የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ | ስፖርት | DW | 08.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ በአልጄሪያ 2 ለ1 ተሸንፏል። በአውሮጳ የእግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ጨዋታ ፖርቹጋል ባልተጠበቀ ሁናቴ በሜዳዋ በአልባኒያ ስትረታ፤ ማኅበሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለችው አዲሲቷ አባል ጂብራልተር በፖላንድ የግብ ጎተራ ሆናለች። ጀርመን ስኮትላንድን ረትታለች።

ርመን ከስኮትላንድ

ርመን ከስኮትላንድ

የፖርቺጊዙ ተወላጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ከትናንት በስትያ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ በመሩት ግጥሚያ ለማሸነፍ አልተሳካላቸውም። አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን በሽንፈት ለመጀመር ተገደዋል። በቅዳሜው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ በነበረው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ነው 2 ለ1 የተረታው።

ለአልጀሪያ በ35ኛው እና 84ኛው ደቂቃዎች ላይ ግቦቹን ያስቆጠሩት ሶውዳኒ እና ብራሂሚ ናቸው። የኢትዮጵያ ቡድንን በባዶ ከመሸነፍ የታደገችው ብቸኛ ግብ የተገኘችው መደበኛው የጨዋታው ክፍለ-ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው 4ኛ ደቂቃ የባከነ ጊዜ ነበር። ግቧን በፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ ያስቆጠረው ሠላዲን ሠዒድ ነው።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የተደለደለችው ማሊ ግብ ጠባቂዋ ማማዶ ሳማሳ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶባትም ቢሆን ማላዊን 2 ለባዶ ረትታለች። የማሊ እና ማላዊ ግጥሚያ መከናወን የነበረበት ቅዳሜ ዕለት ቢሆንም፤ ባማኮ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ጨዋታው ከታቀደለት ጊዜ ከ24 ሠዓታት በኋላ ለመከናወን ግድ ብሏል።

ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ማላዊ እና ማሊ በሚገኙበት ምድብ፤ ማሊ በአንድ የግብ ክፍያ አልጀሪያን በልጣ በተመሳሳይ ሦስት ነጥብ አንደኛ ሆናለች። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ያለምንም ነጥብ በአንድ የግብ ዕዳ ከማላዊ ተሽላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሁለት የግብ ዕዳዎችን ተሸክማ ከምድቡ በመጨረሻ ጠርዝ ላይ የምትገኘው ማላዊን የፊታችን ረቡዕ ለመግጠም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ማላዊ ማቅናቱ ተዘግቧል።

ቶማስ ሙለር

ቶማስ ሙለር

ቤኒንን 4 ለ3 አሸንፋ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምድብን የተቀላቀለችው ማላዊ እና አልጄሪያ ጠንካራ ቡድኖች እንደሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ተናግረዋል። ሞሮኮ ውስጥ የሚካሄደው 30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ ለመሳተፍ ከየምድቡ ሁለት ሃገራት አላፊ ይሆናሉ።

በሣምንቱ ማሳረጊያ፥ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ውስጥ የአውሮጳ የእግር ኳስ ማኅበሮች ኅብረት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።ውጤቶቹን አብረን እንቃኛለን። የጀርመን እና የስኮትላንድ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች ትናንት የተገናኙት ጀርመን ዶርትሙንድ ከተማ ውስጥ ነበር። 60 ሺህ ተመልካቾችን ባስተናገደው ኢዱና ፓርክ ስታዲየም የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ስኮትላንድን 2 ለ1 አሸንፏል። የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ባለቤት የሆነው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በትናንት ጨዋታው ጠንካራ ሆኖ አልተገኘም ሲሉ የጀርመን የመገናኛ አውታሮች ትችት ሰንዝረዋል። ለጀርመን በ18ኛው እና 70ኛው ደቂቃዎች ግቦቹን ላስቆጠረው ግብ አዳኙ ቶማስ ሙለር ዋናው ነገር ማሸነፋቸው ነው።

«እንዴ! ግብ ማስቆጠርማ በእርግጥም ደስ ያሰኛል። ግን ግቡ ለማሸነፍ በቂ ሆኖ ሲገኝ ነው የበለጠ የሚያስደስተው። እናም እግዚአብሔር ይመስገን ያ ተሳክቷል፤ ስለእዚህ ያገኘነው ነጥብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ስለማውቅ በጣም ነው ደስ ያለኝ። እና ደግሞ አሁን ነጥባችንን ማንም ሊቀማን አይችልም »

ስኮትላንድን በዜሮ ከመሸነፍ ያዳነውን ግብ ኢኬቺ አንያ በ66ኛው ደቂቃ ለማስቆጠር ችሏል። የጀርመን እና የስኮትላንድ ጨዋታ መደበኛ ክፍለ-ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ሠዓት የስኮትላንዱ ቻርለስ ሙልግሬው በጭማሪው የባከነ ሠዓት 1ኛው እና 4ኛው ደቂቃዎች ላይ ሁለት ቢጫ በማግኘቱ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ከሜዳ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል። በባከነው ሠዓት 5ኛው ደቂቃ ላይ ዳኛው ለቶማስ ሙለር ቢጫ መርቀው ጨዋታው ተጠናቋል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ሹርለን ተክቶ የገባው ሉቃስ ፖዶልስኪ የትናንቱን ጨዋታ ድክመት እና ጥንካሬ አሠልጣኝ ዮኣሂም ሎቭ እንዲገመግሙት ለእሳቸው እንተው ብሏል።

«የተሻለ መጫወት እንችል እንደነበር እናውቃለን። ግን ሲመስለኝ ብዙ ለመናገር ጊዜው ገና ነው። የተጓደሉ ነገሮች አሉ፤ በእዚያ ላይ ቡድኑ ገና አልተግባባም፤ ግን አንዴ መጣጣሙ ሲመጣ ልክ እንደ ዓለም ዋንጫው አይነት ነው የምንጫወተው። በእዚህም አለ በእዚያ ግን ባገኘነው ሦስት ነጥብ መደሰት እንጂ ዝም ብሎ ድክመቶችን ብቻ እየነቀሱ መተቸት አያስፈልግም። ጨዋታውን የቡድኑ አሠልጣኝ በድጋሚ ሲመለከቱት ይተነትኑታል፤ ከእዚያም በድጋሚ ስንገናኝ ለእኛ ያሳዩናል።»

በጀርመን እና ስኮትላንድ ጨዋታ የጀርመኑ አማካይ ማርኮ ሮይስ ልክ እንደ ዓለም ዋንጫው ሁሉ አሁንም የቁርጭምጭሚት አደጋ ደርሶበታል። አሠልጣኙ ግን አደጋው ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ሲሉ ምኞታቸውን ገልጠዋል።

ትናንትና ከተከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች መካከል ወደ እግር ኳስ ማኅበሩ ብቅ ያለችው ጂብራልታር በፖላንድ የጎል ጎተራ ሆናለች። ካሚል ግሮሲኪ የመክፈቻዋን እና ሁለተኛዋን ግቦች በ11 እና 48ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር፤ 5ኛዋን ግብ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ሉቃስ ሱካላ ከመረብ አሳርፏል። ግብ አዳኙ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ከሐትሪክ አልፎ በአጠቃላይ አራት ግቦችን ለብቻው በማስቆጠር፤ በአጠቃላይ ፖላንድ ጂብራልታርን 7 ለዜሮ አዋርዳ ሸንታለች።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ባልተሰለፈበት ጨዋታ ፖርቹጋል በሜዳዋ በአልባኒያ 1 ለዜሮ ተሸንፋለች። ዴንማርክ አርመንያን ፣ ሰሜን አየርላንድ ሐንጋሪን እንዲሁም የአየርላንድ ሪፐብሊክ ጆርጂያን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ፊንላንድ ፋሮኤ ደሴቶችን 3 ለ1 ስትረታ፣ ግሪክ በሜዳዋ በሮማንያ 1 ለባዶ ተሸንፋ ነጥብ ጥላለች።

የመኪና ሽቅድምድም

ትናንት በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የጣሊያን ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን በመርሴዲስ ተሽከርካሪው ከኋላ ተነስቶ አንደኛ በመሆን አሸናፊ ሆኗል። የቡድን አባሉ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዘንበርግ በሁለተኛነት አጠናቋል። በአጠቃላይ ውጤት ግን ኒኮ ሌዊስ ሐሚልተንን በ22 ነጥቦች ልቆ ይገኛል። ኒኮ እስከዛሬ ባደረጋቸው የመኪና ሽቅድምድሞች አጠቃላይ ነጥቡ 238 ደርሷል።

ሴሬና ዊሊያምስ

ሴሬና ዊሊያምስ

የሜዳ ቴኒስ

በአሜሪካን የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ሴሬና ዊሊያምስ ለl18ኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን በሴቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር ኃያልነቷን አሁንም አስመስክራለች። ሴሬና ዊሊያምስ ካሮሊን ዎኒያኪን ትናንት በተከታታይ 6 ለ3 ለማሸነፍ ችላለች። የዊምብልደን አሸናፊ የነበረችው እና በማጣሪያው የተሸነፈችው የቼክ ሪፐብሊኳ ፔትራ ክቪቶቫ ሦስተኛ ደረጃን አግኝታለች። በነገራችን ላይ 33ኛ ዓመቷ ሊሞላ ትንሽ የቀረው ሴሬና ዊሊያምስ በሴቶችም ሆነ በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ታሪክ እንደእሷ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት ያገነ ስፖርተኛ የለም።

ሴሬና ውድድር በማሸነፍ ያገኘችው ከፍተኛው የገንዘብ ሽልማት 4 ሚሊዮን ዶላር ነው። በ15 ዓመታት የስፖርት ቆይታዋ 5 የዌምብልደን ጨዋታዎችን ጨምሮ ለ18 ጊዜያት ታላላቅ ውድድሮች ላይ ባለድል ለመሆን በቅታለች።

በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ደግሞ ያልተጠበቀ ክስተት ታይቷል። ታዋቂዎቹን እነ ሮጀር ፌዴረር እና ኖቫክ ጆኮቪችን በመርታት ከእዚህ ቀደም 10 ምርጥ ውስጥ እንኳን ያልገቡ ሁለት ስፖርተኞች ለፍፃሜ ደርሰዋል። ለፍፃሜ የበቁት ኬይ ኒሺኮሪ እና ማሪን ሲሊች ናቸው። ከ14 ዓመቱ አንስቶ አሜሪካን ውስጥ መኖር የጀመረው ኬይ ኒሺኮሪ የትውልድ ሀገሩ ጃፓን ውስጥ እጅግ ዝነኛ ነው። ኬይ ኒሺኮሪ ዝነኛው ጆኮቪችን 6 ለ4 እና 7 ለ6 አሸንፎ ነው ለፍፃሜ የደረሰው። ማሪን ሲሊች በበኩሉ ኃያሉ ሮጀር ፌዴረርን በግማሽ ፍፃሜው 6 ለ3 እና 6 ለ4 መርታት በመቻሉ ነው ለፍፃሜ የበቃው። በሜዳ ቴኒስ እጅግ ዝነኛ የሆነው የዓምናው ባለድል ራፋኤል ናዳል በቀኝ እጁ አንባር መዋያ ላይ በደረሰበት ጉዳት ዘንድሮ መወዳደር አልቻለም።

ሌዊስ ሐሚልተን

ሌዊስ ሐሚልተን

የዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ ፊፋ ፕሬዚዳንት፥ ለፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን እና ለጀርመኑ ባየር ሙንሽን ተሰላፊ የሆነ እውቅ ተጫዋችን ለመቅጣት ዛቱ። የ59 ዓመቱ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሚሼል ፕላቲኒ የ31 ዓመቱ ፍራንክ ሪቤሪ የሐገሩ ብሔራዊ ቡድን ሲጠራው ምላሽ ካልሰጠ እንደሚቀጣ አስታውቀዋል። ሪቤሪ የፈረንሣይ አሰልጣን ያደረጉለትን ጥሪ ለቤተሰቦቼ ጊዜ መስጠት አለብኝ በሚል ውድቅ በማድረጉ ነው ቅጣት የሚጠብቀው። በፊፋ ሕግ መሰረት የአንድ ሐገር ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ጥሪ ሲቀርብለት መቀበል አለበት። ሪቤሪ ለፈረንሣይ ተሰልፎ ለመጫወት አለያም ላለመጫወት ለብቻው መወሰን አይችልም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ሪቤሪ አሁንም የአሠልጣኙን ጥሪ ተቀብሎ ካልሄደ ለቡድኑ ባየር ሙንሽን ከመጫወት ሊታገድ ይችላል ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic