የአፍሪቃ ዋንጫና ገፅታዉ | ስፖርት | DW | 06.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የአፍሪቃ ዋንጫና ገፅታዉ

ኢኳቶሪያል ጊኒ ዉስጥ በመካሄድ ላይ ያለዉ የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ከወትሮዉ በተለየ ትናንት የበርካታ ተመልካቾችን ትኩረት ስቦ ነበር። በትናንቱ ጨዋታ ጋና ተፎካካሪዉ የነበረችዉን የአስተናጋጅዋን ሀገር የኢኳቶሪያል ጊኒን ቡድን ሶስት ለዜሮ ሊሸኝ ሲቃረብ ደጋፊዎች ግርግር ቢፈጥሩም ጨዋታሽ መልኩን ለዉጦታል።

ገና ከምድቧ ተጋጣሚዎች ጋ ጨዋታዉን አሀዱ ስትል ጋና በሴኔጋል ሁለት ለአንድ መረታቷ የደጋፊዎቿን ብቻ ሳይሆን የባለስልጣናቱንም ስሜት የነካ ነበር። ለዚህም ነዉ አንድ ባለስልጣን አድረዉ የሚሆነዉን ሳይመለከቱ በጨዋታዉ ማግስት ደካማ ቡድን በማሰለፋችን በወጣቶች የተገነባዉ ጥቁሩ ኮከብ እንኳን ለዋንጫ ሊደርስ ቀርቶ ገና ከተደለደለበት የሞት ቡድን ብዙም ሳይራመድ ተዘርሮ ይሰናበታል የሚል ትችታቸዉን በአደባባይ ለማሰማት የደፈሩት። ነገሩ በተቃራኒዉ ሆነና ቡድኑ ከአልጀሪያና ደቡብ አፍሪቃ ጋ ከባድ ፍልሚያዉን አልፎ ጊኒን ሶስት ለባዶ ቀጣ። ትናንትም የዘንድሮዉን የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገር የኢኳቶሪያል ጊኒን ቡድን ሶስት ለባዶ ሸኘ። አሁን ጋና ለ33ዓመታት የአፍሪቃ ዋንጫ ባለድልነትን በእጇ ለማስገባት አንድ ጨዋታ ብቻ ቀራት። አሰልጣኝ አይራም ግራንት ወጣቶችን ያሰባሰበዉ ቡድናቸዉ ካለፈዉ የዓለም ዋንጫ ወዲህ ትልቅ አስተሳሰብና መልካም አቀራረብ ማሳየቱን አፋቸዉን ሞልተዉ ለመናገር በቁ።

የትናንቱ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ እንደሌሎቹ ጨዋታዎች ሲካሄድ ቢቆይም እንደወትሮዉ በሰላም አልተጠናቀቀም። ጋና ሶስት ለባዶ እየመራች ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በቡድናቸዉ አጨዋወት የተበሳጩት የኢኳቶሪያል ጊኒ ቡድን ደጋፊዎች ጠርሙሶችንም ሆነ በእጃቸዉ ያለዉን ማንኛዉንም ነገር እያነሱ ወደሜዳዉ መወርወር ጀመሩ። በማላቦዉ ስታዲዮም የተገኙት የአስተናጋጅቱ ሀገር ቡድን ደጋፊዎች ወደተጫዋቾቹ ብቻ ሳይሆን ወደጋና ቡድን ደጋፊዎችም ፊታቸዉን አዞሩ ለጥቃት። የጥቁር ኮከቦቹ ደጋፊዎችም በሰዉ ሀገርና ሜዳ መሸሸጊያ መፈለግ ተገደዉ አመሹ። በዚህ ጊዜም ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ የቀረዉ ጨዋታ 30 ደቂቃዎች ያህል ተቋረጠ። የኢኳቶሪያል ጊኒ የፀጥታ ኃይሎች ተረባርበዉ ግርግሩን ካሰከኑት በኋላ ጨዋታዉን ዳኛዉ አስጀምረዉ የጋና አሸናፊነት ተረጋግጦ ተደመደመ። አክራ ላይ ሆነዉ ጨዋታዉን ሲከታተሉ የነበሩት የጋና ቡድን ደጋፊዎች በድሉ ቢደሰቱም አጋጣሚዉ የፈጠረባቸዉ ስሜት ግን የተለየ ነዉ።

