይዙ ግልጽ ነው። ይህንንም የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ተቋም ዩንክታድ በአዲስ ዘገባው አረጋግጧል። ቀደም ባለው ጊዜ ሁኔታ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን ለመጠቃቀስ በጎርጎሮሳውያኑ 1997 ከጠቅላላው የአፍሪቃ ንግድ አንድ-አምሥተኛው ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት የክፍለ-ዓለሚቱ ሃገራት መካከል የሚካሄድ ነበር። ዛሬ ይህ በ 11 ከመቶ የተወሰነ ሆኖ ነው የሚገኘው። በግማሽ ዝቅ ብሏል ማለት ነው። ይህ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ተቋም የአፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ ታፈረ ተሥፋቸው እንደሚሉት ትልቅ ችግር መሆኑ አልቀረም።

«የአፍሪቃ ችግር የንግዱ መዋቅር በሰሜኑና ባደጉት ሃገራት ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው። በዚህ ላይ የአፍሪቃ ምጣኔ-ሐብት በጥሬ ሃብት የውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ መሆኑ ይታወቃል። ዋጋው በሰሜናዊው ሃገራት በሚቀየርበት ጊዜ እንግዲህ በአፍሪቃ ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ ነው ያለው። የእሢያ ሃገራት ለምሳሌ ብዙ እርስበርሳቸው ይነግዳሉ። እናም በዚህ የተነሣ የኤውሮን ቀውስ በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም ችለዋል»

በዕውነትም የእሢያ ሃገራት ግማሹን ምርታቸውን የሚሻሻጡት በመካከላቸው ነው። አውሮፓ ውስጥ እንዲያውም የአህጉሩ ውስጣዊ ንግድ መጠን ከ 70 በመቶ ይበልጣል። እርግጥ ችግሩ በርከት ባሉት የአፍሪቃ መንግሥታትም ሆነ በክፍለ-ዓለሚቱ ጥላ ድርጅት በአፍሪቃ ሕብረት ዘንድ የማይታወቅ አይደለም። በአካባቢ ማሕበራት አማካይነት፤ እንበል በምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ኤኮዋስ ወይም በምሥራቃዊው አፍሪቃ ማሕበረሰብ EAC እና መሰል ድርጅቶች የንግድ መሰናክሎችን ለማስወገድና በመካከላቸው የሚደረግ ንግድን ለማስፋፋት ለዓመታት ሲጥሩ ቆይተዋል።

ግን የአካባቢው ማሕበራት እንዲያውም ችግር ሆነው መገኘታቸው ነው ሃቁ! ብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ለምሳሌ በአንዴ የብዙ ድርጅቶች ዓባላት ሆነው ይገኛሉ። በብሪታኒያው ከፍተኛ የትምሕርት ተቋም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ-ሐብት ተመራማሪ የሆኑት ፖል ኮሊየርና መሰሎቻቸው ይህን በስፓጌቲ፤ ማለት በፓስታ ትብትብ ይመስሉታል።

Afrika Farmarbeiter auf einer Tabakplantage Tabakernte

«በአፍሪቃ ክፍል-ዓለም ያለው መሪር ሃቅ እንዲህ ይመስላል። በውስጣዊ የንግድ መሰናኮሎች የተተበተቡ 54 ሃገራትን እናገኛለን። ሁኔታው አንዱ አገር ከጎረቤት የሚደረግ ንግድን የሚያደናቅፍበት ነው»

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ተቋም ዩንክታድ በዚሁ የተነሣም የአፍሪቃ መንግሥታት የንግድ መሰናክልን በማስወገድ ላይ ብቻ ሣይሆን በተመሳሳይ ጊዜ የኢንዱስትሪ ፖሊሲያቸውንና መዋቅራዊ ግንባታቸውን እንዲያራምዱም ነው በዘገባው ያስገነዘበው። ተቋሙ አያይዞ እንዳመለከተው በአፍሪቃ ዘላቂ ልማትን ማየት የሚቻለው ይህ ሲሆን ብቻ ነው። ዛሬ የአፍሪቃ የእርሻ ዘርፍ ሌላው ቀርቶ የራሱን ሕዝብ ፍላጎት ለመሸፈን እንኳ ብቁ አይደለም።

ስለዚህም 37 የአፍሪቃ ሃገራት ለውጭ ከሚሸጡት በላይ ምግብ ወደ አገር ያስገባሉ። ከነዚህ መካከል ደግሞ ምሳሌ አድርገን የተነሣንባት ናይጄሪያም አንዷ ናት። ገበሬው ኤማኑዌል ኤርዳም ያሳዝናል የድንች ምርቱን በትውልድ ስፍራው በጆስ ተወስኖ መሸጡን ይቀጥላል። የሚያስገርመው ይህ የሚሆነው በሌጎስና በአቡጃ የሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች ለማቀዝቀዣ የተዘጋጀ የጥብስ ድንች፤ ፍሬንች-ፍራይስ ከአውሮፓ በሚያስገቡበት ጊዜ ነው።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ውስጣዊው ንግድ እንዲያብብ የነጻ ንግድ ፖሊሲን ማስፈኑና ገቢር ማድረጉ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው። በዛሬው ጊዜ በአፍሪቃውያን ጎረቤት ሃገራት መካከል ከሚደረግ ንግድ ይልቅ በአፍሪቃና በአውሮፓ ሃገራት መካከል የሚካሄደው አንዳንዴ ቀሎ ነው የሚገኘው። አፍሪቃ ነጻ ንግድን ማስፋፋቷ፣ መሰናክሎችን ማስወገድ መቻሏና ከጥሬ ሃብት ንግድ ወደ አምራችነት በመሸጋገር ውስጣዊው ገበያ እንዲደራ ማድረጓ ለኤኮኖሚ ዕድገቷና ለማሕበራዊ ልማቷ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህ መሠረታዊ ሁኔታ ሳይፈጠር ዛሬ ስለ አፍሪቃ ሕብረት የፖለቲካ አንድነትም ሀነ የፊናንስ ትስስር ማለም ከንቱ ተሥፋ ሊሆን የሚችል ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic