የአፍሪቃ የሂሳብ ከፍተኛ ተቋም፤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 14.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአፍሪቃ የሂሳብ ከፍተኛ ተቋም፤

አዲሱን አይንሽታይን ወደፊት በአፍሪቃ ማፍራት ይቻል ይሆን!? በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገሮች ፤ አሁን ከሚገኙበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቁት፣ በትምህርት መስፋፋት ፤ በተለይም በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ሰፊ እገዛ መሆኑ የሚታበል አይደለም።

default

በአፍሪቃ የመጀመሪያው የሂሳብና የፊዚክስ ከፍተኛ ተቋም የሚገኝባት፣ኬፕታውን

በማደግ ላይ ይገኛሉ ከሚባሉት ክፍላተ-ዓለምና ሃገራት መካከል፤ አብዛኞች የአፍሪቃ አህጉር (አገሮች) መሆናቸው እሙን ነው። ታዲያ ሌሎች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ፤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች፤ በተለይም በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ ማትኮሩ ግድ እንደሚል አፍሪቃውያን ውለው አድረው በሚገባ የተገነዘቡት ዐቢይ ጉዳይ ሳይሆን አልቀረም። በመሆኑም ፤ በአፍሪቃ፣ ተሰጥዖ ያላቸውን ምርጥ ወጣቶች ማሠልጠን የሚቻልባቸው በአጠቃላይ 20 የትምህርት ተቋማት የታቀዱ ሲሆን ፤ የመጀመሪያው፣ የአፍሪቃ የሂሳብ ተቋም (African Institute of Mathematics(AIMS) ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል በኬፕታውን ፤ ደቡብ አፍሪቃ ከተቋቋመ፤ 8 ዓመት ሆኖታል። በዚያ እየተማሩ የሚወጡት ወደፊት የክፍለ-ዓለሙን ዕድገት ያንቀሳቅሳሉ ተብሎ ነው ብሩኅ ተስፋ የተጣለባቸው።እስታስቲስቲክ፤ አልጀብራ፤ የኮምፒዩተር ስሌት፤ ---ማንኛውም በኬፕታውኑ የማቴማቲክስ ሳይንስ ተቋም መማር የሚፈልግ ሂሳብን የሚወድ መሆን አለበት። በዚያ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሳተፍ የሚችሉት፤ እጅግ ጎበዝ መሆናቸው ወይም ትልቅ ተሰጥዖ እንዳላቸው የተረጋገጠላቸው ናቸው። ከምርጥ አፍሪቃውያኑ ተማሪዎች መካከል፣ ዩጋንዳዊው ማይክል ካቴሬጋ ይገኝበታል። አሁን በዚያ የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቋል። ማይክል ካቴሬጋ---

1,« የ AIMS መርኀ ግብር አንድ ዓመት የሚወስድ ነው። በጣሙን የተደራረበና ተያይዞ በጥቅሉ የሚቀርብ ትምህርት ነው የሚሰጠው። ብዙ ነው መማር ያለብን። በዚህም ሳቢያ ያልተቋረጠ የትምህርት ጫና ያስጨንቅሃል»።

እንደ ማይክል ፤ ከመላዋ አፍሪቃ 50 ተማሪዎች፣ ከዚሁ ከፈተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀው ወጥተዋል። የትምህርቱን ወጪ፤ ለምግብና ለማደሪያ ሁሉንም የሚችለው ተቋሙ ነው። ትምህርቱ የሚሰጠውም ሆነ ተማሪዎቹና መምህራኑ የሚግባቡት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው።

ፕሮፌሰሮቹ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ፤ በሙያቸው የተካኑ ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፤ የዚሁ AIMS ተቋም የሥራ መሪ ፕሮፌሰር Barry Green!ደቡብ አፍሪቃዊው ፕሮፌሰር፣ ቤሪ ግሪን፤ ጀርመን ውስጥ በሃይድልበርግ ዩኒቨርስቲ 10 ዓመታት ምርምር ያካሄዱ ናቸው። ወደ ኬፕታውን የተመለሱት እ ጎ አ በ 1990ኛዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። ቤሪ ግሪን እንደሚሉት፤ ለእመርታና ዕድገት ቁልፉ ሂሳብ ነው።

