የአፍሪቃ የመገማገሚያ ሥልት | አፍሪቃ | DW | 31.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ የመገማገሚያ ሥልት

ዓላማዉ ቀላል እና ግልፅ ነዉ።የአፍሪቃ መንግሥታት አንዳቸዉ የሌላቸዉን አመራር፤ ዕቅድና አፈፃፀመን መገምገም፤ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ልምድ መቅሰም።ገቢራዊነቱ እንጂ ግራ-አጋቢዉ።እርግጥ ነዉ ሥልቱ ረቀቅ ያለ የመገምገሚያ ነጥቦች አሉት።መንግሥታት አባል የሚሆኑትም፤ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት አመራራቸዉን ለግምገማ ዘገባ የሚያቀርቡትም በፈቃዳቸዉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:52
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:52 ደቂቃ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ መንግሥታት አንዳቸዉ የሌላቸዉን የፖለቲካና የልማት አስተዳደር ሥልትና አፈፃፀምን ለመገምገም የነደፉትን ዕቅድ ገቢር ለማድረግ አዲስ ሙከራ ተጀምሯል።African Peer-Review-Mechanism የተሰኘዉ የመገማገሚያ ሥልት የተነደፈዉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2003 ነበር።በመንግስታት ፈቃደኝነት ገቢር የሚሆነዉን ሥልት 35 መንግሥታት ተቀብለዉ ቢያፀድቁትም እስካሁን ገቢራዊ አልሆነም።በቅርቡ ግን፤ ፊሊፕ ሳንድነር እንደዘገበዉ፤ ሥልቱን ለሚያስተባብረዉ መስሪያ ቤት አዳዲስ ሐላፊዎች ከተመደቡለት በኋላ ዳግም እንዲያንሠራራ ሙከራዎች እየተደረጉ ነዉ።

የደቡብ አፍሪቃዉ የቀድሞ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ እና የያኔ አፍሪቃዉያን አቻዎቻቸዉ «ለአፍሪቃ ልማት አዲስ ወዳጅነት (NEPAD)» የሚል ሐሳባቸዉን ሲያቀነቅኑ፤ ሐሳባቸዉን ገቢር ለማድረግ ከነደፉት አያሌ ስልቶች አንዱ ነበር።African Peer-Review-Mechanisim (APRM)፤ የአፍሪቃ የመገማገሚያ ሥልት ቢባል ያስኬድ ይሆናል።

ዓላማዉ ቀላል እና ግልፅ ነዉ።የአፍሪቃ መንግሥታት አንዳቸዉ የሌላቸዉን አመራር፤ ዕቅድና አፈፃፀመን መገምገም፤ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ልምድ መቅሰም።ገቢራዊነቱ እንጂ ግራ-አጋቢዉ።እርግጥ ነዉ ሥልቱ ረቀቅ ያለ የመገምገሚያ ነጥቦች አሉት።መንግሥታት አባል የሚሆኑትም፤ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት አመራራቸዉን ለግምገማ ዘገባ የሚያቀርቡትም በፈቃዳቸዉ ነዉ።

Kolonialismus Afrika Karte Aufteilung Kolonialmächte

GIGA በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ሮቤርት ካፔልም «ሐሳቡ ድንቅ ነበር» ባይ ናቸዉ።ማን ገቢር ያድርገዉ እንጂ።

«መልካም አስተዳደርን ለመመሥረት እና የምጣኔ ሐብቱን መርሕ አስተማማኝ ለማድረግ ከተነደፉት ሥልቶች አንዱ ነዉ።የተለያዩ መስኮችን ለማካተት ያለመ ነበር።ሐገራት (ከየግምገማዉ በኋላ) የሚሰጧቸዉን አስተያየቶች ሥራ ላይ ማዋል አለባቸዉ።ግን ገቢራዊነቱ በጣም አዝጋሚ ነዉ።»

እንደታሰበዉ መንግሥታት የምጣኔ ሐብት መርሐቸዉ፤ አስተዳደራቸዉ፤ የፍርድ ቤቶች አሰራሮቻቸዉን፤ ግጭቶችን የፈቱባቸዉ መንገዶች ወዘተ ከነ አፈፃፀማቸዉ ለፅሕፈት ቤቱ ዘገባ ያቀርባሉ።ፅሕፈት ቤቱ ዘገባዉን ለሚገግመዉ ኮሚቴ ያቀርባል።የመሪዎች ጉባኤ የግምገማዉን ዉጤት ያፀድቃል።ተገምጋሚዉ መንግሥት የሚሰጠዉን አስተያየት ይቀበላል።

እስካሁን ከሰላሳ-አምስቱ አባል መንግሥታት ሥራ-አሠራራቸዉ እንዲገመገም ዘገባ ለማቅረብ የፈቀዱት 17 ናቸዉ።የተገመገሙት፤ ሁለት ብቻ።ጅቡቲ እና ቻድ። ሴኔጋል ለሰወስተኝነት ወረፋ ይዛለች።ከሐሳቡ አፍላቂዎች አንዱ ታቦ ምቤኪ ራሳቸዉ «ተነሳሽነቱ የለም» አሉ ባለፈዉ ታሕሳስ።የኬንያዉ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የገምጋሚ ኮሚቴዉን የሊቀመንበርነት ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ግን አፍሪቃዉይን እርስ በርስ ይገማገሙ የሚለዉ «የሞተ» ሐሳብ እንደገና ነብስ የዘራ-መስሏል።

ለAPRM ፅሕፈት ቤት ሐላፊ ሆነዉ አዲስ የተሾሙት ኤዲይ ማሎካ ደግሞ አዋራ የጠገቡ ዶሴዎቻቸዉን ማራገፍ

ይዘዋል።ሥራዉን ለመቀጠል «ማን ምን ማድረግ እንዳለበት መበየን አለበት» ይላሉ-ማሎካ።«በብዛሐ ድርጅት ዉስጥ ያሉ የተለያዩ አካላት ምግባር በግልፅ መበየን አለበት።አባላት አሉ።ኮሚቴዉ አለ፤ ፅሕፈት ቤቱ አለ።ማን ምን ማድረግ እንዳለበት በግልፅ መታወቅ አለበት።ይሕ ሒደት ገና አልተጠናቀቀም።አሁን ሒደቱን ቀጥለናል።ከፍፃሜ እናደርሰዋለን።»

ሥራዉ ከቀጠለ የአፍሪቃ መንግሥታት መልካም አስተዳደርን ለማስረፅ፤ምጣኔ ሐብታቸዉን ለማሳደግ፤ በጥቅል ዉጤቱም የሕዝባቸዉን ኑሮ ለማሻሻል የሚረዱ ሐሳቦችና ልምዶችን ለመለዋወጥ ጥሩ መድረክ ይሆንላቸዋል።እርስ በርስ የሚደረገዉ ግምገማና የሚሰጠዉ አስተያት ለታለመለት ዉጤት የሚበቃዉ ግን ማሎካ እንደሚሉት መንግሥታት ፈቃደኛ ሲሆኑ ብቻ ነዉ። የፖለቲካ ተንታኝ ካፔልም በዚሕ ይስማማሉ።

«ሥድስት-እስከ ስምንት ያሉ መንግሥታት ከተሳተፉ በጣም ጥሩ ነዉ።ሌሎች ሳይሳተፉ ቀርተዉ፤ ተሳታፊዎቹ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ እየተማሩ መልካም አስተዳደርን ማስረፅ፤ ማሕበራዊ ኑሮን ለማሻሻል፤ ሙስናን መዋጋት ከቻሉ (ለሌቹም) ምሳሌ ይሆናሉ።»

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic