የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ጉባኤ እና ሩዋንዳ | አፍሪቃ | DW | 12.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ጉባኤ እና ሩዋንዳ

በአፍሪቃ ምጣኔ ሃብት ላይ የሚነጋገረው የአለም የምጣኔ ሃብት መድረክ ኪጋሊ ሩዋንዳ ውስጥ በመካሄድ ላይ ነው ። ትናንት በተጀመረው በዚህ ጉባኤ ላይ ዘጠኝ የመንግሥታት መሪዎችን ጨምሮ ከ70 ሃገራት የመጡ 1200 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል ። እስከ ነገ የሚቀጥለው የዚህ ጉባኤ ትኩረት የአፍሪቃ ምጣኔ ሃብት የወደፊት እጣ ፈንታ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:53 ደቂቃ

የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ጉባኤ ጉባኤ

ሩዋንዳዊው ኬቪን ካባትሲ የ22 አመት ወጣት ነው ።በአነስተኛ እና በመካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚወርት የግል ድርጅት ባለቤት ነው ።የንግድ ድርጅቶቹ በቡና ምርት በስኳር ንግድ ወይም በቴክኖኖሎጂ መስክ የተሰማሩ ናቸው ። የድርጅቱ አጠቃላይ መዋዕለ ንዋይ ከ15 ሺህ እስከ 5o ሺህ ዶላር ይደርሳል ።ካባቲሲ ያደገው ደቡብ አፍሪቃ ነው ። ቤተሰቡ በሳምንታት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከተገደለበት የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሸሽቶ ደቡብ አፍሪቃ በመሰደዱ ነው እዚያ ያደገው ።ካባትሲ እንደሚለው የርስ በርስ ጦርነቱ ሃገሪቱን ባዶ እጅ ነበር ያስቀረው ።ሰላም ከወረደ በኋላ ርስ በርስ መተማመኑ ሳይቀር ፣ሁሉም እንደገና መገንባት ነበረበት ፤ ይላል ካባትሲ ። ሩዋንዳ አሁን ከአፍሪቃ ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉት የአፍሪቃ አገራት አንዷ ናት ። ካባትሲ በሃገሪቱ ለምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታ ይሰፍናል ብሎ ባያልምም ተስፋ ማድረጉ ግን አልቀረም ። በዚህ ምክንያትም የዛሬ ሁለት አመት ወደ ሃገሩ ተመለሰ። የ1ሺህ ኮረብታዎች መገኛ የሆነችው ሩዋንዳ ለርሱ አንድ ሺህ እድሎች ያሉባት ሃገር ሆናለች ።የአለም ባንክ እንደሚለው የሩዋንዳ ኤኮኖሚ እድገት ወደ 7 በመቶ ይጠጋል ። ይህ ደግሞ ከአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገሮች የምጣኔ ሃብት እድገትጋር ሲነፃጸር ከፍተኛ ነው ።የጄኔቫው የአለም የኤኮኖሚ መድረክም የሩዋንዳ ኤኮኖሚ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ እና ከአፍሪቃ

ኤኮኖሚዎችም እጅግ ተፎካካሪውብሎታል ። ዘንድሮ በአፍሪቃ ምጣኔ ሃብት ላይ የሚነጋገረው የአለም የኤኮኖሚ ጉባኤ ኪጋሊ የተካሄደውም በዚሁ ምክንያት ነው ። ሩዋንዳ ለሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ምሳሌ ልትሆን የምትችል ሃገር መሆኗ ይነገራል ። IHS የተባለው የጥናት ቡድን የአፍሪቃ ጉዳዮች ክፍል ሃላፊ ነፃነት ተስፋዮ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሩዋንዳን ለዚህ ያበቃት የምትከተለው የአሠራር ስልት መሆኑን ገልጸዋል ።
«ሩዋንዳ በጣም ግልፅ እቅድ እና አካሄድ አላት ። መንግሥትም አደርጋለሁ የሚለውን በሥራ ላይ ለማዋል እየጣረ ነው ። ስለዚህ ለአንድ የውጭ ባለወረት ግልፅ አሰራር መኖሩ እና እነርሱም ሊከተሉት የሚችሉ የቀደመ ሥራ ማየት መቻላቸው በጣም አበረታች ነው ። መንግሥት ራሱን እንደ አገልግሎት ሰጭ ነው የሚያቀርበው ።በፋይንናንስ በህክምና እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በኮምኒኬሽን ዘርፎች ሌሎች ሃገራት የተለየ ስልት ነው የሚከተሉት ። ሩዋንዳ ደግሞ የሚያዋጣትን አመዛዝና ይህን መሠረት በማድረግ የራስዋን ስልት ፈጥራለች ።ይህንንም ደረጃ በደረጃ እያካሄደች ነው ። »
የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ጉባኤ ኪጋሊ መካሄዱ ለሩዋንዳ ብዙ ጥቅሞች አሉት ይላል የዛሬ 4 አመት ከቦትስዋና ወደ ሃገሩ ሩዋንዳ ተመልሶ የንግድ ድርጅት ያቋቋመው ኤፍሬም ርዋምዌንገ

«ይህ ጉባኤ ኪጋሊ ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው እኔ ሩዋንዳዊ ነኝ ኪጋሊ ውስጥ ልምዱን ተካፍያለሁ ። እንደ ሃገር እና እንደ ህዝብ ከዚህ ቀደም ልናገኛቸው ልናነጋግራቸው ከማንችል ሰዎች ጋር እየተገናኘነን ነው ። የቱርዝም እንቅስቃሴውን ብንመለከት ሆቴሎች በሙሉ ተይዘዋል ።አሁን ክፍል ማግኘት ያስቸግራል ።ጉዞውን ስንመለከት ደግሞ ብዙዎች በኛ አውሮፕላን ነው ኪጋሊ የመጡት ይህ ሁሉ ኤኮኖሚውን እያሳደገው ነው ።»
የሩዋንዳ የሠራተኛና ቅጥር ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚለው በሃገሪቱ ስራ አጥነትን ለመቋቋም በየአመቱ 200 ሺህ አዳዲስ ክፍት የስራ ቦታዎች ያስፈልጋሉ ። በአለም ባንክ ትንበያ መሠረት በሩዋንዳ በርካታ ወጣቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ ፈላጊ መሆናቸው የሃገሪቱ አንዱ ትልቅ ፈተና መሆኑ አይቀርም ።በዚህ የተነሳም የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት የፖል ካጋሜ መንግሥት ትኩረቱን ብዙ የስራ እድል ሊፈጥር ወደሚችለው ወደ ግሉ ዘርፍ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስልም ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic