የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር | ስፖርት | DW | 28.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የምድብ ዙር በዚህ ሣምንት አጋማሽ ተጠቃሎ ጨዋታው ወደ ሩብ ፍጻሜው ይሸጋገራል።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የምድብ ዙር በዚህ ሣምንት አጋማሽ ተጠቃሎ ጨዋታው ወደ ሩብ ፍጻሜው ይሸጋገራል። ከአራቱ ማጣሪያ ምድቦች እስካሁን የለየለት የመጀመሪያው ምድብ ብቻ ነው። በዚሁ ምድብ አንድ ውስጥ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃና ለውድድሩ እንግዳ የሆነችው ካፕ-ቬርዴ ወደ ተከታዩ ዙር ሲያልፉ ያስገርማል ጠንካሮች ተብለው የታሰቡት ሞሮኮና አንጎላ ከወዲሁ መሰናበት ተገደዋል።

ካፕ ቬርዴ በመጀመሪያ የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ተሳትፎዋ ከደቡብ አፍሪቃና ከሞሮኮ እኩል ለእኩል ስተለያይ ወደ ሩብ ፍጻሜው እንድትዘልቅ ወሣኙ ትናንት አንጎላን 2-1 መርታቷ ነበር። በምድብ-ሁለት ውስጥ ጋና በአራት ነጥቦች ቀደምቷ ስትሆን ዛሬ ከኒጀር በምታካሂደው ግጥሚያ እኩል ለእኩል ውጤት ይበቃታል። ማሊና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ ዛሬ ማምሻውን እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ጨዋታው ከምድቡ ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፈው ሁለተኛ አገር የሚለይበት ነው።

በምድብ-ሶሥት ከናይጄሪያ 1-1 በመለያየትና ኢትዮጵያን 4-0 በማሸነፍ አመራሩን የያዘችው ቡርኪና ፋሶ ወደፊት የመዝለቅ የተሻለ ዕድል ሲኖራት ነገ ከዛምቢያ ጋር በምታደርገው ግጥሚያ እኩል ለእኩል ውጤት ሊበቃት ይችላል። ከውድድሩ ልትሰናበት የምትችለው ዛምቢያና ናይጄሪያ ካሸነፉ ብቻ ነው። በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመዝለቅ የሚቀረው ምርጫ ናይጄሪያን ማሸነፍ ብቻ ነው። እንዲህም ሆኖ ዛምቢያ በቡርኪና ፋሶ መሸነፍ ወይም በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰን ይኖርባታል።

ምድብ-አራት ውስጥ አይቮሪ ኮስት ቶጎንና ቱኒዚያን በማሸነፍ በስድሥት ነጥቦች ቀደምቷ ስትሆን ወደፊት መዝለቋን የሚጠራጠር ማንም የለም። ቱኒዚያና ቶጎ እያንዳንዳቸው ሶሥት ነጥብ ሲኖራቸው ከነገ በስቲያ እርስበርስ በሚያካሂዱት የመጨረሻ የምድብ ግጥሚያ ማን ወደ ሩብ ፍጻሜው እንደሚያልፍ ይለይለታል። ካላንዳች ነጥብ የቀረችው አልጄሪያ ግን እንደ ሌላዋ የማግሬብ አገር እንደ ሞሮኮ ሁሉ ከወዲሁ አልቆላታል።

ወደ ምድብ-ሶሥት መለስ እንበልና ከ 31 ዓመታት የጥም ጉዞ በኋላ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ምንም እንኳ በቡርኪና ፋሶ ብትሸነፍም ወደፊት የመራመድ ዕድሏን ገና እንደጠበቀች ነው። ብሄራዊው ቡድኑ በአጭር ቅብብል አጨዋወት ስልቱና የቴክኒክ ብቃቱ በተለይ ከዛምቢያ ባደረገው ግጥሚያ ደጋፊዎቹን ብቻ ሣይሆን የውጭ ታዛቢዎችን ጭምር ሲማርክ በራሱ ከተማመነ ነገም እንደገና ለስኬት የማይበቃበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እርግጥ ከቡርኪና ፋሶ የታየው የመሃል ሜዳ ድክመት እንዳይደገም በቂ የታክቲክና የቴክኒክ ዝግጅት መደረጉ ግድ ነው።

ብሄራዊ ቡድኑ አሁን ወሣኝ በሆነ ግጥሚያው ዋዜማ በምን ዓይነት የመንፈስና የዝግጅት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዚህ ዓይነቱ ታላቅ ውድድር እንግዳ እንደመሆኑ መጠን በተለይም ካለፈው አርብ ሽንፈት ወዲህ የመንፈስ ማጠናከር ትልቅ ጥረት ማስፈለጉ አልቀረም። ለመሆኑ እንዴት ነው የትግል ቁርጠኝነት ይታያል ወይ?

ባለፈው አርብ ግጥሚያ አዳነ ግርማ በተሰማው ሕመም መጫወት አቅቶት አቋርጦ መውጣቱ፤ የሽመልስ በቀለ መቀየርም እንዲሁ ቡድኑን እንዳጎደለ የኋላ ኋላ በግልጽ ነበር የታየው። ከዚህ በኋላ ነበር የኢትዮጵያ ቡድን መሃል ሜዳውን መቆጣጠር አቅቶት የታየው። እንዴት ነው ነገ እነዚህ ተጫዋቾች መልሰው ይሰለፋሉ? ተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈጠርስ አማራጭ ዘዴ ተሰልቷል ወይ? በዚያው በደቡብ አፍሪቃ የሚገኘውን የፌደሬሺኑን የግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለን ዛሬ በስልክ አነጋግሬ ነበር፤ ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 28.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Sv6
 • ቀን 28.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Sv6