«ይህ አሳፋሪ ነዉ፤ በጣም አስከፊ ነዉ፤ ማለቴ ፖሊስ እዚያዉ ነበረ፤ ወርማሪዎቹ እነማን እንደሆኑ ማየት ይችል ነበር እናም እየለቀመ ሊቀጣቸዉ ይገባ ነበር።»

«መደሰት ሲገባኝ ጋና ብታሸንፍም እፍረትና ዉርደት ነዉ የተሰማኝ። እዚያ የተደረገዉ ነገር የክፍለ አህጉሪቱን መጥፎ ገፅታ አሳይቷል። የምንሠራዉን መጥፎ ሥራ ይፋ አድርጓል፤ እንዲሁም የእኛ የትዕግስት ልክ እስከምን ድረስ እንደሆነም አመላክቷል።»

ዘገባዎች እንደሚሉት በተፈጠረዉ ግርግር 36 የጋና ቡድን ደጋፊዎች ተጎድተዋል። ጋናም ኤኳቶሪያል ጊኒ ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት እንዲወሰድ ጠይቃለች። የጋና የእግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝደንትና የአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮን ፌዴሬሽን ባለስልጣን ክዌሲ ኒያንታኪ CAF ጠንካራ ርምምጃ መዉሰድ ይኖርበታል ነዉ ያሉት። በዛሬዉ ዕለትም CAF በተፈጠረዉ ሁኔታ ኢኳቶሪያል ጊኒ 100 ሺ ዶላር እንድትከፍል ቅጣት ጥሎባታል። እንዲያም ሆኖ ግን የነገዉን ጨዋታ ለመመልከት የአስተናግጇ ሀገር ደጋፊዎች ስታዲዮም እንዲገቡ ተፈቅዷል።

ጨዋታዉ የሚጠናቀቀዉ የፊታችን እሁድ ነዉ። ለዋንጫዉ የሚፎካከሩት ደግሞ ጋናና አይቮሪኮስት ይሆናሉ። የቀድሞዉ የጥቁር ኮከቦቹ ተጫዋች እና የአሁኑ አሰልጣኝ ፌሊክ አቦአጌይ ዋንጫዉን ጋና የመዉሰዷ ነገር ተስፋ አለዉ ባይ ነዉ።

«በዚህ አጨዋወት እኔ ከፍተኛ እድል አላቸዉ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ጥቁር ኮከቦቹ እንዲህ ያለ አስደሳች እግር ኳስ ከተጫወቱ ረጅም ጊዜ ሆኗል። ሌላዉ ቀርቶ በዓለም ዋንጫ ላይ እንኳን እንዲህ ያለዉን ጨዋታ አላሳዩም። ዛሬ በጣም ግሩም ነበር ሁላቸዉንም በጨዋታቸዉ ተደስተናል እናም እሁድ ዕለትም ድንቅ ጨዋታ እንመለከታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

በነገዉ ዕለት ከኤኳቶሪያል ጊኒ ቡድን ጋ ለደረጃ የምትጫወተዉ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ናት። የDRC አሰልጣኝ በማላቦዉ ስታድዮም ለመጫወት ቡድናቸዉ አይፈራም ነዉ ያሉት። ዛሬ ለዘጋቢዎች እንደገለፁትም እሳቸዉም ሆነ ቡድናቸዉ የትናንቱን ትርምስ ወደጎን ብለዉ የእግር ኳሱና ድሉ ላይ ያተኩራሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic