የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን | ስፖርት | DW | 05.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

29ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ባለፈው ሰንበት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል። 29ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ባለፈው ሰንበት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል። አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ ከመደበኛና ተጨማሪ ጊዜ በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት ጨዋታ

በማሊ 3-1 ተረትታ ስትሰናበት ጋና ደግሞ ካፕ ቬርዴን 2-0 በማሸነፍ ከውድድሩ አስወጥታለች። ለካፕ ቬርዴ የመጀመሪያውን የምድብ ዙር በአስደናቂ ሁኔታ አልፎ ለሩብ ፍጻሜ መብቃቱ ራሱ እንደ አንድ ታላቅ ውጤት ሊቆጠር የሚችል ነው። ጋና በአንጻሩ እስከ ፍጻሜው የመዝለቅ ጥሩ ዕድል ያላት ይመስላል።

በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሮች ሁለቴም ለፍጻሜ ደርሳ በፍጹም ቅጣት ምት ለተሸነፈችው ለአይቮሪ ኮስት ይባስ ብሎ ዘንድሮ ሩብ ፍጻሜው መሰናከያዋ ሆኗል። በርከት ባሉ ዓለምአቀፍ ከዋክብት ያሸበረቀችው አይቮሪ ኮስት እንደተለመደው ዘንድሮም በብዙዎች ታዛቢዎች የላቀው የዋንጫ ባለቤትነት ዕድል የተሰጣት አገር ነበረች። ግን አሁንም ኳስ ድቡልቡል ይህን አልፈቀደችም። አይቮሪ ኮስት ከውድድሩ ቀድማ የተሰናበተችው ካለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ገና በማጣሪያው ተሰናክላ ቀርታ በነበረችው በናይጄሪያ 2-1 በመረታት ነው።

በመጨረሻው ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ቡርኪና ፋሶ አጥቂዋ ጆናታን ፒትሮይፓ ባለቀ ሰዓት በአናቱ ባስቆጠራት ጎል ቶጎን 1-0 በማሸነፍ ከ 15 ዓመታት በኋላ እንደገና ለግማሽ ፍጻሜ ዙር አልፋለች። በፊታችን ረቡዕ በግማሽ ፍጻሜው ውድድር ናይጄሪያ ከማሊ የምትገናኝ ሲሆን ቡርኪና ፋሶ ደግሞ የጋና ተጋጣሚ ናት። በነገራችን ላይ ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ተሳታፊዎች ናይጄሪያና ቡርኪና ፋሶ ከኢትዮጵያ ምድብ መመንጨታቸው ሲታሰብ ምናልባትም ኢትዮጵያ ቀላል ተፎካካሪዎች አልገጠሟትም የሚያሰኝ ነው።

ኢትዮጵያን ካነሣን ብሄራዊው ቡድን ከ 31 ዓመታት ናፍቆትና ጥም በኋላ የተመለሰበትን አህጉራዊ ውድድር በማድመቅ ተልዕኮውን አኩሪ በሆነ ሁኔታ ሲወጣ ወደ አገር ሲመለስ በስታዲዮም የተሰበሰቡ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም የደመቀ አቀባበል በማድረግ ክሰውታል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ምንም እንኳ ከምድቡ ዙር ባያልፍም በተለይ ከዛምቢያ ጋር ለዚያውም በረኛው ተቀጥቶበት በአሥር ሰው ያደረገው ትግልና የአጨዋወት ብቃት ኢትዮጵያ ለፉክክር ብቁ መሆኗን ያስመሰከረ ነው።

ከቡርኪና ፋሶም ሆነ ከናይጄሪያ በተደረጉት ግጥሚያዎች የታዩት ስህተቶች በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉና የራሳቸው ምክንያቶች ያሏቸው ሲሆኑ የቡድኑን ብቃት እምብዛም አጠያያቂ የሚያደርጉ አይሆኑም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትንሣዔ ማድረጉ ገና ከደቡብ አፍሪቃ በፊት በአፍሪቃና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ሲከሰት ከእንግዲህ የሚቀረው ስህተቶቹን አርሞና የሚሟላውን ሁሉ አሟልቶ ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ ነው።

ቡድኑ በቅርቡ ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድርና ለመጪው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ በማጣሪያ ትግሉ የሚቀጥል ሲሆን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተገኘውን ልምድ መሠረት አድርጎ መጠናከሩ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑበት ነው አሠልጣኙም ሆኑ ተጫዋቾቹ አዲስ አበባ ላይ በተደረገላቸው የስታዲዮም አቀባበል ወቅት በአንድ መንፈስ የገለጹት።

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን መጠናከር በሚመኙ የስፖርት ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎችና ታዛቢዎች ሰሞኑን ብዙ ብዙ ተብሏል። መንግሥት ለወጣቱ ትውልድ የስፖርት ተሃንጾ አስፈላጊውን በጀትና ድጋፍ መስጠት፤ አመቺ ሁኔታንም መፍጠር ሲኖርበት ፌደሬሺኑም ከፖለቲካ ተጽዕኖ ውጭ በባለሙያዎች የሚመራ መሆኑ ለስኬት ቁልፍ ነው። ብሄራዊ ቡድኑን ለማጠናከር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን ለመጥቀስ ያህል የወቅቱን ቡድን ከተጨማሪ ክለቦች በሚመነጩ ተጫዋቾች እስከ ሰላሣና አርባ በማስፋት ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ፍጥነት እየተገናኙ ልምምድና ጥናት እንዲወስዱ ማድረግ፣ በብሄራዊ ቡድንና በፕሬሚየር ሊጉ ክለቦች አሠልጣኞች መካከል ቋሚና የጠበቀ ትብብር መኖሩ፤ እንዲሁም የክለብ አሠልጣኞችን ዕውቀት ማዳበር ታላቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ብሄራዊው ቡድን በተሻለ ሁኔታ እንዲዳብር ወደ ውጭ ሃገራት እየሄደ ወይም ወደ አገር ከሚጋበዙ ቡድኖች ጋር በመጋጠም ዓለምአቀፍ ልምድ እንዲቀስም ጥርጊያ መክፈትና ገቢር ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህ በተለይም የመንግሥትን ያልተቆጠበ ድጋፍ ይጠይቃል። የደቡብ አፍሪቃው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ተሳትፎ እንዳሳየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጨዋወት ስልቱን ከማስከን ባሻገር ታክቲክንና የተጋጣሚዎችን ግምገማ በተመለከተ የአሠልጣኝ ቡድኑን ማስፋትም የሚያስፈልገው ነው የሚሆነው።

የዋናው የቡድኑ አሠልጣኝ ተግባር የተሟላ እንዲሆን ዓለምአቀፉን እግር ኳስ በቅርብ በሚከታተልና መረጃ ፊልሞችን በማጠናቀር ተጫዋቾቹን በሚያዘጋጅ ባለሙያ፣ ተጫዋቾችን በሚገባ በአካልና በመንፈስ ለግጥሚያ በሚያሰናዳ አጋዥ መታጀቡ በጣሙን የሚጠቅም ነው። የደቡብ አፍሪቃው ውድድር ሌላም ግልጽ ያደረገው በፍጥነት መሻሻል የሚኖርበት ችግር አለ። ይሄውም በመከላከል ረገድ ቡድኑን ደጋግሞ ለቀይ ካርድ መቀጮ ያጋለጠው የአጨዋወት ዘይቤ ነው።

በረኛም ሆነ ተከላካይ አጥቂ ሲመጣበት የመጨረሻ ምርጫው መጥለፍ እንዳይሆን ይህን የሚሸፍን ተጋጋዥ የቦታ አያያዝ አጨዋወት የጋራ ስልት ሊኖር ይገባል። ሌላው ነጥብ ደግሞ ምናልባት ቁልፍ የሆኑ ተጫዋቾች ቀይ ካርድ ተሰጥቷቸው ወይም ጉዳት ደርሶባቸው ከሜዳ ቢወጡ ቀልጥፎ የአጨዋወት ታክቲክን ከሁኔታ ማጣጣም መቻል ነው። ይህ ክፍተት በተለይ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በተደረገው ግጥሚያ ቁልጭ ብሎ ታይቷል። ተጋጣሚን በውል ማጥናት የሚያስፈልገውና ሁለት-ሶሥት አማራጭ የአጨዋወት ዘዴዎችን ቀድሞ ማስላቱ የሚጠቅመውም እዚህ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ ከእንግዲህ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ መሆን የለበትም። ዛሬ ጊዜው ያፈራቸው ተጫዋቾች በግሩም አርአያነት የብዙ ወጣት ስሜት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል። ማን ያውቃል፤ ምናልባት ከሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ድል ከሃምሣ ዓመታት በኋላ ለዚያውም የእግር ውበት መለያ ሆና በኖረችው በብራዚል ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እንበቃም ይሆናል።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊቱ የለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን ወርቅ አሸናፊ ቲኪ ገላና ትናንት ጃፓን- ማሩጋሜ ላይ የተካሄደው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ባለድል ሆናለች። የኒውዚላንዷ ኪም ስሚዝ ሁለተኛ ስትወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው ጃፓናዊቱ ሣኪኮ ማትሱሚ ናት። ቲኪ ሩጫውን በአንድ ሰዓት ከስምንት ደቂቃ 53 ሤኮንድ ጊዜ ስትፈጽም ይህም ሁለተኛ ድሏ መሆኑ ነው። ቲኪ ገላና በዛሬው ዕለት በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ያለፈው 2012 ዓ-ም አትሌት ተብላ የወርቅ ጫማ ተሸልማለች። ቲኪ ለዚህ AIMS/ASICS ሽልማት ስትመረጥ የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊ መሆኗ ነው። በቦስተን የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ደግሞ ሃጎስ ገ/ሕይወትና ጥሩነሽ ዲባባ በየፊናቸው አሸናፊ በመሆን ስኬታማ ሰንበት አሳልፈዋል።

ሃጎስ ገ/ሕይወት በሶሥት ሺህ ሜትር የለንደን ኦሎምፒክ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነውን አሜሪካዊ ጋለን ሩፕን አስከትሎ ነው ያሸነፈው። አትሌቱ የዓመቱን ፈጣን ሰዓትና አዲስ የወጣቶች ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብም በቅቷል። የ 18 ዓመቱ ወጣት በለንደን ኦሎምፒክ በአምሥት ሺህ ሜትር 11ኛ መውጣቱ የሚታወስ ነው። የለንደን ኦሎምፒክ የአምሥት ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ደጀን ገ/መስቀልም በዚሁ ሩጫ ሶሥተኛ ሆኗል።

በሴቶች የሶሥት ጊዜዋ የኦሎምፒክ ወርቅ ተሸላሚ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በሁለት ማይል ስታሸንፍ ቢሆንም በአሯሯጮች መጓቷት የተነሣ የቆየውን የመሠረት ደፋርን ጊዜ ለማሻሻል ባለመቻሏ ቅሬታዋን ገልጻለች። በፍጥነት ልሮጥ እችል ነበር ነው ያለችው። ሞስኮ ላይ በተካሄደ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ውድድርም መሐመድ አማን በ 600 ሜትር ሩጫ ሲያሸንፍ በጃፓን የቤፑ-ኦኢታ ማራቶን ደግሞ የአገሬው ሯጭ ዩኪ ካዋኡቺ ለድል በቅታለች።

Rehhagel - Scolari

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በዚህ ሣምንት ውስጥ በዓለም ዙሪያ አርባ ገደማ የሚጠጉ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል በታላቅ ጉጉት የሚጠበቁትን ለመጥቀስ ያህል በዓለም ዋንጫው አሸናፊ አሠልጣኝ በሉዊስ-ፌሊፔ-ስኮላሪ መልሶ መመራት የጀመረው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም የእንግሊዝ ተጋጣሚ ነው። ከዚሁ ሌላ በሚደረጉት ከባድ ሚዛን ግጥሚያዎች የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓኝ ከደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮን ኡሩጉዋይ ጋር በካታር የምትገናኝ ሲሆን ፓሪስ ላይ ፈረንሣይ ከጀርመን፤ በአምስተርዳም ደግሞ ኔዘርላንድ ከኢጣሊያ ይጋጠማሉ።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Xqn
 • ቀን 05.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Xqn