2,«ለሳይንሳዊ ተግባር መሠረቱ ሂሳብ ነው። የትም ቦታ ቢሆን ያው ነው፤ አውሮፓ፤ አፍሪቃ፤ ፈረንሳይ ወይም ዩናይትድ እስቴትስ ለውጥ የለውም። ለፕሮብሌሞች መፍትኄ የሚሹ፣ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶች ያስፈልጉናል። ብዙዎቹ ፕሮብሌሞች፤ በሂሳብ ቋንቋ የሚገለጡ ናቸው። ሂሳብ ማስተማር ፤ በወጪ ረገድ ሲታይ አመርቂ ነው፤ ውድ ቤተ-ሙከራ አያሻውምና!»

ተማሪዎችን የሚመርጠው ኮሚቴ አባል በመሆናቸውም ቤሪ ግሪን፤ በAIMS ተቋም፣ ማለትም African Institute of Mathematics ውስጥ ማን ትምህርቱን መከታተል ይችላል? ማን አይችልም-የመወሰኑ ሥልጣን አላቸው። ውድድሩ በጣም ከባድ ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ 400 የሂሳብ ተማሪዎች ነበሩ በተጠቀሰው የኬፕታውኑ ተቋም ተመዝግበው ለመማር የተወዳደሩት። ከእነዚያ መካከል፤ 55 ብቻ ነበሩ የተመረጡት። መራጩ ኮሚቴ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው፤ እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ ውጤት የመጀመሪያ ዲግሪአቸውን (ባችለር) ያገኙትን ነው። ይህም በተለይ፤ በሂሳብና በነባቢዬአዊ ፊዚክስ እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡትን ነው የሚመለከተው። ከዚህም በተጨማሪ፤ ምርጥ ተማሪዎች ሰብሳቢው ተቋም፤ ከመላ አፍሪቃ ፤ ከ4ቱም ማዕዘናት ውክልና እንዲኖር በተለይም ደግሞ ሴቶች ተማሪዎች በብዛት እንዲሳተፉ አጥብቆ ይሻል። በአሁኑ ወቅት፤ በኬፕታውኑ ከፍተኛ ተቋም ከሚማሩት የሂሳብ ተሰጥዖ ካላቸው ተማሪዎች መካከል፣ ሲሦው፣ ሴቶች ናቸው።

ትምህርቱ ፤ የአንድ ዓመት ነው። ተማሪዎቹ ያን እንደጨረሱም፤ ለማስተር ዲግሪም ሆነ ለ PhD የሚያበቃቸውን ትምህርት ለመከታተል ማመልከቻዎችን ማስገባት ይችላሉ። ዐቢይ ተሰጥዖ ያላቸውና በሆነ የአፍሪቃ ዩኒቨርስቲ፣ትምህርታችውን መከታተል ለሚሹ ፤ የጀርመን የአካዳሚ የልውውጥ አገልግሎት DAAD (Deutscher Akedemischer Austausch Dienst)ነጻ የትምህርት ዕድል(እስኮላርሺፕ ) ይሰጣል። ከሀገር ሀገር ክፍያው ይለያያል፤ የሆነው ሆኖ፤ በወር ከ 250 እስከ 500 ዩውሮ እንደሚሰጥ ፤ በተጠቀሰው የጀርመን የአካዳሚ ልውውጥ፤ ከሰሃራ ምድረ በዳ በስተደቡብ ላሉ የአፍሪቃ አገሮችና ለላቲን አሜሪካ አገሮች የአመራር ቡድን ዋና ኀላፊ የሆኑት ማርቲና ሹልትዘ እንዲህ ይላሉ።---

3,«ችግሩ፤ በአፍሪቃ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እጅግ ጥቂቶች መሆናቸው ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስተማር የሚችሉ ፣ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው ሰዎች ቁጥር እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑም ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው። እዚህ ላይ ፣ ለእኛ የDAAD ሰዎች፤ የሚቀድመው አንድ ጊዜ በአፍሪቃ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ለሚሹ ሁሉ፣ ፕሮፌሰሮችን የማሠልጠኑ ጥያቄ ነው። »

የጀርመን የአካደሚ ልውውጥ አገልግሎት(DAAD )ባለፉት 3 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ 25 አፍሪቃውያን ረድቷል። ብሩኅ አእምሮ ያለው የ ኬፕታውኑ AIMS ተቋም ተማሪ፤ ዩጋንዳዊው ማይክል ካተሬጋ የሚወደው ይበልጥ በትምህርት መግፋቱን ነው።

4, «የምፈልገው በፋይናንስ ሂሳብ ክፍል ገብቶ መማሩን ነው። ከፍተኛ ህልሜ፤ ምኞቴ፣ ይህ ነው። በሙያ መምህር ነኝ። እናም ፤ ወደ ትውልድ ሀገሬ፣ ዩጋንዳ አንድ ቀን ተመልሼ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም፣ የፋይናንስ ሂሳብ የማስተማር ጽኑ ፍላጎት አለኝ።»

ማይክል ማለፊያ ዕድል አለው። አብዛኞቹ የ AIMS ተማሪዎች አፍሪቃ ውስጥ ለሥራ ይፈለጋሉ።

በዝግጅታችን መግቢያ ላይ እንዳልነው፤ በአፍሪቃ፣ ተሰጥዖ ያላቸውን ምርጥ ወጣቶች ማሠልጠን የሚቻልባቸው በአጠቃላይ 20 የትምህርት ተቋማት የታቀዱ ሲሆን ፤ የመጀመሪያው፣ የአፍሪቃ የሂሳብ ተቋም (African Institute of Mathematics(AIMS) ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል ፣ በኬፕታውን ፤ ደቡብ አፍሪቃ ከተቋቋመ፤ ከ 8 ዓመት ወዲህ፤ ከሰሞኑ፣ በሴኔጋል ከመዲናይቱ ከዳካር፤ በስተደቡብ በሥተምሥራቅ 80 ኪሎሜትር ያህል ራቅ ብላ ባህር ጠረፍ ላይ በምትገኘው እምቡር በተባለችው ከተማ 2ኛው አፍሪቃ አቀፍ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመሥርቷል። ተቋሙ በተከፈተበት ሥነ ሥርዓት ላይየ AIMS ጠንሳሽ ደቡብ አፍሪቃዊው የፊዚክስ ምሁር ኒል ቱሮክ እንዲሁም የጀርመኑ የኖቤል ተሸላሚ የፊዚክስ ሊቅ Klaus von Klitzing ተሳትፈዋል። የሴኔጋሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ዋና ዓላማው በይበልጥ ምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃን ለማገልገል ነው። ይሁንና ከአፍሪቃ በመላ የሚመለመሉ ተማሪዎች ናቸው በውድድር የሚመረጡት። ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋሙ፤ ከ 14 የአፍሪቃ አገሮች የተውጣጡ 35 ተማሪዎችን ተቀብሏል።

የሴኔጋሉ ተቋም ፤ አፍሪቃውያን ፣ በክፍለ-ዓለሙ ላይ ለተጋረጡ ችግሮች ፣ ለምሳሌ ያህል የአየር ንብረት ለውጥ፤ ምግብ በአስተማማኝ ሁኔታ አለመገኘት ፤ ተዛመች በሽታዎችና ለመሳሰሉት መላ እንዲፈልጉ እንዲሁም፤ በራሱ ሳይንስና ቴክኖሎጂንም ለማሳደግ እንዲጥሩ ነው የሚሻው።

በመጀመሪያ ከተቋቋመው ከኬፕታውኑ ተቋም እስካሁን ከ 31 የአፍሪቃ አገሮች፤ 360 ተማሪዎች ተመርቀዋል።

AIMS እ ጎ አ እስከ 2020 ፣ 15 ልዩ ከፍተኛ የሂሳብና ፊዚክስ ተቋማት ለማቋቋም እቅድ አለው።

የሴኔጋሉ AIMS ባልደረባ ፤ ቫንሳ ሪቫሶ፣ እንዳሉት ሁሉም፣ አፍሪቃዊ አይንሽታይን የማፍራት ህልም አለው። ጀርመን ውስጥ በ ዑልም ከተማ የተወለደው ይሁዲው ሥመ ጥር የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አይንሽታይን ፤ እጅግ ብሩኅ አእምሮ እንደነበረው የሚነገርለት፣ የምዓተ ዓመቱ የዘመናዊ ፊዚክስ አባት መሆኑ በአብዛኞቹ የፊዚክስ ሊቃውንት የተመሠከረለት ነው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